ማስታወሻ፦ ይህ መጣጥፍ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም የተጻፈ ነው፤ በድጋሚ የለጠፍሁት የያዘው ሃሳብ ዛሬም ጉዳይ ሆኖ ያለ በመሆኑ ነው።
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ በተለያየ ዘመን የተፈራረቁ አገዛዞች ሥልጣን የጨበጡት በሃይል እንደሆነ ሀቅ ነው። እናም የስልጣን በትር በእጃቸው ያስገቡበትን ቀን የድል ቀን አድርገው ደንግገዋል። ግርማዊነታቸው ጥቅምት 23 ቀን፣ ደርግ መስከረም 2 ቀን፣ ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀንን ብሔራዊ በዓል ብለው አውጀዋል።
በዘመን ዥረት አንዱ ሥርዓት በሌላው እየተተካ ቢመጣም ቴዲ አፍሮ እንደተቀኘው ለህዝቡ አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ ከቶም አልመጣለትም ነበር።
የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ የተሻለ ነገን የተመኘ ሁሉ ቀናቱ የሆነ የምስራች ይዘው ይመጡ ዘንድ እየተመኘ ሲዘክር ቆይቷል፥ በጊዜ ሂደት ግን አገዛዞቹ ከቀደመው ብሰው ሲገኙ ቀናቱን ከማወደስ ይልቅ ሲረግም ኖሯል።
እርግማኑም ‘ሰምሮለት’ የቀደመው የድል ቀን ተሽሮ በሌላ የድል ቀን ሲተካ ኖሯል።
በእኔ ምልከታ ግንቦት 20 ን ስናከብር አንድ በሰላማዊ መንገድ ለመስተካከል ያልቻለ ሥርዓት በሚገባው(ላልቶ ይነበብ) መንገድ የተቀየረበት ቀን እንጂ በራሱ ግብ ሆኖ መታየት አልነበረበትም።
ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆን ዘንድ የብስራት ቀን ተስፋ ነበር እንጂ ዲሞክራሲና ፍትህ ያሰፈነ ለመሆኑ ምስክር ጊዜ፣ እማኙ ህዝብ ነው።
የግንቦት 20 አከባበር እንድምታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነበር። የኢህአዴግ ዲስኩር በዝቶ፣በጉራ ብቻ ተሞልቶ፤ ታገልኩለት ለሚለው ዓላማ ረገድ ራሱ ጠላት መሆኑ በጊዜ ሂደት ተረጋገጠ።
ኢህአዴጎች ለለውጥ የተሰዉ ውድ ጓዶቻቸው አጥንት ሳይወቅሳቸው እንዳሻቸው ሲፈነጩ ከርመው እነርሱም ከህዝብ ማዕበል ሳያመልጡ ይኸው የቀደምቶቻቸው እጣ ደርሷቸው ግንቦት 20 የጮቤ ቀን መሆኑ እንዳከተመ ጊዜ ምስክር ሆኖ፣ እኛም እማኝ ሆነናል።
የዶ/ር አብይ አስተዳደር በይፋ ባያውጅም ግንቦት 20 ን በመጋቢት 24 ለመተካቱ ብዙ አስረጅዎችን ማቅረብ ይቻላል።
መራራ ኑሮ እስከቀጠለ ድረስ ህዝቡ ለለውጥ መስዋዕት መሆኑ የህይወት እውነት ነው። ህዝብ ሌላ የተስፋ ቀን፣ ሌላ የምስራች ቀን ሽቶ ሲባዝን የመኖሩ ጉዳይም ሌላ የህይወት እውነት ሆኖ ይቀጥላል።
አሁንም የለውጥ ሀይል ነን ብለው ለህዝብ ተስፋ የሰጡና ሥልጣን የተቆናጠጡት ለተነሱለት ዓላማ ካልታመኑ፣ ከቀደመው መማር ካልቻሉ፣ ለውጥ ያወጁበት መጋቢት 24 ቀን የተስፋ ሳይሆን የመርገምት ቀን ተብሎ በህዝብ መፈረጁ አይቀሬ ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ! አሜን!!!

አስተያየት ያስቀምጡ