ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዴት ይስፈን?

ማስታወሻ፦ ይህ መጣጥፍ ታህሳስ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ለህትመት በበቃው የሪፖርተር ጋዜጣ ለአንባቢያን ደርሷል። መጣጥፉን በድጋሚ የመለጠፍ አስፈላጊነት የጽሑፉ ጭብጥ ዛሬም ከአንድ አመት በኋላ ጉዳይ ሆኖ በመቀጠሉ ነው። በእርግጥም በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም መደፍረሱ ተባባሰ እንጂ የመቀነስ አዝማሚያ አላሳየም።

መግቢያ

በማኅበረሰብ የንቃተ ህሊና መለኪያ (Social Pyramid)ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በቀደምትነት የምናገኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ነው። ነገር ግን በአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የተማረው ክፍል ምክንያታዊነትና አመክንዮ ርቆት በቡድናዊነት፣ በወገንተኝነትና በብሔርተኝነት ጥላ ተፅዕኖ ሥር ወድቋል፡፡ ትምህርት መሠረታዊ ዓላማውን የሳተ ይመስላል። የዚህ ነፀብራቅ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች፣ የጎጠኝነትና የቡድን ፀብ መናኸሪያ እየሆኑ መምጣታቸው አንዱ ነው።

ተማሪዎች ከሚጠበቅባቸው የሥነ ምግባርና የንቃት ደረጃ የመውረዳቸውን መነሾዎች ስንመረምር የሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ። ከዚህ አንፃር የሥነ ትምህርት ፍልስፍና፣ የትምህርት ሥርዓቱ አስተዳደር፣ የከፍተኛ ትምህርት አስተዳደር ዘይቤ፣ እንዲሁም የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ሚና ተጠቃሽ ናቸው። ይህ መጣጥፍ በእነዚህና በተዛማጅ ነጥቦች ዙሪያ የወፍ በረር ቅኝት ያደርጋል።

የትምህርት ዓላማና ግብ ምንድነው?

ትምህርት ምንድነው? ዓላማውና ግቡ ምን መሆን አለበት? የትምህርት አሰጣጡ እንዴት ይሁን? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ሁለት ዓይነት እሳቤዎች (Schools of Thought) አሉ። የመጀመርያው “Humanist School” ሲሆን፣ ሁለተኛው “Behavioral School” ነው።

በ “Humanist School” እሳቤ የትምህርት ዓላማ የሕዝቡን የአስተሳሰብ፣ ሞራልና ማኅበራዊ መስተጋብሩን ማጠናከር ነው፡፡ ግቡም ተማሪዎች ኃላፊነት እንዲሰማቸው፣ ዕውቀትና ጥበብን ለመመርመር ተነሳሽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ከ “Behavioral School” አኳያየትምህርት ዓላማ ጊዜው የሚጠይቀውን ችግር ለመፍታት ሲሆን፣ ግቡም ቁሳዊ ሀብት ማምጣቱ ነው። ይህን የሥነ ትምህርት ፍልስፍና መሠረቱ ያደረገ የትምህርት አስተዳደር ሦስት መዋቅሮች አሉት። በመጀመርያው እርከን ላይ የትምህርት አመራሮችን እናገኛለን፡፡ ተግባራቸውም የትምህርት ፖሊሲ መቅረፅ፣ ማቀድና በበላይነት ማስተዳደር ነው። በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙት ደግሞ የምሁራዊነት አባቶች ሳይንቲስቶችና መምህራን አሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ምንም ሥልጣን የሌላቸው፣ ተቀባይ እንጂ አጥብቆ ጠያቂነት (Skepticism) እሴት የሌላቸው ተማሪዎች አሉ፡፡

ይህ የትምህርት ፍልስፍና በዘመናችን ገኖ የወጣ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ጅማሮ አንስቶ የሰረፀም ነው፡፡

የሥነ ትምህርት ፍልስፍናና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

የትምህርት አስፈላጊነት የባህሪ ለውጥ ማምጣት እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራል። አንድ ሰው የባህሪ ለውጥ አመጣ ሲባል ደግሞ ሰብዕናው ችግር ፈቺ በሆኑ እሴቶች መገንባቱ ነው፡፡ በሰብዕናው መንፈሰ ጠንካራ የሆነ ማለት ነው።

በትምህርት የገፋ ሰው ሲባል ወኔ ያለው፣ ተስፋ የማይቆርጥ፣ ለችግር የማይሸነፍ፣ ችግር በገጠመው ጊዜ ችግሩን ደጋግሞ ከማሰብ ይልቅ ስለመፍትሔው የሚያስብ ሰብዕናን የተላበሰ፣ በመሆኑም ከስሜታዊነትና ከጨለምተኝነት የፀዳ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የትምህርት መሠረታዊ ግብ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት መሆኑን ዕውቅና የሰጠ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት መተግበር ያስፈልጋል።

አንድ አገር የሆነ ችግር ሲገጥማት ችግሩን ሊፈቱ የሚችሉ የትምህርት ዘርፎች ዙሪያ ለማሠልጠን መነሳሳቷ ክፋት ባይኖረውም፣ ጨርሶውኑ የትምህርት መነሻውም መድረሻውም ቁሳዊ ፍላጎት መሆኑ ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀደመው ዘመን የነበረው የትምህርት ሥርዓት የተሻለ እንደሆነ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ነው። ከ40 እና 50 ዓመታት በፊት ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር፣ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የግብረ ገብ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይህ የለም፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የተማሪዎች ግብረ ገብ ማሽቆልቆል፣ እንዲሁም መምህራን የተማሪዎችን ሥነ ልቦናዊና የሞራል እሴቶችን በማጎልበት ረገድ የነበራቸው ሚና እየቀነሰ መምጣቱ ነው።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለድርሻዎች ሚና

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ የሚጀምረው በ1890 ዓ.ም. ነው። ከዚያ ቀድሞ የትምህርት ዘርፍ በሃይማኖት ተቋማት ይሰጥ ነበር። ይህም በተለምዶ የባህላዊ ትምህርት ሥርዓት ተብሎ የሚታወቀው በቤተ ክርስቲያንና በመስጊድ ውስጥ በሃይማኖት ሊቃውንት ይሰጥ የነበረው ነው። የኢትዮጵያ የሥነ ትምህርትና የታሪክ ምሁራን በጥናታቸው እንዳስገነዘቡን፣ የትምህርት ዘርፉ ተግዳሮቶች ሁለት ናቸው። እነርሱም የትምህርት ፍልስፍና መሠረቶች ችግሮች ያላቸው መሆኑ፣ እንዲሁም በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግሥታት በትምህርት ሥርዓቱ ጣልቃ መግባታቸው ነው።

በርትራንድ ራስል የተባለ እንግሊዛዊ ሊቅ እንደሚያስቀምጠው፣ አንድ መንግሥት (ሥርዓት) የተመሪውን ሕዝብ ዕድል ይወስናል፡፡ ሕዝቡን ለልማትም ሆነ ለጥፋት ሊያውል ይችላል፡፡ ሕዝብ በጋራ ተስማምቶ ይኖር ዘንድ በበጎም ሆነ በአሉታዊ ተፅዕኖው የጎላ ነው። በአጠቃላይ መንግሥት የሕዝቡን የሞራል ከፍታ በመወሰን ረገድ የላቀ ሚና አለው። የትምህርት ዘርፉን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ባህሪ በመንግሥቱ ባህሪ ይወሰናል።  በመሆኑም መንግሥት ይህን ተፅዕኖውን ለበጎ ተግባራት ማዋል ያሻዋል።

እንደ አንድ የመንግሥት አካላት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በተማሪዎቻቸው ዘንድ በጎ እሴቶችን በማስረፅ የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። ተማሪዎች የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ማንነት ያላቸው እንደሆነ ይታወቃል። በመሆኑም እነዚህ ልዩነቶች ውበት እንጂ የፀብ መነሻዎች እንዳይሆኑ መላው የዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት ሊሠሩ ይገባል። የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ለተማሪዎች መብቶች መከበር ፅኑ አቋም ያለው፣ ከሙስናና ከብልሹ አሠራሮች የፀዳ መሆኑ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል።

መምህራን ለተማሪዎቻቸው የዕውቀት አባቶቻቸው ናቸው፡፡ የተማሪዎቻቸውን ግንዛቤና የሞራል ከፍታ በማጎልበት ረገድ ያላቸው ተፅዕኖም የላቀ ነው። መምህራን ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ተማሪዎቻቸውን ስለኢትዮጵያዊነት እሴቶች ማለትም በክፉ ቀን መረዳዳት፣ ፈሪኃ እግዚአብሔር፣ ለሕግ መገዛት፣ ሥርዓተ መንግሥትን ማክበር፣ ውለታ አለመርሳት፣ ለይቅርታና ለዕርቅ ዋጋ መስጠት፣ ይቅር ባይንና አስታራቂን ማክበር፣ ወዘተ መስበክ የሙያ ግዴታቸው ነው።

በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን በተማሪዎች መሀል መከፋፈል የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በሚያስተውሉ ወቅት ቸል ሳይሉ እንዲታረሙ መገሰፅ አለባቸው። በሕዝቡ መሀል ለዘመናት የነበረውን የመተማመንና የመተባበር እሴቶችን የሚንዱ ተግባራትን በአደባባይ መታገል አለባቸው።


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading