ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

ፖለቲካችን እና ፖለቲከኞቻችን እኛው ራሳችንን ይመስላሉ !!!

ሀብታሙ ግርማ (በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር)

ዛሬ በውድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ደም ስንናፍቀው የኖርነውን የነጻነት አየር መተንፈስ በጀመርንበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርስ ለመነቋቆር እና ለመበጣበጥ የሚነሳበት ምክንያት የለውም፤ ነገሩ የፖለቲካ አጀንዳ ልዩነት (ቢኖር እንኳ በንግግር መፍታት ይቻላል) ሳይሆን የአመል ነው። የአመል ችግር የሚለውን የሚጠቀልል የአማርኛ ቃል የቅንነት ችግር (Lack of integrity) ነው። የፖለቲካችን ስንክሳርም ይህ የቅንነት ችግር ነው፡፡

ፖለቲካችን ከሽኩቻ፣ ከጥሎ ማለፍ እና ሴራ ያልተላቀቀው በምንም ሳይሆን በልሂቃኖቻችን ባህሪያዊ ምክንያቶች ነው፡፡ የዚህ ሁሉ መሰረቱ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አጥፊ ባህላችን የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህም ልዩነቶችን በንግግር ሳይሆን ከሆነ በጠብ፣ በሴራ፣ ካልሆነ በኩርፊያ መፍታት ባህላችን መሆኑ ነው፡፡ ቅንነት የሌለበት የህይወት እንቅስቃሴ ሁሉ ጨው የሌለው ወጥ እንደማለት ነው፡፡ ኑራችንን ሁሉ አያጣፍጠውም፤ የአንዳችን ማሸነፍ የሌላችን መሸነፍ፤ የአንዱ መሻል የሌላው መቆርቆዝ፤ የአንዱ ማግኘት የሌላው ማጣት፤ የአንዳችን ማደግ የሌላው መደህየት ይመስለናል፡፡

እናም ሁል ጊዜ ነገሮችን የምንረዳበት መነጽር ሁሉ ከነባራዊ ሁኔታዎች (ለምሳሌ ከጊዜ፣ ከቦታ፣ ከሁኔታ) አንጻር ሳይሆን ከራሳችን ፍላጎት አንጻር ነው፡፡ በዚህም ነገራችንን ስንመዝን ከራሳችን ድክመት ወይም ጥንካሬ አንጻር ሳይሆን በቅርባችን ካሉ፣ ከምናውቃቸው ሰዎች ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች ላይ መፍረድ ልማዳችን ነው፡፡

ሀይማኖተኛ ህዝብ ነን ብንልም እምነት ላይ እምብዛም ነን፤ አትፍረድ ይፈረድብሃል፤ በልንጀራህን ከራስህ አስበልጠህ ውደድ፤ ሁለት ካለህ አንዱን አካፍል ወዘተ…. የሚሉት የአምላክ መመሪያዎች ጉዳችን አይደሉም፡፡

ከሌሎች ጥንካሬ ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ የሌሎችን ስኬት የማሳነስ፣ የበታችነት ስሜት፣ እኔስ ከማን አንሼ የህይወት መመሪያዎቻችን ናቸው፡፡ ኑራችን ሁሉ ከራሳችን ጋር ሳይሆን በሌሎች ህይወት ውስጥ ነው፤ ለዚህም ነው በነገራችን ሁሉ መሻሻልን ለማምጣት የሚያስፈልገው የራስን ድክመትና ጥንካሬ ማወቅ ፍላጎቱም አቅሙም ያጣነነው፤ የዚህ ውጤት ወይም ነጸብራቅ ደግሞ በአብዛኛው የምናጠፋው ጊዜ ለራሳችን ህይወት መሻሻል በሚጠቅሙ ጉዳዮች ሳይሆን በረብ የለሽ ጉዳዮች ተጠምደን ነው፤ በማያልቅና አላስፈላጊ ፉክክር፣ በንትርክ አልያም ሽኩቻ መባዘናችን መገለጫችን ነው፡፡

የፖለቲካ ልሂቃን የምንላቸው ከሌላ አገር ወይም ፕላኔት የመጡ ሳይሆኑ ከኛው ከህዝባችን የሚመዘዙ፣ የዚህ ጎጂ ባህላችን ሰለባዎች በመሆናቸው ከእያንዳንዳችን መደበኛ ዜጎች የተለየ ስብዕና እንዲኖራቸው መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የፖለቲካችን ስሪት ወይም አይነተኛ መገለጫ ከላይ የተገለጸው፣ እርስ በርሳችን ያለን ግንኙነት መልክን ይመስላል፡፡

ዋና ዋና የፖለቲካችን እና የፖለቲከኞቻችንን መገለጫዎች የኛኑ የእያንዳንዳችንን ስብዕናን ይመስላሉ፡፡

የፖለቲካ አጀንዳዎቻችን ህዝባዊ ፋይዳ የሌለው መሆኑ፣ አንድ አይነት የፖለቲካ እሳቤ ይዞ ነገር ግን በተቃራኒው ጽንፍ የረገጠ የፖለቲካ ልዩነት አይነት ምስቅልቅል ፖለቲካ፤ የልሂቁ ክፍል የብስለት ደረጃ ፖለቲካ አጀንዳ ከሚፈልገው እና/ወይም ከሚጠበቀው በጣም የወረደ. መሆኑ፣ የፖለቲከኞቻችን ስብዕና ከመደበኛው ኢትዮጵያዊ ስብዕና ያልተሻለ መሆኑም ለዚያ ነው፡፡
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ትውልድ አሻጋሪ ሃሳብ አንግው ፖለቲካን የሚያራምዱ፣ በፖለቲካ ስብዕናቸውም ሆነ በግል ስብዕናቸው የላቁ ፖለቲከኞች ቢኖሩንም ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ነው፡፡

በአጠቃላይ ቅን አለመሆናችን ለብዙ መከራ ዳርጎናል፤ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገራዊ ችግሮቻችን መነሾ ናቸው የምላቸው ምክንያቶች የዚሁ ውጤት ናቸው፤ የቅንነት ችግር ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
• እውነትን ከሐሰት፤ ትክክለኛውን ከስህተተኛ ለመለየት የመንፈስ፣ የሞራልም ሆነ የአእምሮ ዝግጁነት ማጣት፣
• በስሌት ሳይሆን በስሜት መነዳት፣
• ለበረታው ዕውቅና ከመስጠትና በመንፈሳዊ ቅናት( rational selfishnes) ተነሳስተን ከስኬቱ ሂደት ለመማር ከመሞከር ይልቅ ስኬቱን ለማሳነስ መሞከር፣
• ብልጣብልጥነት፣ ጮሌነት እና የድል አጥቢያ አርበኝነት።
እኛ ኢትዮጵያውያን ቅን ብንሆን ኖሮ፦
• በህይወት መስመራችን ጉዳያችን የሆነን ነገር የምናውቅ፣ በመሆኑም አላስፈላጊና ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችን እንደ ጉዳይ ወስደን ራስ በራሳችንን ባላደከምን፣ የምናደርገው ነገር ሁሉ በምክንያት በሆነ፣ የድርጊቶቻችን ውጤት አንዱን ይዞ አንዱን መጣል አይነት ሆኖብን ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለፈጣሪ እንኳ አስቸጋሪ ህዝቦች ባልሆን ነበር።
• ለተንሸዋረረ የታሪክ አረዳዳድ ባልተጋለጥን ነበር፤ የረጅም ዘመን ታሪካችን ለአንድነታችን መሠረት የሆኑ እጅግ በርካታ በጎ ሁነቶችን ያዘለ ቢሆንም ይህ የታሪክ እውነት ደብዝዞ በአንጻሩ ያለፈው በጎ ያልሆነው የታሪካችን አካል ባልደመቀ ነበር።
• በታሪክ ሂደት ያሳለፍነው በርካታ መልካም እንደነበር ሁሉ መልካም ያልሆኑ ግንኙነቶች እንዳሳለፍን እንረዳ ነበር። በመሆኑም የምንወዳት እና የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ የምንላት አገር ህዝቦቿ በተለያዩ ምክንያቶች(ኃይማኖታዊ፣ የማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳዳር ወዘተ….) በተለያዩ ወቅቶች በአገራዊ እና አለማቀፋዊ ገፊ ምክንያቶች እርስ በርስ የተዋጉ፣ አንዱ ሌላውን ያስገበረበት ሁነቶች በርካታ መሆናቸውን በአንድ በኩል የመካድ በሌላው በኩል የማጉላት አዝማሚያ የፖለቲካችን መዘውር (pillar) ሆኖ ባልተቸገርን ነበር።
• ዛሬ ላይ በጎ ያልሆነውን የታሪካችን አካል እና(ወይም) ወካይ ምልክቶቹን ማንሳታችን ተገቢነቱ ካለፈው ስህተታችን ለመማር እንጂ ለመነታረክ ፣ ለመበሻሸቅ፣ የአሸናፊነት ወይም የተሸናፊነት መንፈስ በማስረጽ ባልከፋፈለን ነበር።
• በመሆኑም ዛሬ ላይ ይህን በጎ ያልሆነ የታሪክ አሻራ ጠባሳ ሰለባ ያልሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል የሆነ ብሔር፣ የሐይማኖት እና የፖለቲካ ቡድን አለመኖሩ፣ በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህ የማህበረብ ክፍሎች(ህዝቦች) ድምር መሆኑን ተረድተን፣ የመጥፎ ታሪካችን ሰለባ የነበሩትን ወገኖቻችንን የሚያበሳጩ፣ ሰቆቃቸውን የሚያስታውሱ ምልክቶች ለሌላኞቻችን የድል አድራጊነት፣ የአሸናፊነት፣ ምልክት ከማድረግ በተቆጠብን ነበር።
• በአጠቃላይ ታሪካችን የመማሪያ ሳይሆን መጥፎ የታሪክ አሻራችን አገርሽቶ ሌላ መጥፎ ታሪክ ለመጭው ትውልድ ለሚያወርሱ እኩይ ድርጊቶች የሚጋብዝ፣ ትልቅ የተስፋ ጮራ የፈነጠቀውን የለውጥ ሂደት የሚቀለብስ፣ ሲከፋም የጋራ ቤታችን የምንላትን ኢትዮጵያ ምኞት ብቻ እንዳትሆን ትልቅ ስጋት ባልሆነ ነበር ።

እኛ ኢትዮጵያዊን ቅንነት ቢኖረን ኖሮ፦
• የአገር አንድነት እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ጨምሮ በእለት ተዕለት ግንኙነቶቻችንን የምንወያየው እና የምንከራከረው ፋይዳ ስላለው ጉዳይ ይሆን፣ በእንቅሰቃሴዎቻችን ሁሉ ትልቁን ምስል ባልተጋረደብን ነበር፣
• በታሪካችን አይተን የማናውቃቸው እንደ ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አብይ አህመድ፣ ደመቀ መኮንን አይነት ጥሩ መሪዎች አግኝተን በነቢብ እየደገፍናቸው በገቢር ግን እየወጋናቸው መሆኑን መገንዘብ ይቻለን ነበር፤መልካም አመራራቸውን ለመደገፍ ከመጣር ይልቅ በየዕለቱ የቤት ስራ ባልሆንባቸው ነበር።

ኢትዮጵያዊያን የቅንንነትን እሴቶችን እሴቶቻቸው በማድረግ ራሳቸውንም ሆና አገራቸውን ከጥፋት ይታደጉ ዘንድ ብቸኛው አማራጫቸው ነው።

መጪው ጊዜ ሁላችንም ቅንነትን የምንለማመድበት ዘመን ይሆን ዘንድ እመኛለሁ።


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading