ሀብታሙ ግርማ
የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም
ጅግጅጋ፣ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚጀምሩበት ወቅት ባለፈው ሳምንት ይፋ ሆኗል። አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጠብ እንደማንሳት ቀላል ነገር የለምና የምረጡኝ ቅስቀሳው ወቅት ደንበኛ የጠብ ወቅት ሊሆን የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው።
ነገሩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ማህበረሰባችን የአመራር ቀውስ በገጠመው በዚህ ወቅት የምርጫ ቅስቀሳ ሊከወን መሆኑ ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ጠብን የሚያሟሙቅ እንጂ የሚያበርድ መሪ ወይም አስታራቂ ሽማግሌ ማግኘት ከባድ ነውና መራጩ ህዝብ የጠብ መንገዶችን መዝጋት ይገባዋል። ይህም ሲባል የምርጫ ቅስቀሳ መድረኮችን ከመደገፍ አንጻር እንጂ ከመቃወም አንጻር ማየት የለበትም ለማለት ነው።
ለምሳሌ ኢዜማ በሚጠራው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የአብን ወይም የኦነግ ደጋፊ በሰልፉ መገኘቱ ለምን ይሆናል?
ኦነግ በሚጠራው የአደባባይ ምረጡኝ ቅስቀሳ የብልጽግና ፖርቲ ደጋፊ ምን ይሰራል?
ስለዚህ ለሚቀጥሉት አራት ወራት የወጣው ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለስድብ ወይም ቧልት፣ ከፍ ሲልም ለብሽሽቅ እና ጠብ አጫሪነት ሳይሆን ለስልጡን ዲሞክራሲያዊነት መጠቀም ያሻል። የምረጡኝ ዘመቻ ወቅቱን የምንደግፈውን ፓርቲ ፕሮግራሞችን ለመገምገም እንጂ ለብሽሽቅ መጠቀም የለብንም።

አስተያየት ያስቀምጡ