ሀብታሙ ግርማ ደምሴ
ማስታወሻ፡
ይህ መጣጥፍ የስነ ጽሁፍ ሰዎች እና ስራዎቻቸው፡ ልቦለድ፣ የተውኔት ድርስት እና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ (1850-1960 ዎቹ) ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ መጽሐፉ በ2011 መስከረም ወር ለህትመት የበቃ ነው፡፡
አሀዱ ሳቡሬ በሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት በድሬደዋ ኢሳና ጉርጉራ አውራጃ፣ አዲጋላ በተባለች መንደር በ1917 ዓ.ም ተወለዱ፤ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የኔታ መንግስቱ ከተባሉ መምህር ዘንድ ፊደል ቆጥረዋል፣ ዳዊት ደግመዋል፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት በድሬደዋው አሊንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ት/ቤት ነው፤ ሶስተኛ ክፍል ሳሉ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በመውረሩ ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም፤ ሀገሩ በጥቂቱም ቢሆን ሲረጋጋ የኢጣሊያንኛ ቋንቋ በድሬዳዋ ከተማ መሰጠት ተጀምሮ ነበርና አሀዱም ቋንቋውን መማር ጀመሩ፡፡
የስምንት ዓመት ታዳጊ ሳሉ አባታቸውን በሞት የተነጠቁት አሀዱ ሳቡሬ መስየ(ሚስተር) ሳቡሬ የተባሉ ፈረንሳዊ ባለሀብት (አባታቸው ተቀጥረው ይሰሩበት የነበረው ድርጅት ባለቤት ናቸው) ታዳጊውን በአደራ ተረክበው እንደ ልጃቸው እየተንከባከቡ አሳደጓቸው፤ በመስየ ሳቡሬ ስም መጠራታቸውም ለዚያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ታሪክ ታላቅ ቦታ የሚሰጣቸው አሃዱ ሳቡሬ ‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ› ጋዜጣ ስትመሰረት የጋዜጣዋ የመጀመሪያው ዋና አዘጋጅ ነበሩ፤ በኢትዮጵያ ሬዲዮም ለዓመታት ሰርተዋል፤ አሃዱ ሳቡሬ የሚለው ስም በተለይ በ1950ዎቹ እጅግ የገነነ እንደነበር ይነገራል፤ ለጋዜጠኝነት መርሆዎች በመገዛት ጥራት ያላቸውን የጋዜጣና የራዲዮ ፕሮግራሞች ያዘጋጁ መሆናቸው በህዝብ ዘንድ አድናቆትና ለእውቅናቸው መሰረት ቢሆንም ከዚህ ባልተናነሰ ለዕውቅናቸው ምክንያት የሆነ ሌላም ነገር አለ ይባላል፤ ይህን ጉዳይ ምን ይሆን?
“……(አሀዱ ሳቡሬ የሚለውን) ስም ታዋቂ ያደረገው አንጋፋ ጋዜጠኛ የነበሩት ብላታ ወልደ ጊዮረጊስ ወልደ ዮሃንስ እኔን አለቃችን አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ለስራ ጉዳይ ናዝሬት አስጠርተውን በሄድንበት ወቅት ከተፈጠረ አጋጣሚ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው፤ የአቶ ይድነቃቸው አባት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እዚያ ሆቴል ስለነበራቸው እሳቸው ሆቴል አልጋ ይዘን ነበር፤ ብላታ ወልደጊዮርጊስ አሀዱ ሳቡሬ የሚባለው ወጣት ጋዜጠኛ ሁላችንንም የሚያስደንቅ እርሱ ነው፤ ብለው ከነጋ ድራስ ተሰማ ጋር ሲያስተዋውቁኝ እርሱንማ በደንብ አውቀዋለሁ ጋዜጣውንም አነባለህ አሀዱ ሳቡሬ አጠገበኝ ወሬ ብለው በግጥም መልክ መናገራቸው ደግሞ ሌለው ለመታወቄ አንዱ ምክንያት ነው፡፡”
አሃዱ ሳቡሬ ጋዜጠኝነት የራሱ የሆነ መርሆች እንዳሉት፣ ጋዜጠኞችም ለመርሆቹ ተገዥ መሆን እንዳለባቸው፣ ሙያው በዕውቀትና በትምህርት የተደገፈ መሆን እንዳለበት ያስገነዘቡ በሳል ጋዜጠኛ ናቸው፤ የመናገርና የመጻፍ ነጻነት በእጅጉ የተገደበ በነበረበት የአጼ ሀይለ ስላሴ ዘውዳዊ አገዛዝ ወቅት ስለ ፕሬስ ነፃነት አስፈላጊነት በአደባባይ ይናገሩ ነበር፤ ለዚህ ተፈጻሚነትም የሚችሉትን አድርገዋል።
በ1966 ዓ.ም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ተብለው በልጅ እንዳልካቸው መኮንን ሲታጩ ስልጣኑን ከመረከባቸው በፊት በአንድ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን ነበረባቸው፤ ይህም መንግስት ለጋዜጠኝነት መርሆች መከበር የነበረውን ቁርጠኝነት ነው፤ ሹመቱን የሚቀበሉት ህዝቡ በራዲዮ፣ በጋዜጣና በቴሌቪዥን ሀሳቡን በነፃነት መግለፅ እንዲችል መንግስት ሲፈቅድ ብቻ እንደሆነ ለልጅ እንዳልካቸው አስረግጠው ገልጸው፣ ይህም ተፈጻሚ እንደሚሆን ቃል ተገብቶላቸው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ስራ ጀመሩ፤ ሆኖም በዚህ ሀላፊነት ጥቂት እንደሰሩ የተገባላቸው ቃል ተፈፃሚ ባለመሆኑ የስልጣን መልቀቂያ አቅርበው ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳትን መርጠዋል፡፡
ጋዜጠኛ አሃዱ ሳቡሬ የ1953ቱ የታህሳስ ግርግር ሲነሳ ስማቸው አብሮ ይነሳል፤ በወቅቱ የመፈንቅለ መንግስቱ ተዋንያን ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድ በንጉሰ ነገስቱ ትዕዛዝ የጦር ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ነበር፤ የችሎቱን ውሎ እንዲዘግቡ የተመረጡት ጋዜጠኛ አሀዱ ሳቡሬ የፍርዱ ሂደቱን በተከታታይ በሬዲዮና በጋዜጣ ዘግበዋል፤ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመስጠት በተሰየመው ችሎት ላይም እንደተለመደው ሂደቱን ሊዘግቡ በፍርድ ቤቱ የተገኙት አሃዱ ሳቡሬ ነበሩ፤ በፍርድ ቤቱ ውሎም አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት ጀነራል መንግስቱ ነዋይ ጥፋተኛ ተብለው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይጠየቃሉ መንግስቱ ነዋይም በብዙዎች ዘንድ ዛሬም በዘውዳዊው መንግስት አወዳደቅ ላይ የትንቢት ያህል ተናገሩ በሚባለው ታሪካዊ ንግግራቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ካሰሙ በኋላ ችሎቱ ለጥፋታቸው ውሳኔ ለመስጠት ለሌላ ቀን ቀጠሮ በመስጠት ይጠናቀቃል፡፡
አመሻሹ ላይ ህዝብ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው የችሎቱ ውሎ በሬዲዮ ሊዘግቡ ጋዜጠኛ አሀዱ ተዘጋጅተዋል፤ ዘገባቸውን ሲያቀርቡ የጀነራል መንግስቱን ወታደራዊ ግርማ ሞገስ፣ ድፍረት የተሞላበት ንግግሩንና የነበረውን መንፈሰ ጠንካራነት ከሞንጎሊያው መሪ ‹ጀነራል ካን› ጋር በማነፃፀር ነበር፤ የወቅቱ ሹማምንት ግን በጋዜጠኛ አሃዱ ሳቡሬ ዘገባ አልተደሰቱም፤ ‹እንዴት ወንጀለኛ ተሞካሽቶ የነገርለታል?› ፣ ‹ የዘገባው መንፈስ ንጉሰ ነገስቱን ከማዋረድ ይቆጠራል› በሚል የትችትና ዛቻ ናዳ አወረዱባቸው፤በዚህ መዘዝም በአርሲ ክፍለ ሀገር አሰላ ከተማ ለአምስት ወራት ያህል በቁም እስር (በግዞት) እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡
አሃዱ ሳቡሬ ብስለት በተመላበት ዘገባዎቻቸው በህዝብ የተደነቁ ጋዜጠኛ ናቸው፤ ዘገባዎች እውነታን ሳይደፈጥጡ፣ ነገር ግን ከአገር ጥቅምና ክብር እንዲሁም ሉአላዊነት አንጻር የተቃኙ መሆን አለባቸው የሚል መርህ እንደነበራቸው የአንድ ወቅት የስራ ገጠመኛቸው ይህን ማንነታቸውን ያሳየናል፤ ጊዜው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን የተቀላቀለችበት ሰሞን ነው፤ በወቅቱ የኤርትራ ፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ደጃዝማች ተድላ ባህሩ የፌዴሬሽኑ የበላይ ጠባቂ ለነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ በቤተ መንግስት ቀርበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀርባሉ፤ ይህን ዜናም በወቅቱ ጀማሪ የቤተመንግስት ዜና ሪፖርተር የነበሩት ጋዜጤኛ ዘውዴ ረታ (በኋላም አምባሳደር) የአቀባበሉ ሂደትና የውይይታቸውን ይዘት ሰፋ ባለ ሀተታ አቀረቡ፤ በጊዜው ማንኛውም ዜና ለህዝብ ጆር ከመድረሱ በፊት ሰባት አባላት ባሉት የዜና አጽዳቂ ቦርድ ይገመገም ነበር፤ ይህም ዜና በተመሳይ ሂደት ማለፍ ስላለበት ለቦርዱ ይቀርባል፤ ከቦርድ አባላቱ አንዱ የነበሩት አሃዱ ሳቡሬ በዜና ዘገባው አልተደሰቱም፤ ‘ምንም እንኳ ዘውዴ ያየውንና የታዘበውን በሀተታው ቢነግረንም ዜናው ለአንድ የአገር መሪ በሚሰጥ የዜና አዘጋገብ የቀረበ ነው፤ ኤርትራ በፌዴሬሽን የተዋሃደች አንድ የኢትዮጵያ አካል በመሆኗ ደጃዝማች ተድላ ባህሩ እንደ ሌሎች ክፍላተ አገራት ገዥዎች መታየት አለባቸው እንጂ እንደ አገር መሪ መቆጠራቸው አግባብ አይደለም፣ በመሆኑም ለግለሰቡ በሚመጥን ደረጃ አጥሮ ይቅረብ’ ብለው ሞገቱ፤ቀሪዎቸ የቦርድ አባላት ግን በዚህ አልተስማሙም ነበርና በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡበት የበላይ አለቃቸው ከነበሩት ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ዘንድ ደረሰ።
መኮንን ሀብተ ወልድም ዜናውን ካዩ በኋላ ዘውዴ የታዘዘውን መፈጸሙን፣ ነገር ግን ዜናው ይህን ያህል መንዛዛት ስለሌለበት አሃዱ ባለው መልክ ይፈጸም ብለው አዘዙ፤ በመሆኑም የኤርትራው ፌዴሬሽን ዋና ስራ ደጃዝማች ተድላ ባህሩ አዲስ አበባ መጥተው ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ዘንድ ቀርበው ስለ ኤርትራ ጉዳይ አስረድተው መመሪያ ተቀብለው እንደሄዱ በመግለጽ ዜናው አጥሮ ለህዝብ ተላለፈ::
ስማቸው ይበልጥ የሚነሳው በጋዜጠኝነቱ ይሁን እንጂ አሃዱ ሳቡሬ አገራቸውን በሚኒስትርነት እንዲሁም በክፍለ አገር አስተዳዳሪነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፤ በጅቡቲ ለሰባት ዓመታት ያህል እንዲሁም በሶማሊያ ለአምስት ዓመታት(ከ1961 እስከ 1965 ዓ.ም ድረስ) የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል፡፡ አሀዱ ሳቡሬ በአሁኑ ወቅት ኑሯቸውን በአገረ አሜሪካ ነው።

አስተያየት ያስቀምጡ