ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

የሁለት ወረርሽኞች ወግ፡ የኮሮና ወረርሽኝ እና ስፓኒሽ ፍሉ (የሕዳር በሽታ)

THE TALE OF TWO DISEASES : Corona Virus Vs Spanish Flu


ሀብታሙ ግርማ ደምሴ

እንደ መግቢያ

ሰሞነኛ የአለማችን መነጋገሪያ የኮሮና ወረርሽኝ ነው፡፡ በሽታው ከአገረ ቻይና መነሻውን አድርጎ በፍጥነት ወደ ሌሎች አገራት እየተዛመተ ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የበሽታው ስጋት ደረጃ የአለማቀፍ ወረርሽ መሆኑን ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም አውጇል፡፡
በ ‘የሁለት ወረርሽኞች ወግ ‘ መጣጥፌ በስፓኒሽ ፍሉ ወይም የህዳር በሽታ እና የኮሮና ወረርሽኞችን ዝምድና በመፈተሽ ከተሳካልኝ አንባቢን አንድ ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ እጎትታለሁ፤ የጽሁፌ ዓላማ በአንባቢ አእምሮ ውስጥ የዘመን ግጥምጥሞሽ ትዝብት አልያም ‘ታሪክ ራሱን ይደግማል‘ የሚለው ብሂል ለመጫር የሚደረግ (የሚሳካ አልያም የከንቱ) ሙከራ ነው፡፡

ማስታወሻ፦ ከመጠነኛ ማሻሻያ በቀር ይህ መጣጥፍ በህዳር 2008 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ለንባብ የበቃ ነው።

የኮሮና ወረርሽኝ እና ስፓኒሽ ፍሉ ዝምድና ይኖራቸው ይሆን?

በእኔ አተያይ ስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ) እና የኮሮና ወረርሽኞች በብዙ መልኩ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ የተመሳስሎሻቸው መገለጫዎች ከብዙ በጥቂቱ፡-
• የበሽታዎቹ አማጪ ተህዋስ ቫይረስ ነው፤
• ሁለቱም የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ ናቸው፤
• የበሽታው ምልክቶች እና በሽታው የሚተላለፍባቸው መንገዶች ተመሳሳይነት አላቸው
• ሌላው የወረርሽኞቹ ተዛምዶ የጊዜ(የዘመን) ነው፡፡
o ከዚህ አንጸር ሁለቱም በአለም የታዩት በጥር ወራት፣ በክፍለ ዘመኑ ሁለት አስርት አመታት መባቻ ነው፡፡
o ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚሉት አበው፣ የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተው የስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ ከተከሰተ መቶ ዓመታት (አንድ ክፍለ ዘመን) ሲደፍን መሆኑ ነው፡፡
o ወረርሽኞቹ የተከሰቱባቸው ወቅቶች የዓለም የፖለቲካ እና የደህንነት አውድና ስሪት ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ይህን ለማብራራት ያህል፡-
 የህዳር በሽታ የተከሰተው አለም በከፍተኛ የብሔርተኝነት ጡዘት የደረሰበት ነበር፤ የብሔርተኝነት ጡዘቱ ባመጣው ጣጣ የአለም ሃያላን አገራት የጦር መሳሪ እሽቅድምድም የገቡበት ነበር፤ ይህ የአለም ሃያላን እሰት እገባ በርትቶ በአለም ታሪክ የአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ዛሬም ሶስተኛው አለም ጦርነት አደጋ በአለም ያንዣበበበት ወቅት እንደሆነ እየኖርነው ጉዳይ ስለመሆኑ ማብራሪያ አያስፈልገውም፡፡

የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ አንባቢ ስለበሽታው ወቅታዊ መረጃ እንዲሁም ስለ ወቅቱ የአለም የፖለቲካ እና የደህንነት ትኩሳት መጠነኛ ግንዛቤ አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለሆነም የሁለቱን ወረርሽኞችን ተዛምዶ ከላይ ባስቀመጥኩት የተመሳስሎሽ ነጥቦች ያወዳድር ዘንድ ስለ ስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ) ወፍ በረር ታሪካዊ ቅኝት አደርጋለሁ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሃዛዊ መረጃዎች

የስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ) ታሪካዊ ዳራ

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሁለት አስርት ዓመታት ለመላው የዓለም ህዝብ የሰቆቃ ዓመታት ነበሩ፤ ምክንያቱ ደግሞ የወቅቱ ሃያላን መንግስታት በሁለት ጎራ ሆነው ጦርነት ውስጥ ገብተው ስለነበር ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ 1914 ዓ.ም እስከ 1918 ድረስ የዘለቀውና የ15 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ይህ ጦርነት በታሪክ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡ የጦርነቱ ማብቃት ሊታወጅ ጥቂት ሲቀረውና ዕልቂቱ ቆመ ሲባል ግን የዓለም ህዝብ ሌላ ፍዳ ማስተናገድ ግድ ሆነበት፤ በሰው ሰራሽ ችግሮች (በዋነኝነት በጦርነት) ተወጥሮ የቆየው መላው የአለም ህዝብ አሁን ደግሞ በእንፍሉዊንዛ በሽታ ከዳር እስከ ዳር ተጠቃ፡፡:
በተለምዶ የእሰፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ መነሻው ከወደ አሜሪካ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ በጥር ወር 1918 ዓ.ም በአንደኛው የአለም ጦርነት ማብቂያ ዋዜማ በጦርነቱ ለመካፈል የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አውሮፓ ለመጋዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ይያያዛል፡፡ በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የተቀሰቀሰው ወረርሻኙ በሶስት ቀናት ብቻ 45 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አጠቃ፤ ወታደሮቹ አትላንቲክን አቃርጠው አውሮፓን እንደረገጡ በሸታውም አውሮፓ ደረሰ፡፡

በካንሳስ በሚገኘው ፉንስተን የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በበሽታው የተጠቁ ወታደሮች በህክምና ላይ

የእንፍሉዌንዛ በሸታው በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በፈረንሳይ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ይሆናል በሚል ወረርሽኙ ለህዝብ ሳይገለጽ ተደብቆ ቆይታል፡፡ በሽታው ይፋ የሆነው እ.ኤ.አ በህዳር ወር 1918 ዓ.ም በስፔን በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ መታየቱን ተከትሎ ነበር፡፡ ስፔን በጦርነቱ ተካፋይ አልነበረችምና በአገሪቱ የጦርነት ጊዜ ሳንሱር አልነበረም፤ በመሆኑም የበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን በማግኘቱ ወረርኙ እስፓኒሽ እንፍሉዌንዛ (ስፓኒሽ ፍሉ) የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡

ስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ) መነሻ ምክንያት፣ ምልክቶች እና ስርጭቱ

የስፓኒሽ ፍሉ አማጪ ቫይረስ ባለመታወቁ መድሃትም ሆነ ማስታገሻ አልተገኘለትም፤ የአማጭው ቫይረስ የታወቀው እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም በእንግሊዛዊያን ሳይንቲስቶች ሲሆን፣ የበሽታው አማጪ ቫይረስ በሳይንሳዊው አጠራር H1N1 ተብሎ ይታወቃል፡፡ በዚህም በሽታው በተቀሰቀሰበት ወቅት በህክምና ስርጭቱን ለማቆም አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ በጥቂት ጊዜም ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከኤሺያ እስከ አፍሪካ፣ከአርክቲክ እስከ ፓስፊክ ደሴቶች ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተዛመተ፡፡

በሽታው እንዲዛመት የአለም የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ነበር፤ ይህም ወታደሮች ከአንዱ የአለም ክፍል ወደሌላው ለዘመቻ መንቀሳቀሳቸው ነበር፡፡ በዚህም አንድ ሶስተኛው የአለም ህዝብ በዚህ በሽታ እንደተያዘ ይነገራል፤ በበሽታው ከተያዙት ውስጥ ደግሞ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆት ለሞት ተዳርገዋል፡፡

የስፖኒሽ ፍሉ በሽታ ምልክቶች፡- ሳል፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ነስር፣ የጆሮና የአንጀት መድማት፣ ተቅማጥ፣ የአይን ማስለቀስ፣ ውጋት እንዲሁም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ የአእምሮ ህመም ያስከትላል፡፡ በዚህም በሽታው ኮሌራ ወይም ፈንጣጣ በሽታዎች ጋር ተተቀራራቢ ምልክቶችን ስለሚያሳይ ብዙ ያምታታ ነበር፡፡

የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክቶች

የበሽታው አስገራሚ ባህሪ አንድ ሰው በበሽታው በተጠቃ በአምስት ቀን ውስጥ ወይ ይሞታል አልያም ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ይፈወሳል፡፡ ይህም እንደ ግለሰቡ የበሽታ መከላከል አቅም ይወሰናል፤ ቫይረሱ የተፈጥሮ የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክም ሲሆን ጠንካራ የመከላከል አቅም ያለው ሰው ከአምስት ቀናት በላይ መቋቋም ስለሚያስችለው በስድስተኛው ቀን ፈውስ ያገኛል፡፡

የስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ከሞላ ጎደል በመላው ዓለም ተሰራጭቶ ነበር

ሲኖ ባይሎጂካ የተሰኛ የህክምና ጥናት ማዕከል ባደረገው ጥናት መሰረት በአሜሪካ እስከ 28 በመቶ የሚሆነው ህዝባ በበሽታው ተጠቅቶ ነበር፤ 675 ሺህ ገደማ የሚሆነው ህዝባ ደግሞ በበሽታው ሞታል፡፡ ወረርሽኙ በህንድ የከፋ ነበር፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 17 ሚሊዮን ህንዳዊያን በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በጃፓንም 23 ሚሊዮዮ ህዝቦችን ያጠቃው በሽታው 400 ሺህ ገደማ የሚሆኑትን ደግሞ ገድሏል፡፡ እንግሊዝ ሩብ ሚለዮን፣ ፈረንሳይ ደግሞ 400 ሺህ ዜጎቻቸውን በበሽታው አጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከጥር ወር 1918 ዓ.ም እስከ ታህሰስ 1920 ዓ.ም በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ የቆየው የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ፈጅቷል፤ የሟቾቹ ቁጥር እስከ 200 ሚሊዮን ይሆናል የሚሉ መረጃዎችም አሉ፡፡
የወረርሽኙን ጉዳት የከፋ ያደረገው አምራች ዜጎችን በከፍተኛ ሁኔታ ማጥቃቱ ነበር፡፡ በበሽታው ከሞቱት መካከል ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 34 ዓመት የሆኑ ወጣቶች አብዛኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ በመሆኑም በሽታው ካደረሰው ሰብዓዊ ውድመት ባለፈ ጥሎት ያለፈው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠባሳ የከፋ ነበር፡፡

ስፓኒሽ ፍሉ በአፍሪካ

ወረርሽኙ በአፍሪካ በሁለት ዙር ነበር የታየው፤ የመጀመሪያው በፈረንጆቹ በ1918 ዓ.ም የጸደይና የበጋ ወራት ሲሆን ሁለተኛውና የከፋ ጉዳት ያደረሰው ደግሞ በበልግ ወራት የታየው ነበር፡፡ በሽታው ለመጀመረያ ጊዜ በአፍሪካ የታየው በወቅቱ የእግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችው በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታዎን ሲሆን በአጭር ጊዜ ወደሌሎች የአፍሪካ አገራት ተስፋፋ፡፡
ሚስተር መሪ (Murray) የተባሉ አጥኚ Global Pandemic በተሰኘ ጥናታቸው እንዳሰፈሩት የበሽታው ስርጭት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ላይ ሰፊ ነበር፤ በክፍለ አህጉሩ የተከሰተው የሞት መጠን በመላው ዓለም በበሽታው ከተከሰተው ሞት ውስጥ የ29 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በተለይም በምዕራብና ደቡባዊ አፍሪካ ጥፋቱ የከፋ ነበር፤ በጋና እስከ መቶ ሺህ ዜጎች እንዳለቁ ይገመታል፤ በምስራቅ አፍሪካም ቀላል የማባል ቁጥር ላቸው ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በእንግሊዝ ሶማሊ ሰባት በመቶ የሚሆኑ ህዝቦች በበሽታው ሲሞቱ፣ በኢትዮጵያም ከአርባ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል ፡፡

ስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ በአፍሪካ ያኖረው ማህበራዊ እና የማህበረሰባዊ መስተጋብር አሻራ

ከሰብዓዊ ውድመቱ ባለፈ ወረርሺኙ በአፍሪካ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትላል፡፡ በጊዜው አጠራር ደቡብ ሮዴሺያ (የዛሬዋ ዚምባብዌ) አምራች የሰው ሀይል በበሽታው በመያዙ የወርቅ ማውጫ ማዕድናት እንዲዘጉ ሆኖ ነበር፤ በዚህም በማዕድን ዘረፉ ላይ የተንጠለጠለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ክፉኛ ተጎዳ፡፡ ወረርሽኙ በማላዊና በዛምቢያም ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ከፍ ያለ ነበር፡፡ በናይጀሪያም፣ በተለይ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በሽታው የከፋ ጥፋት በማድረሱ ተጠቅቶ ምርት በማሽቂልቆሉ ቀድሞ ለምግብነት የመይወውለው ካሳቫ ለምግብነት መዋል የጀመረው የወረርሽኙ መቀስቀስን ተከትሎ ነበር፤ በአነስተኛ ጉልበትና ብዙም ልፋት የማይጠይቀው ካሳቫ ተመራጭ ምግብ ስለነበር በጊዜው በስፋት መመረት ጀመረ፡፡

የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በአፍሪካ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አልነበረም፡፡ በሽታው ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ የኢኮኖሚ ደረጃን ሳይለይ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ቅኝ ገዢዎች በሽታው ከጥቁር ህዝቦች የመጣ እንደሆነ በማናፈስ የዘር መድልዖ ለድረግ ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ ችግር በተለይም በደቡብ አፍሪካ የጎላ ነበር፤ በዚህም ነጮችና ጥቁሮች ማንኛውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ላይ እንዳያደርጉ የሚደነግግ አዋጅ እንዲጸድቅ ተደረገ፡፡

በቦትስዋናም በሽታው በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ አድርጋል፡፡ በጋና የሆነው ደግሞ ትንሽ ለየት ያለ ነበር፤ በሽታው ተንሰራፍቶ በርካታ ሴቶች በመጠቃታቸው ከነባራዊው የጋናዊያን ባህልና ወግ ባፈነገጠ መልኩ ባሎች የሴቶች ድርሻ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው የቤት ውስጥ ስራዎች መስራት ግድ ሆነባቸው፡፡ በዚህም ወንዶች ወደ ማዕድ ቤት ገብተው በቆሎ መፍጨት፣ ምግብ ማብሰል የመሳሰሉትን ስራዎች ይከውኑ ጀመር፡፡

ስፓኒሽ ፍሉ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ በሽታው የታየው የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየበት ጥር 1910 ዓ.ም ከአስር ወራት በኋላ በህዳር ወር 1911 ዓ.ም ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብሎ በሽታው መግባቱ አይቀርም በሚል ለቅድመ ትንቃቄ ስራዎች ለመስራት የሚያስችል ስራ እምብዛም ነበር፡፡

የስፓኒሽ ፍሉ ተጠቂ ከሆኑት የአለም ህዝቦች መካከል ኢትዮጵያዊያን ይጠቀሳሉ

በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው በኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቆንሰላ ያደረገው ነገር ነበር፡፡ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻረድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ በ1990 ዓ.ም ባሳተሙት An Introduction to the Medical History of Ethiopia በሚለው የምርምር ስራቸው እንደጻፉት በሽታው በውል ያልታወቀ ነበርና ምናልባትም የፈንጣጣ በሽታ ይሆናል በሚል በወቅቱ በኢጣሊያ ቆንስላ ትብብር በሀምሌ ወር 1910 ዓ.ም አስር ሺህ ዶዝ የፈንጣጣ ክትባት ወደ ኢትጵያ እንዲገባ ተደርጎ ነበር ፡፡ የሆነው ሆኖ ከዘመናዊ የህክምና ጋር ለማይተዋወቀው የኢትዮጵያ ህዝብም ወረርሽኙ ታላቅ መቅሰፍት ነበር፡፡ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ በመላው አገሪቱ ከባድ ዕልቂት ማስከተል ጀመረ፡፡ በተለይም ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ መረበሽን ፈጥሮ ነበር፡፡
በበሽታው ከተጠቁ ታላላቅ የዘመኑ ሹመኞችና የቤተ መንግስት ሰዎች መካከል ራስ ተፈሪ መኮንን (ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ) እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አቴጌ መነን አስፋው ይገኙበታል፡፡ እንዲያውም የራስ ተፈሪና ቤተሰቦቻቸው ሀኪም የሆኑት ሊባኖሳዊው ዶክተር አሳድ ቼይባን ራሳቸው የበሽታው ተጠቂ ነበሩና የራስ ተፈሪን ቤተሰብ የሚያክም ጠፍቶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

ራስ ተፈሪ መኮንን እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አቴጌ መነን አስፋው

ከህዳር 7 እስከ ህዳር 20 1911 ዓ.ም ለአስራ አራት ቀናት ገደማ የቆየው በሽታው በህዳር ወር የተከሰተ በመሆኑም ህዝቡ የህዳር በሽታ እያለ ይጠራው ጀመር፡፡ ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት ወረርሽኙ እስከ አርባ ሺህ ኢትዮጵያዊንን ለሞት ዳርጋል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ዘጠኝ ሺህ ዜጎች በበሽታው ሞተዋል፡፡
በተለይም ህዳር 12 ቀን 1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሞቱበት በመሆኑ ቀኑ በጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር፣ ከዚያ በሃላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደባህል ተወስዶ በየዓመቱ ህዳር 12 ቀን የጽዳት ዘመቻ ይደረግ ጀመር፤ ይህም በተለምዶ ህዳር ሲታጠን የምንለው ነው፡፡

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በየአመቱ ህዳር 12 ቀን ቆሻሻን ማቃጠል ማህበረሰባዊ ልማድ ነው

በስፓኒሽ ፍሉ በሽታ የተደረጉ የህክምና ምርምሮች እና ውጤቶቻቸው

ዶ/ር እናውጋው መሃሪ ፣ዶ/ር ክንፈ ገበየሁ እና ዶ/ር ዘርጋባቸው አስፋው የተባሉ የህክምና ባለሙያዎች በጋራ ያሰናዱትና በ2013 እ.ኤ.አ የታተመው The Manual of Ethiopian Medical History ላይ እንደሰፈረው የ1918ቱ የእንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በአሜሪካን አገር የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ (Vanderbilt University) ምሁራን ሲሆን ወቅቱም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በሃላ ባሉት ዘመናት በየጊዜው የተሻሻሉ ክትባቶች በምርምር ተገኝተዋል፡፡
በ1918 ዓ.ም እንደተከሰተው እንፍሉዌንዛ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ባያውቅም ዛሬም ድረስ ግን የሰው ልጆች የጤና ፈተና መሆኑን አላቆመም፡፡እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ብቻ በመላው ዓለም አምስት መቶ ሺህ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዘርፊ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የእንፍልዌንዛ ክትባቶች የዋጋ ውድነት መፍትሄ ካላገኘ፣ ህዝቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ካልተሰጠ፣ መንግስታት በሽታውን ለመከላከል ከፍ ያለ ትኩረት እስካልሰጡ ድረስ በእንፍሉዌንዛ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት መቀነስ አዳጋች ነው፡፡


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading