ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

የሙስሊም ወገኖቻችን ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው!

ሀብታሙ ግርማ (በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር)
ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም
ጅግጅጋ፣ ኢትዮጵያ


መግቢያ



ጉዳዩን ፖለቲካዊ ካላደረግነው በቀር ለሞጣ ሙሰሊሞች መቆም ያለበት አማራው ወይም ሙስሊሙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ብቻ አይደለም፤ ሰው የሆነ ሁሉ በሰብዓዊነት ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። ከዚህ አኳያ በግሌ ማድረግ ያለብኝን የሰብዓዊነት የሞራል ግዴታ ለመወጣት ለተጎዱት ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ዛሬ የአቅሜን ለግሻለሁ።

የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የሞጣ ሙስሊሞችን ጉዳት ከሰብዓዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ መልክ ለመስጠት የመሞከር የተሳሳተ አዝማሚያ በምክንያት ለመሞገት ነው። በዚያውም የሙስሊሙ ማህበር ጥያቄዎችን ፍትሃዊነት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ሁነቶች አንጻር መገምገም ነው።

የተንሸዋረረው የታሪክ ትንተና እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስንክሳሮች


ካለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ወዲህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰላለፎች የትግል መሰረት የማርክሲስታዊ የታሪክ ትንተና መሣሪያ የሆነው የጨቋኝ- ተጨቋኝ ክፍፍል (exploiter-exploited dictum) ነው።

በ1960ዎቹ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች አጀንዳ መሰረት ይህ ማርክሲስታዊ የቅራኔ የታሪክ ሆኖ የቅራኔው መሰረት ላይ ሁለት አተያይ ነበር። አንደኛው የፖለቲካ ቡድን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚተነትነው በመደባዊ ቅራኔ ሲሆን፣ ሁለተኛው የፖለቲካ ሀይል የኢትዮጵያ ታሪክ ከብሔር ቅራኔ አንጻር ነበር። የኋለኛው ቡድን ዛሬም በተጽዕኖው የኢትዮጵያን ፖለቲካ እያሾረው ይገኛል። ብሔር ተኮር የጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት ዋናው የፖለቲካ ስንቅ ሆኖ ዛሬም እየዘወረን አለ።

ነገር ግን በእኔ ዕውቀት የትኛውም አይነት ቅራኔን መሰረት ያደረገ የታሪክ ትንተና የፖለቲካ ጥሬ ዕቃ ማድረጉና ፖለቲካን ለመከወን የሚደረግ ጥረት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ጥቅሙ ታሪካዊ ቅራኔን በማለዘብ ለዘላቂ የማህበረሰብ አንድነት እና የተሳካ ብሔረ መንግስት ግንባታ አስተዋጽኦ አለው። አሉታዊ ገጽታው የፖለቲካ ሥርዓቱ ጊዜው የሚጠይቀውን የህዝብ ችግር ለመፍቻ ከመሆን ይልቅ ተጨማሪ ትውልድ ተሻጋሪ ቅራኔዎችን ለመፍጠር በር ከፋች ሊሆን የሚችልበት እድል ያሰፋዋል።
ቅራኔን መሰረቱ ባደረገ የፖለቲካ ስሪት ፖለቲካ ቂም መወጫ መሳሪያ ስላለመሆኑ ዋስትና ሊኖር አይችልም፡፡ ይህም የቀድሞው ጨቋኝ የዛሬ ተጨቋኝ፤ የዛሬ ተጨቋኝ ደግሞ በተራው የነገ ጨቋኝ የመሆኑ ጉዳይ አይቀሬ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካው ስርዓት በጭቆና አዙሪት ተመልቶ ፖለቲካ የችግር መፍቻ ቁልፍ ሳይሆን የችግር ምንጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያን የገጠማት የፖለቲካ ቀውስ መሰረታዊ መነሻውም በቅራኔ ታሪክ የተገነባው የፖለቲካ ስርዓት ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

የሆነው ሆኖ የቅራኔ ታሪክን መሰረቱ ያደረገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተንሸዋረረ መሆኑ ሳያንስ የታሪካዊ ቅራኔውን በትክክለኛ አስረጅነት አለመግለጹ ሌላው ችግር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የብሔር ቅራኔን መሰረቱ ያደረገው የፖለቲካዊ ስርዓት የኢትዮጵያን ህዝብ የዘመናት ችግር ከመግለጽ አንጻር ቢያንስ ምሉዕነት የጎደለው ነው፡፡

የዚህ ችግር ነጸብራቅ ከሆኑ አንዱ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለዓመታት ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች የፖለቲካ ስርዓቱ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄውን የመጠርጠር አዝማሚያ የነበረው መሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ታሪካዊ ዳራ


ብሔር ተኮር የጭቆና የታሪክ ትርክት ካልመለሳቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጉዳይ ነው።የፖለቲካን አጀንዳ ከታሪክ ቅራኔ አንጻር እንኳ ቢቃኝ የኢትዮጵያ የታሪክ ትንተና መሆን የነበረበት ብሔራዊ ቅራኔ ሳይሆን በመደባዊ ቅራኔ ነበር።

የረጅም ዘመን የኢትዮጵያ የሥነ መንግስት ታሪክ የፊውዳል ሥርዓተ ማህበር ነው። የፊውዳል ሥርዓተ መንግስት አሻራዎች አንዱ የሚና እና የተጠቃሚነት ክፍፍል ማህበረሰባዊ መሰረትን ያማከለ ነበር። ማህበረሰባዊ መሰረቱ ሀይማኖት፣ ጾታ፣ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ደረጃ (የባላባት ማህበረሰብ፣ የጭሰኛ ማህበረሰብ፣ የቀጥቃጭ ማህበረሰብ፣ የአዝማሪ ማህበረሰብ ወዘተ….) ሊሆን ይችላል። በዚህም የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ወዘተ ሚና፣ ደረጃ ወይም ተጠቃሚነት ማህበረሰባዊ ማንነትን መሰረት ያደረገ ነበር።

በሀይማኖት ደረጃ የማህበረሰቦችን ክፍፍል ካየን ሙስለሙ የማህበረሰብ ክፍል ኢኮኖሚያዊ ሚና ንግድ ነበር። የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ሚና ኢና ተጠቃሚነት ደግሞ በፖለቲካ፣ በቢሮክራሲ፣ በትምህርት፣ በግብርናው እና በመሬት ባለቤትነት ዘርፎች ላይ ነበር። በመሆኑም የሙስሊሙ ማህበረሰብ በፖለቲካ እና በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ሚናው ከሞላ ጎደል ምንም ነበር። ይህን ታሪካዊ ሀቅ መካድ አይቻልም።

ዛሬ የፖለቲካና የህዝብ አስተዳደር አካታች ይሁን ተብሎ ጥሩ ሂደት ላይ እንገኛለን፤ ይህ የአካታችነት መርህ አንደኛው አስረጅ በታሪክ አጋጣሚ በፖለቲካና በመንግስት ሚናቸው አናሳ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች (ለምሳሌ ሴቶች፣ ሙስሊም ማህበረሰብ አካላት፣ ወዘተ..) ወደ ቢሮክራሲው እና የመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካላት ማምጣት ነው፡፡ በመንግስት ቢሮክራሲ እና የፖለቲካ ሚና መጨመር አለበት የሚለው የሙስሊም ወንድሞቻችን ጥያቄ ፍትሃዊነት ከዚህ ነባራዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር ብንመለከተው ሚዛናዊ ፍርድ እንዲኖረን ያደርጋል።

ከዚህ አንጻር ሙስሊም ወገኖች ተወካዮች የመንግስት የአስተዳደራዊ ውክልና ሲጠይቁ የግብጽ እና የሌሎች የአረብ አገራት ተላላኪ አድርጎ መውሰድ ፍረጃ አንጂ እውነትን መሰረት ያደረገ አይደለም። በመሠረቱ በአገር ላይ የሚኖር ስጋት የለም ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን ይህ የመንግስት የደህንነት መዋቅር ሥራ ነውና ለሚመለከተው አካል ብንተወው ጥሩ ይመስለኛል።


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading