ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

‘አዲስ አበባ የማን ናት?’ የሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያዊያን በማድረግ ይፈታል!

ማስታወሻ:- ይህ መጣጥፍ መጋቢት 4 ቀን 2011ዓ.ም (March 13 2019) ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ለአንባቢያን ደርሷል። መጣጥፉ የሚያጠይቃቸው ጉዳዮች ዛሬም ያልተፈቱ ጉዳዮች ናቸው። በመሆኑም በዚህ መጣጥፍ የይዘትም ሆነ የጊዜ ጠቋሚ የቅርጽ ማስተካከያ አልተደረገም። አንባቢ ይህን ይገነዘብ ዘንድ በአክብሮት ለማሳሰብ እወዳለሁ። ጽሑፉን ከመጀመሪያው ህትመት ማንበብ ለምትሹ በሚከተለው ሊንክ ማግኘት ትችላላችሁ። ሰናይ ንባብ https://www.ethiopianreporter.com/article/15054


ሀብታሙ ግርማ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር


መግቢያ

በዚህ መጣጥፍ ሁለት ጉዳዮች ተነስተዋል፤ አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተላለፉት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር ተያይዞ የተነሳው ውዝግብ ነው።


አዲስ አበባ የማን ናት?

የሰሞኑ የሶሻል ሚዲያ ጉዳይ አዲስ አበባ የማን ናት? የሚለው ነው። የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ መነሳቱ ስህተት የለውም። ችግሩ ኢትዮጵያ የዜጎቿ የመሆኗ ነገር እጅግ ባጠራጠረበት ዘመን አዲስ አበባ የማን ናት? ብሎ መጠየቁ የፌዝ ስለሚመስል ነው። ጥያቄው የፌዝ ነው ተብሎ ግን መልስ መስጠት አለመቻል ማብቂያ ለሌለው ሙግት እና/ወይም ጠብ ያጋልጣል። ይህ አይነት ሙግት ወይም ጠብ መንስኤም፣ ውጤትም (አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ)፣ ማለቂያም የለውም፤ ትርጉም አልባ ነው።
ከማህበራዊ ሚዲያዎች ትዝብቴ አዲስ አበባ የማን ናት? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡትን በሶስት ቡድን መክፈል ይቻላል።
የመጀመሪያው በአብዛኛው አዲስ አበቤ ሲሆን፣ ይህ ቡድን አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት ይላል።
ሁለተኛው ቡድን ከአዲስ አበባ ውጭ ያለ፣ በአመዛኙ የኦሮሞ ወገን ሲሆን አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የኦሮሞ ህዝብ ናት ይላል (በአዲስ አበባ የሚኖር የኦሮሞ ወገን አዲስ አበቤ ራሱን በብሔር የመግለጽ ዝንባሌ የለውም የሚል እምነት ስላለኝ ነው)።

ሶስተኛው ቡድን አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ናት የሚለው ነው። ይህ ቡድን ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ብዙሃኑ ሀቀኛ አይደለም፤ አልያም የመንጋ ውዝግብ ሰለባ ነው። ምክንያቱም አንድ ኢትዮጵያ ባለበት አንደበቱ የአጉል ብሔርተኛነት ጩኸት ያሰማል። በእውነቱ ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ጉዳዩ ስለማድረጉ እጠራጠራለሁ ።እንዲያውም አወናባጅ ይመስለኛል።
ከሶስቱ ቡድኖች በተለይ በኢትዮጵያ አንድነት ስም የሚነግደው ጎራ እጅግ አደገኛ ነው፤ ምክንያቱም በአገር ቀልድ የለምና። አባላቱ በአብዛኛው የሚፈልጉትን መርጠው ማድመጥ የሚሹ፤ የሚዛናዊነት መለኪያቸው ሃሳብ ሳይሆን ግለሰባዊ ስሜታቸውን ከማስታገስ አንጻር እንጂ እንጂ ቆመንለታል ለሚሉት የኢትዮጵያ አንድነት ከማጠናከር አንጻር አይደለም። ይህ ሀይል ገሚሱ እሳት፤ ገሚሱ ቤንዘን አርከፍካፊ፣ ከፊሉ ደግሞ አራጋቢ ሆኖ አገር እየለበለበ፣ ነገር ግን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚለፍፍ ጸረ-ኢትዮጵያ ነው። እሳት ቤንዚን አነፍናፊ ነው፤ ቤንዚንም እሳት አነፍናፊ ነው። ውጤቱ ቃጠሎ ነው፤ የቃጠሎው ወላፈን እንደወረደ የሚፈጀው ደሃውን ህዝብ ነው። በእሳት እየተለበለበ እየረገፈ ያለው የኢትዮጵያ ምሰሶና ማገር ነው። ይህ የዘመናችን የኢትዮጵያ አሳዛኝ እውነት ነው።
ከኢትዮጵያ መፍረስ አንድም የሚጠቀም የለም። አገር ሲፈርስ የእያንዳንዳችን እጣ ፈንታ አንድም ከኢትዮጰያ ጋር አብሮ መፍረስ፣ አልያም ስደት ነው። ከሁለቱ መጥፎዎች የኋለኛው የከፋ ይመስለኛል። አገር የሌለው በሄደበት ከሰው በታች መሆኑን ለመረዳት ከአገር ወጥቶ መኖር አይጠበቅም።
በእኔ ግንዛቤ አዲስ አበባ የማን ናት? የሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያን የኢትዮጵያዊያን በማድረግ ይፈታል።


የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች የውዝግብ ጉዳይን በተመለከተ…….

የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቤቶች የውዝግብ ጉዳይን በተመለከተ መልስ ከመስጠት ይልቅ ሁለት ተዛማጅ ጥያቄዎች መጠየቅ መርጫለሁ።
ጥያቄ አንድ፦ ከአዲስ አበባ ወሰን 25 ኪሜ ገደማ ተገብቶ የአዲስ አበባ ቤት ማስፋፊያ ሲሰራ የድንበር ጉዳይን የወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጥያቄ አንስቶ ነበር? የወቅቱ የአዲስ አበባ አስተዳደርስ ይህን ጉዳይ ለምን ዘነጋው?
ጥያቄ ሁለት፦ የተነሳው ውዝግብ የብሔር ጉዳይ ነው ወይስ የአስተዳደራዊ? ከዚህ አንጻር የቤት እጣ ከደረሳቸው 51,000 ሰዎች መካከል በብሔር መጠሪያቸው የኦሮሞ ተወላጆች የሆኑ እንዳሉ ይታመናል፤ ታዲያ ኦሮሞ በመሆናቸው ተለይተው በቤቶቹ የመኖር ዋስትና አግኝተዋል? ከሌላ ብሔር ተወላጆች የቤት እድለኞች ደግሞ በቤቶቹ እንዳይኖሩ ተከልክለዋል?

እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳቴ ችግሩን ለማቃለል ሳይሆን ከስሜት እና አጉል ብሔርተኝነት ወጥተን ጉዳዩን እንድንመረምር ለማሳሰብ ነው። ይህም ከውዝግቡ የሚያተርፉ አካላት የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ ወይም ተጠቂ እንዳንሆን ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ።
ጥያቄዎቹን ማንሳቴ ከምንም በላይ በዶ/ር አብይ የሚመራውን የለውጥ አመራር ባልፈጠረው ችግር ከመወንጀል እንድንታቀብ፣ በመሆኑም የለውጥ ሀይሉ ተከፋፍሎ እንዳይዳከም፣ ተስፋ ያደረግነው ሁሉ እንዳይጨልም በአስተውሎት መጓዝ እንዳለብን ለማስታወስ ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading