ሂሩት በቀለ፣ ነፍስሽ በሰላም ትረፍ

የድምጻዊት(ዘማሪት) ሂሩት በቀለ ህልፈት ስሰማ በጣም አዝኛለሁ፤ እርሷ የዘመናዊ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ጅማሮ መሰረት ከሆኑ ብርቅዬ እንስት ጥበበኞች አንዷ ናት፤ የህዝብ ልጅ ብትሆንም ህይወቷ ጸጥ ያለና የተረጋጋ፣ የመጨረሻ እድሜ ዘመኗን በመንፈሳዊ ህይወት ያሳለፈች፤ በግላዊ ህይወቷ የ7 ልጆች እናት፤ የ10 ልጆች አያት እንዲሁም የ 7 ልጆች ቅድመ አያት ለመሆን የቻለች እድለኛ ናት፤ ይህ የቤተሰባዊ ህይወቷ ስኬት ብዙ ሴት ድምጻዊያን(ሙዚቀኞች) ያልታደሉት እንደሆነ ልብ ይሏል

የህይወቷን ጉዞ በአጭሩ መግለጽ ካስፈለገ፣ ሂሩት የአለማዊውንም ሆነ መንፈሳዊውን አለም ሚዛን ጠብቃ የኖረች እንቁ ኢትዮጵያዊት ነበረች
ሞት የሰው ልጅ ሁሉ እዳ መሆኑን ሂሩት ‘ህይወት እንደ ሸክላ’ በተሰኘው አይረሴ ዘፈኗ እንዲህ ታስታውሰናለች፦
<< እድሜው ሲገሰግስ ከንቱ ሰው ዘንግቶ
ነገ አልፎልኝ ይላል ማለፉን እረስቶ
አይቀር መንፈራገጥ ያ ሆድ እስኪሞላ
ወድቃ እስክትሰበር ህይወት እንደ ሸክላ >>
እኔም እላለሁ፣ ሞት የሁላችንም እዳ ቢሆንም ሰርቶ ማለፍ ህያውነት ነው፤ ሂሩት በስራዎቿ ትውልዶችን መሻገር ችላለች፣ ወደፊትም በትውልዶች ስትታወስ ትኖራለች

ድምጻዊ ሂሩት በቀለ በአንድ ቃለምልልሷ ወደ መንፈሳዊ ህይወት የሄደችበትን ሁኔታ “አለምን ሮጬ አመለጥኳት” በማለት ገልጻ ነበር፤ የምህረት አምላክ ነብሷን ተቀብሎ ከደጋጎቹ ወገን ያሳርፍ፤ ለቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ጓደኞቿ መጽናናቱን ይስጥ!

አስተያየት ያስቀምጡ