ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

መርስዔሀዘን ወልደቂርቆስ (1891-1971 ዓ.ም)

REMEMBERING MERSIE-HAZEN WOLDEKIRKOS (1898-1978)

መርስዔሀዘን ወልደ ቂርቆስ ከአለቃ ወልደ ቂርቆስና ከወ/ሮ የሸዋ ወርቅ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ጅሩ አውራጃ በ1891 ዓ.ም ተወለደ። ወላጅ አባታቸው በቤተ ክህነት ትምህርት የገፉ ነበሩና ልጃቸውም በርሳቸው መንገድ እንዲያልፉ ይመኙ ስለነበር መንፈሳዊ ትምህርት የጀምሩት ገና አፍ መፍታት እንደጀመሩ ነበር፡፡ ወደተለያዩ አድባራትና ገዳማት እየተዘዋወሩም በቤተ ክህነት ትምህርት የተሻለ ዕውቀት ያስጨብጣሉ በሚባሉ ሊቃውንት ተምረዋል፤ በመጀመሪያ እንጦጦ መንፈሳዊ ት/ቤት ገብተው አለቃ ገ/መድህን በተባሉ መምህር ያሬዳዊ ዜማ እንዲሁም ቅኔ አጥንተዋል፤ የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ ከተባሉ መምህር ዘንድም የብለይ ኪዳን መጽሀፍትን ለሶስት አመታት አጥንተዋል፡፡  በዚህም ከአለቃ ታዬ ታሪክን ፣ከአለቃ ወልደጊዮርጊስ ጥበብን፣ ከአለቃ ገ/መድህን ደግሞ የዜማና ቅኔ ትምህርት ቀስመዋል

በነበራቸው የላቀ የመንፈሳዊ ዕውቀት የወንበር ፀሐፊ (የቤተ መንግስት ፀሐፊ) እንዲሆኑ ሲሾሙ ገና የ20 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ በጊዜው ሀይማኖታዊ መጽሀፍትን የሚተነትኑና የምዕመናንን መንፈሳዊ ግንዛቤ ያሳድጋሉ በሚል መንፈሳዊ መጻህፍትን የሚያዘጋጁ ሊቃውንትን ያካተተ የህትመት ኮሚቴ በወንበር ጽ/ቤት ስር ተዋቅሮ ነበር፡፡ መርስዔሀዘንም የዚህ ኮሚቴ አባል ሆነው ነበር ስራቸውን የጀመሩት፡፡ ለዘመናዊ ትምህርት በነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎትም ስራቸውን እየሰሩ በተገዳኝ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወስነው ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው ነበር፤ በአለቆቻቸው ጫና ምክንያት ግን መቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ይሁንና ራሳቸውን በንባብ በማብቃታቸው ልክ እንደመንፈሳዊ እውቀታቸው ሁሉ የአለማዊ ዕውቀታችውም የጠለቀ ነበር

መርስዔሀዘን በ1917 ዓ.ም የብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ሲቋቋም የወንበር ጸሀፊነት ስራቸውን ለቀው የጋዜጣው ምክትል አዘጋጅ ሆነው ተቀጠሩ፤ነገር ግን በጋዜጠኝነቱ ከስድስት ወር በላይ አልዘለቁም፤ በዚያው ዓመት ወደተከፈተው ተፈሪ መኮንን ት/ቤት በመምህርነት ተዛወሩ፤ በት/ቤቱ የአማርኛና ግእዝ ቋንቋ መምህር ሆነው እስከ 1922 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡ መርስዔሀዘን በተለይ የአማርኛ ቋንቋ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲጠና ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ቋንቋውን ከማስተማር በዘለለም ተማሪዎች በጥልቀት ለመገንዘብ የሚያስችሏቸውን አጋዥ መጻህፍትን በማዘጋጀት ይታወቃሉ

በ1918 ዓ.ም ያዘጋጁትና በ1935 ገደማ ደግሞ አስፋፍተው ለህትመት ያበቁት <በአዲስ የተሰናዳ የአማርኛ ሰዋሰው> በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአማርኛ ሰዋሰው መጽሀፍ ነው[1]፡፡ ይህ መጽሀፍ በትምህርትና ስነጥበብ ሚኒስቴር ተመርጦ ለሃምሳ አመታት ያህል (ከ1919-1969 ዓ.ም ድረስ) የተማሪዎች ማስተማሪያ ሆኖ አገልግሏል[2]፡፡ መርስዔሀዘን ወልደ ቂርቆስ በ1936 ዓ.ም ያዘጋጁት <የአማርኛ ሰዋሰው መክፈቻ> ፣ <የአማርኛ ሰዋሰው ለጀማሪዎች> በሚል በ1941 እና በ1942 ዓ.ም በሁለት ቅጾች አከታትለው ያሳተሟቸውን ጨምሮ ሌሎች ለቋንቋው ዕድገት በር ከፋች የሆኑ መጻህፍትን ጽፈዋል።

መርዔሀዘን ከኢጣሊያ ወረራ አመታት በፊት ያደርጉት የነበረውን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ በነጻነት ማግስትም አጠናክረው ነበር የቀጠሉት፡፡ የፋሽስት ጦር ተወግዶ ዘውዳዊው መንግስት ስልጣኑን መልሶ እንደጨበጠ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ተሾመው እስከ 1936 ዓ.ም ድረስ በዚህ ሃላፊነታቸው ቆይተዋል፤ ከ1936-1946 ዓ.ም በዘውዳዊው መንግስት የብሔራዊ ቤተመዛግብት ጽ/ቤት አስተዳዳሪ ነበሩ፤ የፍትህ ሚኒስቴር በምክትል ሚኒስትር ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ከ1950 እስከ 1963 ዓ.ም በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ዘውዳዊ መንግስት የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት)  በሬጅስትራርነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ በኋላም የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከ1963 ዓ.ም አንስቶ ከመንግስት ስራ በጡረታ እስከተገለሉበት 1966 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የቅርስ ጥበቃ ም/ቤት አማካሪ ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት መሰረት በተጣለባቸው ዓመታት ለዘርፉ ዕድገት ፋና ወጊ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት መርስዔሀዘን ከመምህርነት ስራቸው በተጨማሪ በትምህርቱ ዘርፍ በአመራር ሃላፊነት ቦታዎችም ያደረጉት ተሳትፎ ታላቅ ቦታን የሚሰጠው ነው፡፡ የትምህርት አሰተዳደር ስራቸውን ሀ ብለው የጀመሩት በጅግጅጋ ከተማ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የሆነው በቀድሞ ስያሜው የራስ መኮንን ት/ቤት (ባሁኑ ውቅት የጅግጅጋ ሼህ አብዱሰላም የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት የሚባለው) ነበር[3]፤ በ1922 ዓ.ም የተመሰረተው የዚህ ት/ቤት የመጀመሪያው ርዕሰ መምህር መርስዔሀዘን ወልደ ቂርቆስ ናቸው

መርስዔ ሀዘን ከትምህርት ዘርፍ ስራቸው በተጓዳኝ በጊዜው የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሶማሌ (ሶማሌላንድ) መካከል  የድንበር ማካለል ለሚያስፈጽመውና በሁለቱ አገራት በጋራ በተዋቀረው  ኮሚቴ ኢትዮጵያን ወክለዋል፤ ከ1923 እስከ 1927 ዓ.ም ድረስ በኮሚቴው በነበራቸው ቆይታ የአገራቸውን ጥቅም ለማስከበር በንቃት ተንቀሳቅሰዋል

በዘመናዊ የኢትዮጵያ ትምህርት ታሪክ የከፍተኛ ትምህርት የጅማሮ እንቅስቃሴዎች  የመርስኤ ሀዘን ሚና የላቀ ነበር፡፡ በአገራችን ቀዳሚው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1942 ዓ.ም ሲቋቋም የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የመጀመሪያው የቦርድ ሰብሰቢ እርሳቸው ነበሩ[4]

በ1953 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ  ወደ ዩኒቨርሲቲ አድጎ፣ መጠሪያውንም ‹ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ› በሚል ሲመሰረት የዩኒቨርሲቲው መሪ ቃል (Motto) የነበረው “ኩሉ አመክሩ ወዘ ሠነየ አጽንዑ” የሚል ነበር ። የአማርኛ ግርድፍ ትርጉሙ ሁሉን መርምሩ፣ የተሻለውን አጽኑ  የሆነውና ከክርስትና ቅዱስ መጻህፍት የተቀዳው ይህ  መሪ ቃል ለዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ቦርድ ያስተዋወቁት ደግሞ መርስኤሀዘን ወልደቂርቆስ ናቸው፤ ቦርዱም አጽድቆት ለበርካታ አመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ motto ሀኖ ቆይቷል [5]

መርስኤ ሀዘን የፍትህ ስርዓቱ ዘመናዊ ይሆን ዘንድ የነበራቸው ድርሻም ታላቅ ነበር፤ በመንፈሳዊና ባህላዊ ህጎች የተቃኙትን ጥንታዊ አገረኛ ህጎችን ከዘመናዊ የህግ መርሆችና አስተሳሰቦች ጋር በማዛመድ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዲኖራት የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በኢትየጵያ ዘመናዊ የህግ ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆነውና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዋና የህግ ማጣቀሻ ሆኖ ያገለገለው የ1953ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አርቃቂ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል።

መርስኤ ሀዘን ለታሪክ ትልቅ ቦታ ነበራቸው፤ ‹ታሪክ የሩቁን አቅርበው የሚያዩበት፣ ትናንሾችን አካላት አጉልቶ የሚሳይ እንደቴሌስኮፕ ያለ መሳሪያ ነው› ሲሉም የታሪክ አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡ በተለይም የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ በተጠናከረ ሁኔታ ይጠና ዘንድ የነበራቸው ሚና ትልቅ ነበር፡፡ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት ጽ/ቤት አስተዳዳሪ ሆነው ባገለገሉበት ወቅት ከ74 በላይ በሚሆኑ ጥራዞች  ታሪካዊ መዛግብትን አደራጅተዋል፤ እንዲሁም ጥንታዊ የታሪክ ድርሳናትን በመጠበቅ እንዲሁም የስነቃል ሀብትን በማሰባሰብና  በማደራጀት ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል

በግላቸው ባሳለፉት ዘመን የታዘቡትን፣ የሰሙትንና በቅርብ የሚያውቁትን በመመዝገብ የዘመኑን የኢትጵያ ማህበረ-ፖለቲካ እንድንገነዘብ የሚያስችሉ በርካታ የታሪክ መጽሀፍትን አዘጋጅተዋል፡፡በዚህ ረገድ፦ <በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ካየሁትና ከሰማሁት> (1935)፣ ‹የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመን › (1938)፣  <በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመን> (1938) መጽሀፍቶቻቸው ይጠቀሳሉ፤ እነዚህን ሶስቱን ጥራዞች ባንድ በማድረግ ልጃቸው አምሃ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ‹የሀያኛው ክ/ዘመን መባቻ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት (1896-1922)› በሚል በ1999 ዓ.ም ለህትመት አብቅተዋል

መርስኤ ሀዘን በዕድሜ ዘመናቸው በስራ ጉዳይም ይሁን በአጋጣሚ በአካል ተገኝተው ያዩትን የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ሁነቶችን የመመዝገብ ልምድ የነበራቸው መርስዔሀዘን በ1927 ዓ.ም በኦጋዴን በረሃ የዊልዊል ጦርነት በኢትዮጵያና በኢጣሊያ ጦር መካከል የተካሄደውን ውጊያ ውሎዎች መዝግበው ይዘው ለታሪክ አቆይተዋል፤ ሌሎች በርካታ የታሪክ መጻህፍትንም አዘጋጅተዋል፦ ‹የተመርጠ መንግስት ታሪክ በመወ አልሁ ለቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘኢትዮጵያ> (1943)፣ ‹አውደ መዋዕል (አልማናክ)› (1939)፣ ‹የኢትዮጵያ መዝገበ ዕለታት› (1939)፣ ‹የንጉስ ሳህለስላሴ ንጉሰ ሸዋ የመቶኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ›(1941)፣ <የአምስቱ የመከራ አመታት አጭር ታሪክ> (1937)::  ‹ታሪከ ዘመነ ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ፣ ከጸሀፈ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ › (1959)፣ ‹ ዜናሁ ለልዑል ራስ መኮንን ዘጸሀፎ ግራ ጌታ ሀይለ ጊዮርጊስ› (1965) ከብዙ በጥቂቱ የመርስዔሀዘን ትሩፋቶች ናቸው፤ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ በተለያዩ ወቅቶች ያደረጓቸውን ንግግሮች ‹ፍሬ ከናፍር ዘ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ› በሚል  በሰባት ቅጾች በመጽሀፍ መልክ አዘጋጅተዋል፡፡ የመጀመሪያው ቅጽ በ1944 ለህትመት ሲበቃ ሌሎቹ ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው በ1955፣ 1957፣ 1959፣ 1961፣ 1963፣ 1964 ታትመዋል

ከወጥ ታሪክ ቀመስ መጻህፍቶቻቸው በተጨማሪ ከውጭ ምንጭ ቀድተው በአማርኛ አሰናድተዋል፣ መርስኤ ሀዘን ወ/ቂርቆስ፡፡ በዚህ ረገድ በግሪካዊው የታሪክ ጸሀፊ ሄርዶተስ ‹The history of the antiquity› በሚል የተጻፈውን ‹የጥንት ታሪክ› በሚል በአራት ቅጾች (1947፣ 1948፣1948፣ 1952)፣ ድርሰቱ የሀርበርት ማኪ የሆነው ‹In search of science> መጽሐፍ  <ጥበብን መፈለግ፡ ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ› በሚል ተርጉመው ለህትመት አብቅተዋል

መርዔሀዘን በመንግስት የሃላፊነት ጫና ስር ሆነው በተለያዩ ማህበራዊና ሀይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የጎላ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበራቸው ተሳትፎ የጎላ ነው፡፡ ከ1939 እስከ 1953 ድረስ መጽሀፍ ቅዱስን በአማርኛ ቋንቋ  ለመተርጎም የተቋቋመው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ነበሩ፤ በተጨማሪም ፍትሀ ነገስትን  በአማርኛና በግዕዝ  ለማዘጋጀት በተሰየመው ኮሚቴ ከ1962 እስከ 1963 ዓ.ም ተሳታፊ ነበሩ

በተለያዩ አለማቀፍ የሃይማኖት ስብሰባዎች ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተክርስቲያንን ወክለው የተካፈሉት መርስዔሀዘን ወልደ ቂርቆስ የቤተ ክርስቲያኗ አምባሳደር ነበሩ ማለት ይቻላል፤ እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም የአለም የቤተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በሆላንድ አገር አምስተርዳም ከተማ ሲመሰረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ተሳትፈዋል[6]

[6] በምክር ቤቱ መስራች  ጉባኤ ላይ ቤተ ክርስቲያኗን የወከሉት ሌላኛው ኢትዮጵያዊ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሐረርጌ ሀገረ ስብከት  አስተዳዳሪ የነበሩት አቡነ ቴዎፍሎስ ናቸው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን እና በግብጽ ኮፕቲክ ቤተ-ክርስቲያን   መካከል ለዘመናት የቆየው አለመግባባት በሰላም ይፈታ ዘንድ የነበራቸው  ሚና ታላቅ ነበር፡፡ መርስኤሀዘን ወደ ግብጽ አሌክሳንደሪያ በተደጋጋሚ እየተመላለሱ ሁለቱን ቤተ ክርስቲያናት ለማስማማት በብዙ ጥረዋል፤ ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ የመሰየም ስልጣን ሊኖራት ችሏል[7]፡፡

[7] ለ1600 ዓመታት ያህል በግብጽ ኮፕቲክ ቤተ-ክርስቲያን ስር ሆና የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት የራስዋን ሊቀ ጳጳስ እንዲኖራት ጥያቄ ብታቀርብም በእስክንድሪያ ጳጳሳት ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡የግብጽ ቤ/ክ ሀሳቡን የምትቃወመው በ325 ዓ.ም በተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ኢትዮጵያውን ሊቀ ጳጳሳት እንዳይኖራቸው፣ የሚሾመው ጳጳስም ለዘለኣለም የግብጽ ሰው እንዲሆን ተደንግጓል በማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ደግሞ የግብጽ ጳጰሳት የአገሩን ቋንቋ የማያውቁና በዚህም  በሚገባ ማስተማር የማይችሉ መሆናቸውን ፣ የኒቂያ ጉባኤ ለተባለውም ግብጻዊያንን ብቻ እንጂ የሌሎች እህት ቤተ ክርስቲያናትን ያላሳተፈ፣ ኢትዮጵያም ክርስትናን የተቀበለችው የኒቂያ ጉባኤ ከተደረገ በኋላ በመሆኑ በኒቂያው ህግ ተገዥ መሆን ግዴታዋ እንዳልሆነ፣ ክርስትና የዘር ልዩነት የማያደርግ መሆኑ፣ እንዲሁም የግብጽ ፓትርያርክ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ስትወረር ጥለው ወደ ግብጽ መሄዳቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን መሪ አልባ አድርጓት እንደነበር በማውሳት አበክረው በመከራከራቸው ግብጾችም ኢትዮጵያ የራሷ ፓትርያርክ እንዲኖራት ፈቀዱ፡፡ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓ.ም በግብጽ ካይሮ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴና ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው በተገኙበት ኢትዮጵያዊው ጳጳስ አቡነ ባስልዮስ በግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ቂርሎስ  ተቀቡ፡፡

በጊዜው ሀይማኖታዊ መጽሀፍትን የሚተነትኑና የምዕመናንን መንፈሳዊ ግንዛቤ ያሳድጋሉ በሚል መንፈሳዊ መጻህፍትን የሚያዘጋጁ ሊቃውንትን ያካተተ የህትመት ኮሚቴ በወንበር ጽ/ቤት ስር ተዋቅሮ ነበር፡፡ መርስዔሀዘንም የዚህ ኮሚቴ አባል ሆነው ነበር ስራቸውን የጀመሩት፤ በዚህም በርካታ ሀይማኖታዊ መጻህፍትን ጽፈዋል፣ ተርጉመዋል፡፡ ከነዚህም መካከል፡- ‹ትምህርተ ህጻናት› (1917)፣ ‹ሰማዕተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትጵያዊ› (1943)፣ <መጽሀፈ ቅዳሴ (በግእዝና በአማርኛ (1920)፣ ‹የመጀመሪው ኢትዮጵዊ ፓትርያርክ› (1956)፣ ‹ወንጌል ቅዱስ › (1916)፣ ‹መጽሀፈ ሲራክ› (1914)፣ ‹አረጋዊ መንፈሳዊ› (1922)፣ <ሰባቱ ኪዳናት(1920) <የቤተክርስቲያን ጸሎት> (1936)፣ ‹የቤተክርስቲያን ዜና› (1938)፣ ‹መጽሀፈ ቅዳሴ> (1926)፣ ‹The Liturgy of the Ethiopian Church>( 1954)፣ <መጽሀፍ ቅዱስ፡የብሉይና የሀዲስ ኪዳን መጽሀፍት> (1953)፣ <ፍትሀ ነገስት> (1962) ይገኙበታል::

ኢትዮጵያን ለዘመናት በሁለገብነት ያገለገሉት መርስዔሀዘን ለዘርፈ ብዙ አበርክቶታቸው በርካታ ሽልማቶችንና ዕውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡ ለአማርኛ ቋንቋ ዕድገት ላበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ በ1964 ዓ.ም የቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ የሽልማት ድርጅት የስነ ጽሁፍ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ በቤተሰቦቻቸው፣ በአድናቂዎቻቸው ትብብር በስማቸው ፋውንዴሽን ተቋቁማል፡፡ ባለትዳርና የሶስት ወንዶችና ሶስት ሴት ልጆች አባት የነበሩት ብላቴን ጌታ መርስዔሀዘን ወልደ ቂርቆስ በጥቅምት ወር 1971 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ ስርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባው የካ አቦ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

ዋቢ መጽሀፍት (Books) እና የጥናት ስራዎች (Articles) ዝርዝር

List of References used to Prepare biography of Blaten-getal Mersie-Hazen Woldekirkos

[1] Amare Asgedom, 2005, page 12

[2] መርስዔሀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ የሃያኛው ከ/ዘመን መባቻ፡ ካየሁትና ከሰማሁት፣ ገጽ 283

[3] Two Leading Ethiopian Writers, Journal of Semetic Studies, Vol25, No.1, 1980 , page 89.

[4] Amare Asgedom, 2005. Higher Education in Pre-Revolution Ethiopia: Relevance and Academic Freedom , The Ethiopian Journal of Higher Education Vol. 2 No. 2

[5] The Reporter(English)News Paper, 31 July 2004.


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in , , , , , , , , ,

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading