እንደመግቢያ
የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ በተሰናዳ የብልጽግና ፓርቲ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ያደረጉት ንግግር አወዛጋቢ ነበር፡፡ የዚህ ጽኁፍ ጭብጥ ስብዕናን በሚነካ መልኩ በምሁራዊ እሴቶች (virtues of intellect) ጉዳይ ላይ ያነሱትን ዘለፋ አይነት ንግግር መነሻ እና እንድምታዎች መፈተሸ ነው፡፡
አንባቢ እንዲገነዘብልኝ የምፈልገው በጠቅላዩ ንግግር ላይ መልስ ለመስጠት መሞከሬ ጉዳዩ መልስ ለመስጠት የመሚመጥን ሆኖ ሳይሆን ቢያንስ በግሌ ከእርሳቸውና ከአመራራቸው ብዙ በጎ ነገሮች እጠብቅ ስለነበር ነው፡፡ ንግግራቸው የስሜት መጎዳት (ንዴት) የፈጠረብኝ ቢሆንም ይህን መጣጥፍ የማሰናዳቱ መነሻ በሃሳብ ለመሞገት እንጂ የዶር አብይና ደጋፊዎቻቸውን ስብዕና ለመንካትም አይደለም፡፡ የሃሳብ ሚዛናዊነትን መጠበቁ ሙያዬም (የአካዳሚክ ሰው ነኝ) ያስገድደኛል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህን ጽሑፍ ለማሰናዳት በመጀመሪያው ከብስጭት ስሜት ለመውጣት አንድ ሁለት ቀናትን የማገገሚያ ጊዜ መውሰድ ነበረብኝ፡፡ በሀተታዬ እኔ ወደምፈልገው ድምዳሜ ለመድረስ ከመፈለግ አንጻር ስህተት እንዳልሰራ (በስነ አመክንዮ ትምህርት ይህ አይነት ስህተት fallacy of deductionism ይባላል) ወይም ስሜት-መር ድምዳሜ ላይ ላለመድረስ በተቻለኝ መጠን ለመጠንቀቅ ሞክሬአለሁ፡፡

ዶ/ር አብይ እንደ አገር መሪ እና እንደ ፖለቲከኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን ከጨበጡበት ካለፉት ሁለት አመታት ገደማ ጀምሮ ንግግሮቻቸውን በትኩረት ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ በአብዛኛው የስልጣን ወራቶቻቸው የንግግሮቻቸው ዓላማ እና ጭብጥ አገራዊ አንድነትን ስለማምጣት እና በጽኑ ተሸርሽሮ የነበረውን የመንግስት ቅቡልነት መጎዳት ለመጠገን ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ አንድነትን ኣላማ ባደረገ ንግግሮቻቸው ብስለትን፣ አስደማሚ የሃሳብ ፍሰት፣ ለንግግሮቻቸው አስረጅ ሲያደርጉ ተጨባጭ ሀቆችን፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እና ጽንሰ ሃሳባዊ እና ፍልስፍናዊ ድጋፎችን በማቅረባቸው በአጭር ጊዜ በህዝብ ልብና አእምሮ እንዲገቡ አድረጓቸዋል፡፡
በመሰረቱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር ዓላማውን አገራዊ አንድነት እና ህዝባዊ ወንድማማችነትን ካደረገ ንግግር በቅርጽም ሆነ በአቀራረብ የተለያየ ነው፡፡ በእኔ እምነት ዶር አብይን በፖለቲካዊ ንግግሮቻቸው እምብዛም የምናውቃቸው አይመስለኝም፡፡ በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ በያዝነው ዓመት ዕውን መሆኑን ተከትሎ ግን ፖለቲከኛውን አብይ አህመድ ማየት ጀምረናል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ተገኝተው ትልልቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎችም ሆነ ስብሰባዎች ላይ ከተናገሩት እንደተረዳሁት ተቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ዋነኛ መለያ የሆነው የፖለቲካ ልሂቃን ሃሳባቸውን የሚሸጡት አግባብ ሃሳብ ላይ እንዲያተኩር መፈለጋቸውን ነው፡፡ ነቀፋ፣ ጠለፋ እና ሴራ መለያው የሆነው የፖለቲካ ገበያችንን ለማስተካከል የሚያደርጉትን ጥረት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓት ለማስተካከል የዚህ ትውልድ ትልቅ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ለዚህ መሳካት ሁሉም ኢትዮጵዊ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት እላለሁ፡፡
ነገር ግን በቅዳሜው ንግግራቸው ራሳቸው ዶር አብይ ወደ ብሽሽቅ ፖለቲካው እየተንደረደሩ እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡
የዶ/ር አብይ ንግግር እንድምታ ምንድነው?
ለብልጽግና ፓርቲ ገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው መድረክ የፓርቲው ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር አብይ ምስጋና ለማቅረብ ወደ መድረኩ የወጡ ቢመስልም ባለሃብቶችን ለማወደስ ምሁራንን መውቀስ ለምን እንደፈለጉ አላውቅም፡፡ ፖለቲካዊ አላማ አለው እንዳይባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ድጋፍ መሰረታቸው ነጋዴው ማህበረሰብ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡
በመሰረቱ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ነጋዴውም ሆነ ምሁራን የአገዛዞች የፖለቲካ ተጠቂዎች እንጂ የድጋፍ መሰረቶች የነበሩበት ወቅት የለም፡፡ ዶ/ር አብይ ነጋዴውን(ባለሃብቱን) የፓርቲቸው የድጋፍ ማህበራዊ መሰረት ለማድረግ አስበው ቢሆን እንኳ በባለሃብቱ እና በምሁራኑ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል የፍላጎት ተቃርኖ (conflict of interest) አይታየኝም፡፡ በመሆኑም ሁለቱ የማህበረሰብ ክፍሎች የፖለቲካ ባላንጣ ሊሆኑበት የሚያስችል ንድፈ-ሃሳባዊ አስረጅ የለም፡፡ እንዲያውም የዳበረ የካፒታሊዝም ስርዓት በሚከተሉ አገሮች እንደምናየው የኢኮኖሚው መሰረት የንዑስ ከበርቴው ማህበረሰብ ክፍል ከምሁራን ጋር በጥምረት መስራታቸው ነው፡፡ የካፒታሊዝም ስርዓት በሰው ልጅ ታሪክ ከታዩ የተለያዩ ስልተ-ምርት ዓይነቶች የተሻለ ስኬታማ የሆነበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡
በአጠቃላይ በንድፈ ሃሳባዊም ሆነ በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ታሪካዊ እውነታ መነጽር አስረጅነት ባለሃብቱ እና ምሁሩ ክፍል የፍላጎት ተቃርኖ የላቸውም።
ይህ በሆነበት ሁኔታ ታዲያ ዶር አብይ ይህን ንግግር እንዲደርጉ ያደረጋቸው ምክንያት ነባራዊም ሆነ ጽንሰ ሃሳባዊ እውነታ አለው ለማለት አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ የዶ/ር አብይ የአመራር ፍልስፍናዊ መሰረት ሆነው የመደመር ቀመር ሁሉም ሙያ/ዘርፍ ተደጋጋፊ እንደሆነ አስረግጦ ያስረዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የፓርቲያቸው ብልጽግና ስብእናዊ መሰረት የሆኑትን እውነት እና እውቀት የሚጻረር ነው፡፡
ዶር አብይ በንግግሮቻቸው ደጋግመው እንዳወሱት ፓርቲቸው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አንጻር በሃሳብ መስመር ለመሞገት በቂ አማራጭ ሃሳቦች አሉት፡፡ የፓርቲያቸው የፖለቲካ መሪ ጽንሰ ሃሳብ የመደመር ፍልስፍና፣ ግቡ ደግሞ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሆነ በንግግሮቻቸው ደጋግመው አውስተዋል፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ለሚነሱባቸው ወቀሳዎችም ሆነ ተቃውሞዎች መልስ ለመስጠት እንደምታ ያለው ቃላት ወይም ሽሙጦችን ጣል ማድረጋቸው ቢስተዋልም መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንዳደረጉት ንግግር በምንም መልኩ በጎ ጎኑን ለማየት የሚያስቸግር ንግግር አልሰማሁም።
በእኔ እምነት ለአወዛጋቢው የዶር አብይ ንግግር ሶስት መላምታዊ ገፊ ምክንያቶች አሉ፡፡
የመጀመሪያው ዶ/ር አብይ ጉምቱ የፖለቲካ ተገዳዳሪዎቻቸውን በሙያቸው (በተማሩት ትምህርት መስክ) በማስታከክ ለመሸንቆጥ ያደረጉት ሙከራ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢዜማው መሪና የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ብርሃኑ ነጋ፣ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች የሆኑትና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኖቹ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ጃዋር መሃመድ የዶ/ር አብይ የቃላት ጥይት ኢላማ እንደሆኑ ይገመታል።
ሁለተኛው የዶር አብይ ንግግር ገፊ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ምሁራን ያስተላለፉት መልዕክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር የከፍተኛ ትምህርት ቁንጮ የሆኑት ምሁራን ለሃገር በቀል ዕውቀት መስፋፋት ካላቸው ጉጉት አንጻር (የምር ከሆነ) ተጨባጭ አገራዊ ችግሮች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ከማሳሰብ አኳያ ሊሆን ይችላል፡፡
ሶስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሁርነት እና ምሁራዊ እሴቶች ያላቸው የተዛባ አመለካከትና የተሳሳተ ግንዛቤ ሊሆን ይችላል፡፡
የዶር አብይን ንግግር ከላይ በተጠቀሱት ሶስት መላምቶች አግባብ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡
የዶ/ር አብይ የፖለቲካ አመራር ተክለ-ስብዕና እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጨባጫዊ እውነታዎች
የዶር አብይን ንግግር በአውዱ ለመተቸት እንዲያመች እንደ አገር መሪና እንደ ፖለቲከኛ የተክለ-ስብዕናቸው መሰረት የሆኑ ጉዳዮችን ማጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በእኔ ግንዛቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግስታዊ (ቢሮክራሲያዊ) አስተዳደር ስብዕናቸው እና በፖለቲካ አስተዳደር ስብዕናቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ በመንግስታዊ አስተዳደራቸው ሰውን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር ፍልስፍና አላቸው፡፡ በፖለቲካዊ ስብዕናቸው ደግሞ ከተለመደው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ወጣ ባለ መልኩ ከሴራ እና መጠላለፍ ይልቅ የፖለቲካ ልሂቃን መርህን እና አማራጭ ሃሳብን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚሹ ይመስሉኛል፡፡
ዶር አብይ በቅርቡ ለንባብ በበቃው መደመር መጽሃፋቸው እንዳስነበቡን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ለማሻሻልና የሰለጠነ ክርክር እንዲኖር ለማስቻል ፖለቲከኞች በአማራጭ ሃሳብ ቢቀርቡ፤ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት አግባብ ደግሞ ከክርክር ይልቅ በንግግር (በውይይት) መንፈስ ቢቃኝ የተሻለ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያታቸውን ሲስቀምጡ ነባራዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልሂቃን የክርክር ባህል በብዙ ህጸጾች የተሞላ በመሆኑ ነው፤ ዶር አብይ የሚያመላክቱት አንዱ የከርክር ግድፈት የተናጋሪውን ሃሳብ እና የተናጋሪውን ስብዕና ለመለየት አለመቻል (አለመፈለግ) ነው፡፡ በዚህም ሃሳቡን ከመሞገት ይልቅ የተናጋሪውን ስብዕና መንካት የተለመደ በመሆኑ የሃሳብ ልዩነቱን በሰለጠነ መልኩ ለማቅረብ እና ለማስረዳት ያስቸግራል፡፡ በውጤቱም ፖለቲካ የህዝብ ችግር መፍቻ መድረክ ሲገባው እንዲያውም ወደ ሙግት እና አተካሮ እንዲሁም ህዝብን ወደ መከፋፈል የሚወስድ ነው፡፡ እኔም ይህን የምጋራው ነው፤ የፖለቲካ ስርዓታችን መለያ ከሆኑት አንዱ የሆነው ዋልታ-ረገጥ የፖለቲካ አጀንዳዎች (polarized political agenda) ምክንያትም ይህ የተበላሸው ሃሳብ ልዩነታችንን የምናስተናግድበት አግባብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፖለቲካዊ ስብዕና መሰረት ይህ ከላይ የተገለጸው እንደሚሆን አገምታለሁ፡፡
በእኔ እምነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር መነሻ ነተራራቀ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይሆን ልሂቃኖቻችን ስብዕና ከመርህ ይልቅ በሴራ እና መጠላለፍ (የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያጠኑ ምሁራን ይህን የሸዋ ፖለቲካ ይሉታል) ጊዜያቸውን ስለሚያባክኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ልሂቆቻችን መርህን መሰረት አድርገው ፖለቲካ ስራቸውን ቢሰሩ የኢትዮጵያ አብዛኛው ችግር ይቀረፋል እላለሁ፡፡ ነገር ግን ነባራዊው የፖለቲካ ጨዋታ ህግ መርህ ባልሆነበት ሁኔታ እንደ ዶር አብይ መርህ እና ሃሳብ ላይ መሰረት አድርጎ ለሚሰራ ፖለቲከኛ አስቸጋሪ፣ አንዳንዴም የሚያበሳጭ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ስርዓት መለያ መርህ እና አመክንዮ ባልሆነበት ሁኔታ አንድ ፖለቲከኛ ሃሳቡን ለመሸጥ ከራሱ እምነት ወይም መርህ አንጻር ሊወጣ የሚችልባቸው (የሚገደድባቸው) ሁኔታዎች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ በእንዲህ አይነቱ ሁኔታ የፖለቲካ ጨዋታን ለማሸነፍ የተገዳዳሪዎችን አቋም (ሚዛን) መመልከት የግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ መርህ የሚከተለው ፖለቲከኛ በቀላሉ በሴረኞች ወጥመድ ውስጥ የሚገባበትና ከፖለቲካ ጨዋታው በሽንፈት የሚወገድበት ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡
በእኔ መረዳት ዶር አብይ በፖለቲካዊ ስብዕናቸው ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ከራሳቸው ፍላጎት (እምነት) አንጻር ያለውን ጎን እንጂ ከተገዳዳሪዎቻቸው አንጻር ያለውን ገጽ ለማየት እምብዛም ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በአመዛኙ ከሃሳብ ይልቅ በትንኮሳ፣ በግለሰባዊ ብሽሽቅ እና በሴራ የተሞላ እንደመሆኑ ዶር አብይ ለዚህ የሚሆን ባህሪያዊ ማስተካከያ ይኑራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ከዚህ ጽሑፍ ጭብጥ እና ኣላማ አካያ ከእርሳቸው በተቃራኒ ያሉት ሶስት ፖለቲከኞችን በስም መጥቀስ ይኖርብኛል፡፡ እነርሱም ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ጃዋር መሃመድ ናቸው፡፡ ዶር አብይ ከእነዚህ ሶስት ተጽዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ሰዎች አንጻር በፖለቲካ ልምድ እና በፖለቲካዊ ተክለስብእና የተለዩ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ እና ፕሮፌሰር መረራ ተጨባጩን የኢት|ዮጵያ የጨዋታ ሜዳ እና ህግ ጠንቅቀው ያውቁታል፤ በምን ሰዓት ምን መናገር እንዳለባቸው ጨምሮ በፖለቲካዊ ንግግሮቻቸው የሰከኑ፣ ከመናገራቸው በፊት ንግግራቸው ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት አውቀው ወይም ፈልገው ነው፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ አቶ ጃዋር መሃመድ ምንም እንካ በፖለቲከኛነት ብዙም ልምድ ባይኖረውም የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር መሆኑ ቢያንስ ፖለቲካን በነቢብ ያውቀዋል፡፡ ከዚህም በላይ የጃዋር የፖለቲካ ተክለ-ስብዕና እንደኢትዮጵያ አይነት ሴራ እና መጠላለፍ ለበዛበት ፖለቲካ ስርዓትን ለመዘወር የሚመች ነው፡፡
መሰረቱን መርህ ያደረገና ከራሱ አንጻር ፖለቲካን የማየት ስብዕና ያለው ፖለቲከኛን በቀላሉ ንዴት እና ስሜት ውስጥ ማስገባት ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት ፖለቲከኛ በተገዳዳሪዎቹ ከሚፈተንባቸው መንገዶች አንዱ ለሚሰነዘርበት ፖለቲካዊ ትንኮሳዎች መልስ የሚሰጥበት አግባብ የበዛ ወይም የማይመጣጠን የመልስ ምት መስጠት፣ በዚህም የፖለቲካ ነጥብ እንዲጥል መሆኑ ነው፡፡ ዶር አብይ ሰሞኑን በሚሊኒየም አዳራሽ ያደረጉት ንግግር ተገዳዳሪዎቻቸው የሆኑትን የኢዜማው መሪና የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ብርሃኑ ነጋ፣ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች የሆኑትና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኖቹ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ጃዋር መሃመድ በሙያቸው (በተማሩት ትምህርት መስክ) በማስታከክ ለመሸንቆጥ ያደረጉት ሙከራ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ በእርግጥም ዶር አብይ በዚህ ንግግራቸው ከባድ ነጥብ የጣሉ ይመስለኛል፡፡ እኔም ብሆን የጠቅላዩን የፖለቲካ ብስለት እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ምሁራንን መውቀስ የማይቻልባቸው ምክንያቶች
ከዚህ መጣጥፍ ጭብጥ እና አላማ አንጻር ቀደም ብለው ከተገለጹ ሶስት መላምቶች ሁለተኛው የአወዛጋቢው የዶር አብይ ንግግር መግፍኤ ለአገር በቀል ዕውቀት ጉጉት ስላላቸው፤ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ችግር ፈቺ እና ተጨባጭ ችግር በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲመራመሩ ከመፈለግ የመነጨ፣ እንደ አገር መሪ የሰጡት አባታዊ ተግሳጽ ሊሆን ይችላል (ይህን እኔ ባላምንበትም ሌሎች የሚያነሱት መከራከሪያ ሊሆን ይችላል)፡፡ የሆነው ሆኖ ጠቅላያችን ከትምህርት ዘርፉ እና ከምሁራን የአገር በቀል ዕውቀትን መሻታቸው፣ እንዲሁም ምሁራን ለአገራቸው በተሻለ ሁኔታ ማበርከት አለባቸው ያሉት ትክክል ቢሆንም ኢትዮያዊያን ምሁራንን እርሳቸው ባነሱበት አግባብ እና ማንካሰስ መግለጽ በሞራልም ሆነ በተጨባጭ እውነቶች ቢፈተሸ ሚዛን አይደፋም፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ምሁራንን መውቀስ የማይቻልባቸው ቢያንስ አራት ምክንቶች አሉ፡፡
ምክንያት አንድ፡ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ጅማሮውን ያደረገው ሃገር በቀል ዕውቀትን በባዕድ አገራት ስርዓተ ትምህርት በመተካት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የባህላዊው (አገር በቀል) የትምህርት ስርዓት ከዘመናዊው የትምህርት ስርዓት ጋር ማዋደድ ባለመቻሉ ዘመናዊ ትምህርት ተጨባጭ የህዝብ ችግሮችን መፍታት አልቻለም፡፡ ዶር አብይ አገር በቀል ዕውቀት እንዳይስፋፋ የሆነው በዋናነት በምሁራኑ ግለሰባዊ ችግር ሳይሆን እንደመንግስት (እንደ አገር) የትምህርት ዘርፉ መዋቅራዊ ችግር እንደሆነ ለመገንዘብ አልቻሉም ወይም አልፈለጉም፡፡ይህ ባይሆን ኖሮ በንግግራቸው ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት የአስረጅ ግድፈት ባልፈጸሙ ነበር፡፡
ምክንያት ሁለት፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን ያገኙት በራሳቸው ግላዊ ጥረት፣ በውጭ አገራት መንግስታት (ዪኒቨርሲቲዎች)የነጻ የትምህርት ዕድል ድጋፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነጻ የትምህርት ዕድሉ ግን በነቢብ ነጻ ቢባልም ነጻ አይደለም፡፡ የትምህርት ድጋፉን የሚያደረጉት አገራት (አካላት) ይህን የማድረጋቸውን ትርፍ እና ኪሳራ በደንብ አስልተው ነው፡፡ አገራቱ የትምህርት ዕድሉን የሚሰለጥት አንድም ርዕዮተ ዓለማዊ ፍላጎቶቻቸውን አልያም በከፍተኛ ደረጃ የተማረ የሰው ሃይል ክፍተታቸውን ለመሙላት በማሰብ ነው፡፡ በመሆኑም የሰለጠኑበት ትምህርት በአገር በቀል ዕውቀት አይደለም። ኢትዮያዊያን ምሁራን ተጨባጭ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ቢፈልጉ እንኳ በተገለጹት አግባቦች ይገደባሉ፡፡ አንድም ርዕዮተ ዓለማዊ ፍላጎቶቻቸውን አልያም በከፍተኛ ደረጃ የተማረ የሰው ሃይል ክፍተታቸውን ለመሙላት በማሰብ ነው፡፡ ኢትዮያዊያን ምሁራን አገራዊ ተጨባጭ ችግሮችን ለመፍታት ቢፈልጉ እንካ በተገለጹት ሁለቱ አግባቦች ይገደባሉ፡፡
ምክንያት ሶስት፡ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግስታት (የፖለቲካ ስርዓቶች) ለዕውቀት አዎንታዊ አመለካከት ያልነበራቸው መሆኑ ምሁራን ለአገራቸው እና ለህዝባቸው መስጠት የሚችሉትን (የሚፈልጉትን) ያህል እንዳያበረክቱ ያደረገ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ አገሪቱን ያስተዳደሩ ስርዓተ መንግስታት ስለዕውቀት ሃይልነት ቢደሰኩሩም ትምህርት/ዕውቀት የሚያመጣውን ለውጥ ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ዶር አብይ በንግግራቸው በምሁራኑ ላይ የለጠፉት ችግር የተጠራቀመ የስርዓተ መንግስታት ችግሮች (የእርሳቸው መንግስት የነበረው ኢህአዴግን ጨምሮ) መሆናቸውን መገንዘብ አልቻሉም ወይም አልፈለጉም፡፡
ምክንያት አራት፡ ምሁራኖቻችን በሙያቸው ለህዝብ ማበርከት ያልቻሉበት ሌላው ምክንያት ህሊናዊ ጉዳይ ነው፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአንድ ንግግራቸው እንዳወሱት በአገራቸው ከፖለቲከኛው ይልቅ ጋዜጠኛ፣ ምሁራን ወይም አክቲቪስቱ ራዕዩን ለማስፈጸም የተሻለ ዕድል አለው፡፡ በምዕራቡ አለም እንኳን ምሁራን ይቅርና ማንኛውም ዜጋ ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችለው ጠንካራ ተቋማዊ፣ ህገ መንግስታዊ፣ ህጋዊ እና ኢኮኖሚያዊ መደላድል አለ፤ በመሆኑም ምሁራን ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያውሉት በሙያቸው ለህዝብ የሚጠቅም ስራ በመስራት ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የህዝብ ችግርን ለመፍታት እና ፍትህ ለማምጣት የሚያስችል ተቋማዊ፣ ህጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ ስርዓት ባለመኖሩ የደሃው ህዝብ ጠበቆች ምሁራን አንዲሆኑ የሞራል እና የህሊና ግዴታ አለባቸው፡፡በእኔ እምነት አብዛኛው የኢትዮጵያ ምሁራን ወደ ፖለቲካው የሚገቡት ስልጣን እና ገንዘብን ሽተው ሳይሆን ይህን ህሊናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ተገደው ነው፡፡ ኢትዮጵዊያን ምሁራን ይህን ግዴታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ትግል ባለ ተራ የፖለቲካ መሪዎቻችን ሲያሳድዷቸው፣ ሲያስሯቸው፣ ሲሳለቁባቸው ኖረዋል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በብዙ ህዝባዊ እና/ወይም የፓርላማ ንግግሮቻቸው ወቅት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ እና የቅንጅቱ አቶ ተመስገን ላይ ሲሳለቁ አስታውሳለሁ፡፡ ባለ ተራው ባለስልጣን ዶር አብይም ተራው ደርሷቸው በምሁራን እና ምሁራዊ እሴቶቻቸው (virtues of intellect) ላይ ተሳልቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የፖለቲካ ስርዓቱ የወለዳቸውን የተጠራቀሙ ችግሮች ለመሙላት የሚያደርጉትን የፖለቲካ ትግል ባንካሰሰ ሁኔታ አንድ ቀበሌ መርቶ የማያውቅ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ወዘተ.. ብለው መዘባበታቸው ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የህዝብ ስልጣን የያዘ የፖለቲካ መሪ ሁሉን አዋቂ ነው!
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዶክትሬት ዲግሪውን የሰራ ኢትዮጵያዊ ኢኮኖሚስት ሃብት አለመፍጠሩ ወይም ባለሃብት መሆን አለመቻሉ ያሳፍራቸዋል፤ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሰላማዊ ፖለቲካ በአገሪቱ እንዲሰፍን አለማድረጉም እንዲሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ፒ.ኤች.ዲ የህዝብን ችግር ቢፈታ ኖሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዶክትሬት ዲግሪያቸው ምን አንንደሰሩበት አላውቅም፡፡ ነገር ግን መልሱን ራሳቸው ዶር አብይ በቅርቡ የብሔራዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶችን በሚሊኒየም አዳራሽ ሰብስበው ከተናገሩት እናገኘዋለን፡፡ በመድረኩ እንደተናገሩት (ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት) ለአገራቸው ማበርከት የሚችሉት ብዙ ሃሳብ እያላቸው (ነገር ግን የፖለቲካ ስልጣን ስላልነበራቸው) ለህዝባቸው መስጠት የሚችሉትን ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ግን (የፖለቲካ ስልጣኑን ስለጨበጡ) ራዕያቸውን ለመተግበር ዕድል አግኝተዋል፡፡
ነገር ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንድ ሰው የፖለቲካ ስልጣን ሲያገኝ ትናንትን ይረሳል፡፡ ዶር አብይ የፖለቲካ ስልጣኑን ሲጨብጡ ትናንታቸውን ረሱት፤ እናም አንድ በፒኤች ዲግሪ ደረጃ የትምህርት ዝግጅት ያለው ኢትዮጵያዊ በተማረው ትምህርት እንደይሰራ የሚሆንበትን ምክንያት (ሁኔታዎች ስላልተመቻቹለት ሳይሆን) ከግለሰቡ ድክመት አንጻር ነው ብለው በአደባባይ ተናገሩ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሰላም እና ግጭት አፈታት መስክ ያጠናቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኖቤል ሎሬት ያደረጋቸው ፒ ኤች ዲ ዲግሪያቸው ይሆን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እኔ የማውቀው በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የህዝብ ስልጣን የጨበጠ ፖለቲከኛ ሁሉን አዋቂ መሆኑን ነው፡፡ በአገሬ ፖለቲከኛ አይሳሳትም፤ ቢሳሳትም ምን ሊገደው? ዶር አብይ በኢትዮጵዊያን ምሁራን ላይ እንዲያ የተሳለቁት የፖለቲካ ስልጣን ስለጨበጡ ነው፡፡

Leave a reply to አሸናፊ ምላሽ ይቅር