ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

እኛ ኢትዮጵያዊያን የአባይን ጉዳይ አሸንፈናል፤ አሁን የቀረን ራሳችንን ማሸነፍ ነው!

. መግቢያ

ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በአባይ ወንዝ ላይ ያለንን ቁጭት በብዙ መልኩ ስንገልጽ ኖረናል፤ አዝማሪው በድምጹ፤ ጸሐፍት በብዕራቸው፤ ተዋንያን በመድረክ ቴአትሮችና ፊልሞች እንዲሁም ምሁሩ በጥናትና ምርምሮቹ ስለአባይ ተክዘው ኖረዋል፤ እንደመታደል ሆኖ ይህ ትውልድ ከዚህ ትካዜ ለመላቀቅ የሚስችለውን አኩሪ ገድል ችግሮች  ሳበግሩት አባይን በአገሩ አስሮ ለሃይል ማመንጫነት፣ ለአሳ ሃብት ልማት እንዲሁም ለቱሪዝም ወዘተ አውሎታል

አሁን የበረታብን ትልቁ ተግዳሮት ከራሳችን ጋር ያላቆምነው ጦርነት ነው፤ የዘመናችን የኢትዮጵያ ችግር እኛ ህዝቦቻ ራሳችንን ማሸነፍ አለመቻላችን ነው! ራስን ለማሸነፍ እንቅፋት ከሆኑብን ነገሮች ዋናው ስለጉዳዩ ያለን የተሳሳተ ግንዛቤ/አተያይ ነው፤ ለብዙዎቻችን ራስን ማሸነፍ መሸነፍ ነው፤ ራስን ማሸነፍ ደካማነት ነው፤ ነገር ግን ራስን ማሸነፍ ጀግንነት ነው፤ ሽንፈት ሳይሆን ድል ነው፤ ራሱን ያሸነፈ ከራሱ አልፎ በዙሪያው ላሉ ሁሉ መፍትሄ ይሆናል

እኛ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ከመረመርነው የችግሮቻችን ሁሉ መሰረት የሚሆነው ከራሳችን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባታችን ነው፤ ራሳችንን አለማሸነፋችን ነው፤ ሁላችንም ደረጃው ወይም ፈርጁ ይለያይ  እንጂ ከራሳችን ጋር ጦርነት ላይ ከከረምን ውለን አድረናል፤ በመሬት ላይ የምናየው የህዝብ ምስቅልቅል የፖለቲከኞች ቁማር እና/ወይም ዳፋ ብቻ አይደለም፤ እያንዳንዳችን ዛሬ ላለንበት አስከፊ ሁኔታ ድርሻ አለን

ይህ አጭር መጣጥፍ በሚከተሉት ነጥቦች ዙሪያ ዳሰሳ ያቀርባል፡-

  • ለመሆኑ ራስን ማሸነፍ ምን ማለት ነው?
  • ራሱን ያላሸነፈ ሰው ባህሪያት መገለጫዎች ምንድናቸው?

ለመሆኑ ራስን ማሸነፍ ምን ማለት ነው?

በማህበረሰባችን ውስጥ ብዙ ጊዜ እንደታዘብኹት ራስን ማሸነፍ ከአልሸነፍ ባይነት ጋር ማምታታት አለ፤ ሰዎች ራሳቸውን ማሸነፍ የሚያቅታቸው ራሳቸው ከሌሎች አንጻር እያወዳደደሩ በሚፈጠርባቸው የስሜት ምስቅልቅል ከህሊናቸው/ከእውነት ጋር የሚያደርጉት እሰጥ-እገባ ነው፤ በእኔ አረዳድ ፉክክር፣ ውድድር መሆን ያለበት ከራስ ጋር ነው፤ ጦርትን ግን ከራስ ጋር መግጠም ትርፉ  እብደት ነው

ከራስ ጋር የሚደረግ ጦርነት መንስኤው አሉታዊ የሆነ የውስጥ መንፈስን ለማረቅ ካለመፈለግ/ዝግጁ ካለመሆን የሚመነጭ ነው፤ ከራስ ጋር ጦርነት አንድ ሰው አሉታዊ ስሜቶችን ለመሸሸግ ከህሊናው ጋር የሚያደርገው ግብ ግብ ወይም ሽኩቻ ነው፤  ከራስ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ቅንነትን፣ ሃቅን፣ መተሳሰብን፣ ፍቅርን ጋርዶ በግለሰብ፣ በቤተሰብ በማህበረሰብ፣ በህብረተሰብ እንዲሁም በህዝብ አብሮነትና፣ አንድነት፣ ሰላም እና ደህንነት ላይ ትልቅ ጋሬጣ ይሆናል፤ በአጠቃላይ ከራስ ጋር የሚደረግ ጦርነት ራስን ካለማሸነፍ ይመነጫል

ራሱን ያላሸነፈ ሰው ባህሪያት መገለጫዎች ምንድናቸው?

በመሰረቱ ከራስ ጋር የሚደረግን ጦርነት ማሸነፍ አይቻልም፤ በእኔ አረዳድ ራስን ያለማሸነፍ መገለጫዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

  • ከራሱ ጋር የተጣላ ሰላም የለውም፣ ለሌሎችም ሰላም አይሰጥም
  • ከራሱ ጋር የተጣላ እውነትን ለመቀበል ይቸግረዋል፣ በመሆኑም ራሱን ሲዋሽ ይኖራል
  • ከራሱ የተጣላ ፍቅር የለውም፤ ፍቅር መስጠት አለመቻሉ ሳይጎዳ ፍቅር መቀበል አለመቻሉ ሌሎች ስለፍቅር የሚከፍሉትን መስዋዕትነቶች አይገቡትም ወይም ዋጋ ያሳጣቸዋል
  • ከራሱ የተጣላ የፍቅር እሴቶች የሆኑት፣ ማለትም ይቅርታ ማድረግ፣ መጸጸት፣ መከባበበር፣ መደማመጥ፣ እና መተሳሰብ አይኖሩትም፤ ከራሱ የተጣላ እነዚህን የፍቅር እሴቶች ለራሱም ሆነ ለሌሎች አይሰጥም፣ አይቀበልምም
  • ከራሱ የተጣላ ስለራሱ ለማሰብ ጊዜም የለውም፣ ምክንያቱም አእምሮውን በማይጠቅሙት ነገሮች ሞልቶ የአእምሮን የማሰብ፣ የማሰላሰል እንዲሁም የማስታወስ አድማስ ስለሚጠብ የራሱን ችግር ነቅሶ ማውጣት፣ መፍትሄም ለማበጀት አይችልም፤ የቅናትና የምቀኝነት መንፈስ ያጠቃዋል
  • ከራሱ የጣላ ለችግሮቹ መፍትሄ ሳይሆን ተጨማሪ ችግር ፈጥሮ ራሱንም ሆነ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ሲያስቸግር ይኖራል፤ የራሱን ችግር በሌሎች በማሳበብ፣ ራስን ነጻ ለማውጣት ከንቱ መባዘን ውስጥ ይገባል
  • ራሱን ማሸነፍ ያቃተው ሰው ስሜተ-ድንዙዝ ነው፤ ምን እንደሚያስደስተው፣ ምን እንደሚያስከፋው፣ ምን እንደሚያስተክዘው፣ ወዘተ…. ራሱም አያውቅም፣ ሌሎችም አያውቁም፤ በዚህም በድብርት፣ በጥላቻ፣ በመሰላቸት ድባብ ውስጥ መኖር መገለጫው ነው፤ እነዚህን አሉታዊ ስሜቶቹን ለማስታገስ ሁልጊዜ በአሉታዊ ድርጊቶች ውስጥ ራሱን ያገኘዋል
  • ራሱን ማሸነፍ ያቃተው ሰው ለመንፈሱ ምግብ ስለሚነፍጋት መንፈሱ የመነመነች ናት፤ መንፈሱ ደካማ ናት፤ በመሆኑም ነገሮችን/ችግሮችን የመቻልና የማሳለፍ አቅም የለውም፤ ቶሎ ሆድ ይብሰዋል፣ ራሱ በደለኛ ሆኖ ሳለ ተበዳይ ሆኖ ይቀርባል፤ ሁልጊዜ የተጠቂነት ስሜት ይዞ ይኖራል፤ ስሜቱን መግራት ስለማይችል ንዴቱንም ሆነ ደስታውን መቆጣጠር ይሳነዋለው፤ በመሆኑም በደስታውም ሆነ በንዴቱ ጊዜያት ሁሉ በዙሪያው ባሉ ሁሉ ሁከትን ይፈጥራል፤ በዚህም ራሱ ባተሌ ሆኖ ሌሎችንም ባተሌ ለማድረግ ይሞክራል
  • ራስን ማሸነፍ ችግር ፈቺ ከመሆን ይልቅ ችግር ተንታኝ ይሆናል

እንደመውጫ

ዛሬ እንደአገር እና እንደህዝብ የገጠመን ትልቁ ችግር ራሳችንን ማሸነፍ አለመቻላችን መሆኑን ተገንዝበን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድልን ስናስብ ከራሳችን ጋር ከገባንበት ጦርነት ለመላቀቅና ራሳችንን ድል ለማድረግ ቆርጠን በመነሳት መሆን ይገባል!

በመጨረሻም መጪው አዲሱ አመት ኢትዮጵያዊያን ራሳችንን የምናሸንፍበት አመት እንዲሆን ፈጣሪ ይርዳን!


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading