ለማ መገርሳ ቢደመሩ ጥሩ ነው፣ ባይደመሩ መጥፎ አይደለም!
ሀብታሙ ግርማ
ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም
ጅግጅጋ፣ ኢትዮጵያ
ቁም!
የዚህን መጣጥፍ ርዕስ ብቻ አንብቦ ተስፈኛ ካድሬ (ተካ) ብሎ የሚፈርጅ ካለ (አይጠፋም)፣ መልሴ አዎ ተካ ነኝ የሚል ነው። የዶ/ር አብይ አህመድ ካድሬ ሊሆን የሚችለው እንደአብዛኞቹ የደርግ (ኢሠፓ) ወይም የኢህአዴግ ካድሬዎች በስብዕናው ሆዱን የወደደ ወይም ማዕረጉን(ክብሩን) የጠላ ሳይሆን ሁለቱንም የሚጸየፍ ነው። የአብይ ካድሬ ከበዛ ግለኝነት (ego) ባርነት ራሱን ነጻ ያወጣ፤ ከራሱ ጥቅም ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ የሚሰጥ፤ ለአገልግሎቱ ክፍያው የህዝብ ጥቅም የሆነ፣ በጥቅም ተደልሎ ሳይሆን በበጎ ፍቃድ እሴቱ (voluntarism) ተነሳሽነቱ በመሆኑ የአብይ ካድሬ ብሆን ኩራት ይሰማኝ እንጂ አልሸማቀቅም።
መግቢያ
የብሔር (የማንነት) ፖለቲካ ባይመቸኝም ከብሔር ፖለቲካ በአንድ ጊዜ መውጣት አስቸጋሪ መሆኑን ስለምገነዘብ ቢያንስ የፖለቲካ አስተዳደሩ መርህ የብሔር ማንነትን ከአገራዊ አንድነት ጋር ያስማማ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ። ይህን ምልከታዬን በተደጋጋሚ ለህዝብ በደረሱት ፅሑፎቼ አስነበቤአለሁ። ይህ እሳቤዬ የዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣንት ተከትሎ መንግስታዊ መርህ እንደሆነ ተስፋዎች አይቻለሁ። በቅርቡ የብልፅግና ፓርቲ ምስረታን ተከትሎ ይህ የግል አቋሜ ፖለቲካዊና ተቋማዊ ቅርጽ ሊይዝ እንደሆነ ስገነዘብ በዶክተር አብይ አህመድ የአመራር መርህ በሆነው መደመር ፍልስፍና ላይ የነበረኝ እምነት ይበልጥ ጨመረ። በግሌ ከዶክተር አብይ መምጣት ቀድሜ ነው የተደመርኩት። ለዚህ ደግሞ በ2008 ዓ.ም በተጻፈውና በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጆርናል በታህሳስ 2010 ዓ.ም የታተመውን ጽሑፌን ማንበብ ይቻላል።
በነገራችን ላይ ይህ ጥናት የአሜሪካ የካሊፎርኒያ አገረ-ግዛት የሚገኘው ስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ እንደማጣቀሻ ያገለግላል ብሎ ተማሪዎቹ እንዲያነቡ በቤተ-መፃህፍቱ አኑሮታል። አንባቢ በሚከተለው ሊንክ ሊያገኘው ይችላል።
ለማ መገርሳ ቢደመሩ ጥሩ ነው፤ ባይደመሩም መጥፎ አይደለም!
ከላይ ያቀረብኩት ሀተታ ያለፉት ሁለት ቀናት በአገራችን የፖለቲካ መንደር የተሰማውና የለውጥ አመራሩ የመከፋፈል መርዶን ተከትሎ አሁንም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሊ ጎን መሆኔን ለመግለጽ፣ እንዲሁም ምንምንኳ አልደመርም ቢሉም (መብታቸው ነው!) ለታላቁ መሪ ኦቦ ለማ መገርሳ ያለኝን ክብር ለመግለጽ ነው። በነገራችን ላይ አለመደመር ማለት መቀነስ ማለት አይደለም። በመደመር ቀመር መሠረት ፍረጃ የለም፤ ወዳጅ፣ጠላት፤ተደማሪ፣ተቀናሽ የሚባል ከቶውንም የለም!
በእኔ እምነት የኦቦ ለማ መገርሳን ውለታ የሚረሳ ከሃዲ ነው። ሰውየው ጭቆናን እና ጨቋኞችን አሳዶ መቀመቅ ለመክተት በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል ፊትአውራሪ ነበር። ለዚያም ነው ‘ለማ መገርሳን የሚያህል ግዙፍ ከአብይ አህመድ ተነጥሎ ለውጡ ምን ያህል ርቀት ይጓዛል?’ የሚለው የሚያሳስበን።
ምንምን’ኳ የለማ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የላቀ ቢሆንም፣ ከአብይ መለየታቸው ግን መጥፎ አይሆንም። ‘የለውጡ ጎማ ፍጥነቱን ሊቀንስ ቢችልም ከግቡ መድረሱ አይቀርም’።
በአገር እና በህዝብ መቀለድ ይቅር የማይሉት ወንጀል ነው!
በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ከተጀመረበት ከ1950 ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የግለሰቦች ፓርቲዎችን መምጣት እና መሄድን ከአገር ህልውና ጋር ማያያዝ እየተለመደ የመጣ የማይጥም ቀልድ ነው። አንድ ሰው ሲቀልድ በራሱ ላይ ቢሆን አዝናኝ ነው፤ ካልሆነ ከቅርብ ወዳጅ ጋር ክብርን የጠበቀ ቀልድም ይቻላል፤ ነገር ግን በአገር እና በህዝቦቿ ላይ መቀለድ ይቅር የማይባል ጸብ ነው!
በተለያዩ ወቅቶች ይህችን አገር የሥልጣን ጥማታቸውን ለማርካት መያዣ እያደረጉ ሊቆምሩባት የሞከሩ ቀልደኞች ሁሉም ተዋርደዋል። በቅርብ ዘመናት እንኳ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ፣ መንግስቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊ ሁሉም ሞክረው መጨረሻቸው ስደት አልያም የውሻ ሞት ሆኖ አይተነዋል። አብይ አህመድ ከዚህ የተማረ ይመስለኛል፤ ካልሆነ እርሱም ልኩን ያገኛል። ዛሬም ‘ለማ መጣ፣ ለማ ሄደ ነው’ እንጂ የእርሱን ግለሰባዊነት ከአገር ህልውና ጋር ማዛመድ በመቶ ሚሊዮን ህዝብ ላይ ማሾፍ ነው። ማንም ምንም ቢዘባርቅ ኢትዮጵያ ትናንት ነበረች፣ ዛሬም አለች፣ ነገም ትኖራለች።
ከብልግና ፓርቲ ጋር ወደፊት!
የቀድሞው ኢህአዴግ (የአሁኑ ብልጽግና) ሰዎች ህዝብን በዘር ሸንሽነው ኢትዮጵያን እንመራለን ብለው ሞክረው ነገር ግን ራሳቸው ተከፋፍለው ተባሉ። ለህዝብ ያነሱት ሰይፍ ራሳቸውን ቀላው። የብልጽግና ፓርቲ ዕውን የመሆኑ መግፍኤ ይህ ይመስለኛል።
ይህ መሬት እንዲወርድ ከተፈለገ ደግሞ ቢያንስ የፖለቲካ አመራሮች (ልሂቃን) ከብሔርተኝነት የተላቀቁ መርህ የተመሠረተ እንደሆነ እረዳለሁ። እንግዲህ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሁሉም የለውጡ አመራሮች ይህን አምነው ነው ብልጽግናን የመሠረቱት።
ይህ ከሆነ በኋላ ‘ይኼ ቢሆን ኖሮ አይ ያ ቢሆን ኖሮ ማለቱ የራስ ድክመት ነው።’ ከአሁን በኋላ በግለሰቦች ጸብ ህዝብ ሊንገጫገጭ አይገባም፣ አይችልምም!
በመሠረቱ ኦቦ ለማ መገርሳ አልደመርም ማለታቸው ደካማ አያስብላቸውም፤ ወትሮውንም የአቋም ሰው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፖለቲከኛ መሆናቸውን አንዘንጋ፤ ነገር ግን የሃሳብ ልዩነታቸውን በሴራ ፖለቲካ የሚያወራርዱ ደካማ ሰው አይመስሉኝም።
በዚህ ሁለት ቀናት እንደታዘብኹት ለማ መገርሳን በሃሳብ ተሸንፈው የተሸኙ የደካማ ደካሞች መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው አሰፍስፈው እየጠበቋቸው ነው። ከነውረኞች መንደር እግራቸውን በማራቅ ክብራቸውን እንደሚጠብቁ ሙሉ እምነት አለኝ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ይባርክ! አሜን!

አስተያየት ያስቀምጡ