
1. መግቢያ
በእኔ አረዳድ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ትውውቁን ካደረገበት ከ1950 ዎቹ ጀምሮ ያለውን ጊዜ በግርድፉ በሶስት ዘመናት ማዕቀፍ መክፈል ይቻላል፤ የጊዜ ማዕቀፉ በየዘመኑ የነበሩ በየትምህርት ቤቱ ብልጫ ያመጡ ወጣት ተማሪዎች በየስርዓተ መንግስታቱ ይቀርብላቸው በነበረው ማበረታቻና የስራና ህይወታቸውን ብሎም ቤተሰብ እና አገራቸውን በሚቀይር መልኩ የእውቀት፣ ስልጠና፣ የሥራ ዕድል እና ገንዘብ (ሐብት) የማፍራት ዕድል የመኖሮ አለመኖር ልኬት ነው
በዚሁ አግባብ ዘመናቱን በሶስት ማዕቀፍ ብንከፍለው፣ የመጀመሪያው የዘመን እርከን ከ1950 ዎቹ እስከ 1967 ዓ.ም ያለው ነው
ሁለተኛው ደግሞ ከ 1970 ዎቹ እስከ 1980 ዎቹ መጀመሪያ ያለው ነው
ሶስተኛው ከ1980 ዎቹ አጋማሽ አሰከ ዛሬ ያለው ነው

2. አጭር ሐተታ
በመጀመሪያዎቹ ሁለት የዘመን ማዕቀፍ ከፍ ያለ የዕውቀት ባለቤት የነበሩ ተማሪዎች መንግስታዊ በሆነ መዋቅር (አደረጃጀት) ተማሪዎቹን ወደከፍተኛ የስራ ዕድል የሚያደርሷቸው ከፍ ያለ የትምህርትና ስልጠና ዕድል ይመቻች ነበር፤ በዚህም ከፍተኛ ትምህርት ብልጫ ያላቸው ተማሪዎች ልፋታቸውና ያላቸው አቅም ባክኖ እኖዳይቀር፣ በዚህም ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን እንዲሁም አገራቸውን በዕወቀትና በገንዘብ የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ያስቻላቸውን ጥሪት የዘመኑ መንግስታት ጉዳይ ብለው ሰርተውበታል፤ በዚህም ብዙ ውጤት እንደተገኘ የሚካድ አይመስለኝም፤ እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባ ነገር ቢኖሮ በየዘመናቱ በራሳቸው ተጣጥረው ለውጤት የበቁ ጎበዝ ተማሪዎች እንደነበሩም ጭምር ነው
በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዘመናት ደረጃው ቢለያይም በአገራችን በርካታ የተማረ የሰው ሐይል ባለመኖሩ ጎበዝ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀላሉ ጥሩ ተከፋይ ሰራተኛ ይሆኑ እንደነበር ሳንዘነጋ፣ አለማቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው በትልልቅ አለማቀፍ ተቋማት በከፍተኛ የስልጣን እና የደመወዝ (ገቢ) እርከን እንዲሰሩ ለመሆኑ መንግስታዊ ድጋፉ ቀላል አልነበረም
የሁለቱ ዘመን ማዕቀፍ ሌላኛው ገጽታ ደረጃው ቢለያይም አንድ ተማሪ በራሱ ጥረት ከተለያዩ አለማቀፍ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር የሚገናኝበት የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ግለሰባዊ ጥረቱ ብዙ ጉድቶች ነበሩበት፤ ስለሆነም ይህን ጉድለት በመንግስታዊ ተቋማት ለመሙላት የተደረገው ጥረት ተገቢም፣ አስፈላጊም ነበር
በሶስተኛው የዘመን ማዕቀፍ ከላይ የተመለከተው መንግስታዊ ድጋፍ እምብዛም የነበረበት አልነበረም፣ ነገር ግን ተማሪዎች በራሳቸው ጥረት በከፍተኛ የዕውቀትና የስራ (የደመወዝ) እርከን ተቀጥረው እንዲሰሩ አስቻይ የሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮች( በተለይም ካለፉት ጥቂት አመታት ጀምሮ ተደራሽ እየሆነ የመጣው የግንኙነት ቴክኖሎጂ መኖሩ) የተፈጠሩበት የዘመን ማዕቀፍ ነው
ነገር ግን የመንግስት ተሳትፎ አለመኖሩ፣ በተጨማሪም እየተፈጠረ ያለውን የግንኙነት መረብ በሚገባን (በተፈለገው ደረጃ) ለመጠቀም ባለመቻሉ በዘመኑ የተነሱ ባለምጡቅ አእምሮ ባለቤት የሆኑ ወጣት ተማሪዎቻችን (እኔን ይጨምር ይሆን? 😆🤣) ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸው ፣ ማህበረሰባቸው እንዲሁም አገራቸውን በዕውቀት፣ በገንዘብ፣ ከፍ ሲል በአለማቀፍ መድረኮች በሚኖራቸው ተሳትፎ አገራችን ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ይኖራት ይገባ የነበረ ተጽዕኖ ባክኖ ቀርቷል።
ይህ ጉድለት ቢቀረፍ ኖሮ ሌላው ቀርቶ እንደ አገር ከፍተኛ ማነቆ የሆነብን የውጭ ምንዛሪን ድርቀትን በከፍተኛ ሁኔታ ያረሰርስልን ነበር፤ ከዚህ አኳያ ባለ ምጡቅ አእምሮ ተማሪዎቻቸው ላይ የሰሩ አገራት፣ ለአብነት ዚምባቡዌ፣ ናይጀሪያና ግብጽ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎበዝ ተማሪዎቻቸው በተለያዩ አገራት በሚገኙ ተቋማት ኦንዲሁም አለማቀፍ ተቋማጥ ተቀጥረው በመስራታቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላር በየአመቱ ወደአገራቸው ይልካሉ

3. የመፍትሔ ሐሳብ
ይህ ጉዳይ የሚኮረኩረኝን ያህል ለማለት (ለመጻፍ) አልፈለኩም፤ አንባቢ እንዳይሰለች ስለፈለኩ
ስለሆነም አሁን ያለፈ አልፏልና ብዙ መቆጨት (የሐረር ሰው እንደሚለው ‘ሂራር መጥራት’ ) አያስፈልግም፤ ቀጥታ ወደ መፍትሔው!
በመሠረቱ ለመፍትሔው ሁላችንም የሐሳብ መዋጮ ማድረግ አለብን
ከጽሑፌ ጭብጥ አንጻር በቀጥታ ባይገናኝም ተቀራራቢ የሆነ አንድ የማውቀው አስተዋጽኦ አለ፤ ይህም በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የረጅም ጊዜ የስራ ባልደረባዬ የሆነው ሙክታር ዑስማን (ሙክታሮቪች) በራሱ ጥረት ያሳተመው ‘ሥራ አዳኝ’ የሚል የከፍተኛ ትምሀርት ተቋማት በሥራ ገበያው (Job market) ላይ ውጤታማ ተሳትፎና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሏቸው እሴቶችን የሚተነትን መጽሐፍ ነው
ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ
ነገር ግን ከጽሑፌ ጭብጥ አንጻር ዛሬ እኔ አንድ ሐሳብ ይዤ መጥቻለሁ፦
ከባለብሩህ አእምሮ ተማሪዎቻችን ተገቢውን ጥቅም እንድናገኝ መንግስታዊ ድጋፍ ቁልፍ ቢሆንም በዋናነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ማስተማሩ የረጅም ልምዱ ያለን (እኔን ጨምሮ) የጎበዝ ተማሪዎችንን አቅም በማልማት ተማሪዎቹ ከራሳቸው አልፎ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እንዱሁም አገራችን የምትኮራባቸው ሐብታሞች (የዕውቀት፣ የስልጠና እና የገንዘብ ሀብታሞች) ልንሰራባቸው የምንችላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ይኖራሉ፤ እኔም አንድ መሬት ላይ መውረድ የሚችል የፕሮጀክት ሐሳብ ይዤ መጥቻለሁ
በመሆኑም ይህ ጉዳይ የሚቆረቁራቸው ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት ሊያገኙኝና በጋራ መክረን በጋራ መስራት እንችላለን
4. እንደመውጫ
የባለ ብሩህ አእምሮ ተማሪዎቻችንን ዕውቀትና ልፋት የሚመጥን ኢንቨስትመንት በማድረግ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ከራሳቸው አልፎ ቤተሰብና አገርን በሚጠቅም አግባብ ወደ ሐብት (ገንዘብ) መቀየር ይቻላል፤ ይህን እውን ለማድረግ አብረን እንስራ!
አስተያየት ያስቀምጡ