ሀብታሙ ግርማ
ይህ መጣጥፍ የስነ ጽሁፍ ሰዎች እና ስራዎቻቸው፡ ልቦለድ፣ የተውኔት ድርስት እና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ (1850-1960 ዎቹ) ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ መጽሐፉ በ2011 መስከረም ወር ለህትመት የበቃ ነው፡፡
አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም በዘመናዊ የኢትዮጵያ አገረ ግዛት ግንባታ መባቻ ወቅት በተራማጅ አስተሳሰባቸውና በሀይማኖታዊ አስተምህሮታቸው ጎልተው የሚነሱ የስነ ሃይማኖት (theology) ምሁርና የታሪክ ጸሃፊ ነበሩ፡፡ በዚህች አጭር መጣጥፍ የእኚህን አንጋፋ ሰው የህይወት ታሪክ በአጭሩ ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡ በህይወት ጉዛቸው ትርክት የወቅቱን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ከፍታና ዝቅታ ለማስቃኘት እሞክራለሁ።
አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም (1853 – 1916 ዓ.ም) ከቀደምት ኢትዮጵያዊያን ምሁራን አንዱ የሆኑት አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም ህዳር 21 ቀን 1853 ዓ.ም በወቅቱ አጠራር በጌ ምድር አገረ ግዛት፣ ከምከም ቃሮዳ፣ ይፋግ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡ በግብርና ስራ የሚተዳደሩት አባታቸው የትምህርትን ጥቅም ጠንቅቀው የተረዱ ነበሩና ልጃቸው ገና አፍ መፍታት ሲጀምር ከፊደል ገበታ እንዲተዋወቅ ወደ ትምህርት ቤት አስገቡት፤ የወላጆቻቸው እንክብካቤ ግን ብዙም የዘለቀ አልነበረም፤ እናታቸውን በህጻንታቸው ያጡት አለቃ ታዬ አባታቸው ጥለዋቸው ወደ ሸዋ ክፍለ አገር በመሰደዳቸው አጎታቸው ይኖሩበት ከነበረው ትግራይ እንዲሄዱ ሆነ፡፡ እዚያ ሲደርሱ ግን አጎታቸው ወደ ህንድ አገር እንደሄዱ ስለተነገራቸው ወደዚያው መሄድ አለብኝ ብለው ጉዟቸውን በመርከብ ለመጀመር ወደ ቀይ ባህር ዳርቻዋ ምጽዋ ከተማ አመሩ፤ ነገር ግን ውጥናቸው እንዳሰቡት ሳይሆን የህይወት ጉዟቸውን በሌላ አቅጣጫ የቀየረ ሆነ። በምጽዋ ምንም ዘመድም ሆነ የሚያውቁት ሰው ያልነበራቸው አለቃ ታዬ እንደ ቤተሰብ ሰብስቦ ሊያስተምራቸው የስዊድሽ ሚሽነሪ ት/ቤት ፈቀደ።
የስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት በአለቃ ታዬ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፤ በትምህርት አቀባበላቸው ፈጣን እና አይነግቡ ነበሩና የትምህርት ቤቱ ዲሪክተር የነበሩት ሊንዳሃል የቅርብ ረዳታቸው እንዲሆኑ አቀረቧቸው፤ በዚህም ቅዱሳን ጥንታዊ መጻህፍትን በመተርጎሙ ስራ ላይ የያኔው ወጣት ታዬ በትጋት ተሳትፈዋል።
አለቃ ታዬ መንኩሉ ከሚባለው የሚሽነሪ ትምህርት ቤት ሳሉ ለሀገረኛ መጽሃፍትና ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ስርዓት የተለየ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ጥንታዊ መጻህፍትንም እያደኑ አብዝተው ይመራመሩ ነበር፤ ነገር ግን መጻህፍቱ በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በመሆናቸው የግዕዝ ቋንቋን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፤ እናም በ1875 ዓ.ም ወደ ትውልድ መንደራቸው ተመልሰው ግዕዝ ትምህርት ቤት ገቡ፤ ከሁለት ዓመታት በኋላ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በጌ ምድርን ለቀው ወደ ምጽዋ አቅንተው በመምህርነት፣ በአስተርጓሚነትና በወንጌል ሰባኪነት አገልግለዋል።
የምእራቡን ክርስትና አስተምህሮ እና የአውሮፓን ባህል መሰረት አድርጎ የተቀረጸውን መንፈሳዊ የትምህርት ስርዓት በአንድ በኩል፣ እንዲሁም ከታላላቅ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አድባራትና ገዳማት የምስራቁን የክርስትና አስተምህሮ በጠለቀ ሁኔታ መርምረዋል፤ ያገኙትን መንፈሳዊ ዕውቀት ለህዝብ ለማስተላለፍም ‹መጽሀፈ ሰዋሰው› የሚለውን መጽሃፋቸውን አደራጅተው ነበር።
አለቃ ታዬ ከአስራ ሶስት ዓመታት በኋላ በ1890 ዓ.ም ወደ ትውልድ አገራቸው በጌምድር ተመልሰው ወንጌልን ሊሰብኩ፣ በዚያውም የቅኔ ትምህርታቸውንም በበጌ ምድር ዙሪያ በሚገኙ ታላላቅ ገዳማት ሊከታተሉ መጡ።
አስተምህሯቸው ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀኖናን የሚቃረን ነው በሚል ከህዝብ ውግዘትን አስነስቶባቸው ነበር። ማህበራዊ መገለል፣ ብሎም አካላዊ ጥቃት ተደጋግሞ ደርሶባቸዋል፡፡ የበጌምድር አውራጃ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት አባቶችና ካህናት ከሰዋቸውም ነበር፤ በዚህም የአውራጃው ገዢ ከነበሩት ከራስ መንገሻ አቲከም ዘንድ ቀርበው ሀይማኖታዊ አቋማቸውን እንዲገልጹ ተደረገ፡፡ በሸንጎው ላይ አለቃ ታዬ ባንድ ጎን፣ ከሳሾቻቸው ደግሞ በሌላ ሆነው ለረጅም ሰዓታት ተከራከሩ፤ ራስ መንገሻ አቲከምም የአለቃ ታዬን ሀሳብ ይበልጥ ገዢ ሆኖ ስላገኙት የሙግቱን የአሸናፊነት ፍርድ ሰጧቸው።
ይህ የአለቃ ታዬ አሸናፊነት ሙግቱን ከመርታትም ባለፈ ትርጉም ነበረው፤ አጋጣሚው ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርቲያን ሊቃውንት ጫና ለጊዜውም ቢሆን እፎይታን ለማግኘታቸው ምክንያት ሆናል። እንዴት? በክሱ ሰበብ ራስ መንገሻ አቲከምን አግኝተዋል፤ በአጭር ጊዜም ጥሩ ግንኙነት መስርተው ነበርና አለቃ ታዬ የሚደርስባቸው መገለልና መድልዖ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት እንዲያውቀው ሆኗል። ራስ መንገሻ አቲከም አለቃ ታዬን ደብዳቤ አስይዘውና አሽከራቸውን እንዲያጅቧቸው አድርገው ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሰደዷቸው።
በጊዜው የአጼ ዮሐንስ የልጅ ልጅ የሆኑት ራስ ስዩም መንገሻ በአጼ ምኒልክ መንግስት ላይ ሸፍተው ነበርና በራስ መኮንን የተመራ ጦር ወደ ሰሜን ዘምቶ ነበር፤ ምኒልክም የጦሩን ሁኔታ ለመከታተል ደነባ አካባቢ ተገኝተው ነበርና አለቃ ታዬን ያገኟቸው በዚያው ነበር፤ አመለካከታቸውን በተመለከተም እንዲገልጹላቸው አድርገው ነበር፤ ዳግማዊ ምኒልክ መጽሀፈ ሰዋሰው የተሰኘውን መጽሃፋቸውን ቀደም ብለው አንብበው ስለነበር በአለቃ ታዬ አለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ልህቀት ተደንቀው ነበር፤ ነገር ግን መንበራቸውን የሚያናጋውን የራስ ስዩም መንገሻ መሸፈት መፍትሄ የሚሰጡበት ወሳኝ ወቅት ስለነበር ሸዋ ከቤተ መንግስታቸው ዘንድ ቀጠሮ ይዘው ለጊዜው ደግሞ ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲመለሱ ሊደርስባቸው የሚችልን መገፋት ይጠብቃቸው ዘንድ ደብዳቤ አስይዘው ሸኟቸው፡፡ ደብዳቤው እንዲህ ይነበባል፦
ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ፤ አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም የሚባል ሰው ምጽዋ የነበረ፣ ሃይማኖቱን እኛ መርምረነዋልና ማንም አንዳች አይበለው በሃይማኖት ነገር።
በኅዳር 6 ቀን 1891 ዓ.ም በወረኢሉ ከተማ ተጻፈ።
አለቃ ታዬ በተለይም ከአጼ ምኒልክ ጋር መገናኘታቸው የመጠቀ መንፈሳዊና አለማዊ ዕውቀታቸውን ከቤተ መንግስት እንዲደርስ ያደረገ፣ ለታላላቅ ሹመት እንዲታጩ መንገድ የከፈተ ነበር፤ ወደ አውሮፓ የማቅናት ዕድል የተፈጠረላቸውም በዚሁ አጋጣሚ ነበር። በዚህም አጼ ምኒልክ የጀርመን መንግስት በበርሊኑ የኦሬንታል ጥናት ተቋም ግዕዝና አማርኛ የሚያስተምር ምሁር እንዲልክላቸው በጠየቁት መሰረት አለቃ ታዬ ወደ ጀርመን እንዲሄዱ ሆነ።
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መንግስታቸውን ካጠናከሩ በኋላ ትኩረት አድርገው ይሰሩባቸው ከነበሩ ተግባራት አንዱ በተለያዩ ወቅቶች ከኢትዮጵያ ተዘርፈው ወደ አውሮፓ አገራት የተወሰዱ ጥንታዊ መጻህፍትና ቅርሶችን ማሰባሰብ ነበር። ይህን ለማድረግ ይመቻቸው ዘንድ ደግሞ የመዛግብቱን ዝርዝር እንዲሁም የሚገኙበትን ሁኔታ ማጥናት ቅድሚያ አደረጉ፤ አጼ ምኒልክ ይህን ተግባር ያስፈጽሙላቸው ዘንድ ለአለቃ ታዬ የሚከተለውን ደብዳቤ ላኩ ።
ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ሥዩመ እግዚአብሄር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ይድረስ ከአለቃ ታዬ እንዴት ሰንብተሃል፤ እኔ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ በጀርመን አገር ሁሉ ይልቁንም ላይፕሲ በምትባል ከተማ ብዙ የኢትዮጵያ አሉ ማለት ሰምቻለሁ፡፡ የእኛ አገር የሚጠቅሙትን ስም ስማቸውን በቶሎ ጽፈህ እንድታስታውቀኝ ይሁን፡፡ ሀምሌ 18 1,ቀን 1898 ዓመተ ምህረት፤ አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ፡፡
አለቃ ታዬም በታዘዙት መሰረት በጀርመንና ፈረንሳይ አገራት የሚገኙ ሰባ አንድ ገደማ የሚሆኑ ጥንታዊ መጻህፍትን ዝርዝር መዝግበው በደብዳቤ ለንጉሰ ነገስቱ አሳውቀዋል፡፡ በግላቸውም አንድ መቶ ሰላሳ ያህል በጀርመን ይገኙ የነበሩ ጥንታዊ የብራና መጻህፍትን ወደ አገር ቤት መልሰዋል ።
አለቃ ታዬ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አጼ ምኒልክ ከልዩ ክብር ጋር ሹመት ሰጥተዋቸዋል፡፡ ብላቴን ጌታ ኀሩይ ወለደ ሥላሴ ‹‹የሕይወት ታሪክ››በተሰኘ መጽሐፋቸው ሁኔታውን ሲገልጹ፦
‹‹…… በጀርመን መንግስት ሦስት ዓመት ሙሉ ግእዝ ቋንቋ አስተምረው ኒሻን ተሸልመው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አፄ ምኒልክም ኒሻን ሸልመው ያባታቸውን አገር ሰጥተው ወደ በጌምድር ሰደዱዋቸው።››
በበጌ ምድር በአስተዳዳሪነት የመሾማቸው ዜና እንደተሰማ በመሳፍንቱና መኳንንቱ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ አስነሳ። በዳግማዊ ምኒልክ የተሰጣቸውን ጉልት ገሚሱን በኃይል በመንጠቅ ቀሪውንም ለመጠቅለል ያሰቡት ደጃዝማች መሸሻ ወርቄ ሀይማኖትን ሰበብ አድርገው ተነሱባቸው። በጊዜውም የቤጌ ምድር ገዢ ለነበሩት ንጉሥ ወ/ጊዮርጊስ “….አለቃ ታዬ ሃይማኖቱ የንስጥሮስ ነው ይህንንም ሃይማኖት ለሕዝቡ ያስተምራል” ብለው ጻፉላቸው፤ ንጉሥ ወ/ጊዮርጊስም ለአለቃ ታዬ ይህንን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ጻፉ፦
‹‹ይድረስ ለአለቃ ታዬ፣ እንደምን ሰንብተሃል? እኔ እግዚአብሄር ይመስገን ደህና ነኝ፡፡ ዝም ብለህ ተቀመጥ ሰንልህ እንደዚህ ያለ ትምህርት ከየት ያመጣኸው ነው?! ለምን ተጣላኝ እንዳትል!››
በ1903 ዓ.ም ኀዳር 24 ቀን ተጻፈ።
አለቃም ደብዳቤው እንደደረሳቸው ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሆኑን፣ ያለ አግባብ ግፍ እንደተፈጸመባቸው ለንጉሥ ወ/ጊዮርጊስ በመግለጽ የተወሰደባቸውን እርስት እንዲያስመልሱላቸው ጠየቁ፤ ንጉሱም ደጃዝማች መሸሻን አስጠርተው የወሰዱባቸውን ጉልት ለአለቃ እንዲመልሱላቸው ፈረዱ፤ ሁኔታው ያልተዋጠላቸው ደጃዝማች መሸሻም ነገሩን ከረር አድርገው፤ ጉዳዩን በወቅቱ የበጌ ምድር ጳጳስ ወደነበሩት አቡነ ማቴዎስ አደረሱ፤ ጳጳሱም ሸንጎ ጠርተው ሃሳባቸውን እንዲያስረዱ አዘዙ፤ ደጃዝማች መሸሻም ይህን አሉ፦
……..ለሥዕልና ለመስቀል አይሰገድም፣ በሞቱ ቅዱሳን አማላጅነት አያምንም፣ ዝክርና ምፀዋት የሞተ ሰውን ሊያጸድቅ እንደማይችል ይናገራል፣ የልማድ ጾም ዋጋ እንደሌለው ይሰብካል፣ ቀናትን አያከብርም፤ ሃይማኖቱ ፀረ ማርያም ነውና ሀገር መግዛት አይገባውም፤ አይደለሁም ካለም ሥዕለ ማርያም ይምጣና ይስገድ…… በማለት ከሰሱ፡፡
ሥዕለ ማርያም መጥቶ አለቃ ታዬ እንዲሰግዱ ሲታዘዙ (በዘጸአት 22፤ 1-5 ያለውን ክፍል ጠቅሰው) ለሥዕል መስገድ እንደማይገባ በማብራራት ምላሽ ሰጡ። በቀረቡባቸው ክሶች ላይ ከፍ ያለ ክርክር ከተደረገ በኋላ አለቃ ታዬን ለመርታት የሚያስችል በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ባለመኖሩ ጳጳሱ ከባልደረቦቻቸውና ከመኳንንቱ ጋር መክረው ለወደፊቱ ይህን ትምህርት እንዳያስተምሩ ገስጸው ለቀቋቸው።
በአለቃ ታዬ መለቀቅ የተበሳጩት ካህናት በጊዜው የአፄ ምኒልክ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ተሰማ ናደው በማመልከት ያለ ሕግ ወደ ወኅኒ ቤት እንዲገቡ አደረጉ፡፡ ከደጃዝማች ሙሉጌታ እና ከደጃዝማች ይገዙ ሀብቴ ጋር በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ ፡፡
የአገር ባለውለታ የሆኑት አለቃ ታዬ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ህልፈትን ተከትሎ በነበራቸው የሀይማኖት አስተምህሮ ልዩነት ሰበብ ልፋታቸውና ድካማቸው አፈር እንዲበላው ተፈርዶበት፣ ክብር ሲገባቸው ዕጣ ፈንታቸው ግን እስርና ግዞት ሆኖ ብዙ ሲሰቃዩ ቆይዋል፤ ነገር ግን ወግ አጥባቂ ያሆኑት ልጅ ኢያሱ ወደ ንግስና መንበሩ ሲመጡ ይደርስባቸው የነበረው ጫናም ሆነ እስር ጋብ አለ፡፡ ከልጅ ኢያሱ በኋላ የመንግስት ስልጣኑን በያዙት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እና ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ የአስተዳደር ወቅት ደግሞ የተሻለ ነጻነት አግኝተው ነበር። በተለይ ተፈሪ መኮንን የተሻለ ግንዛቤና ዕውቀት ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ወደ መንግስታቸው ስላቀረቡ አለቃ ታዬ በ1912 ዓ.ም የመንግስት አማካሪ ሆነው ተሾሙ፡፡
ከመንግሥት ኃላፊነት ተግባራቸው በተጓዳኝ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይም ተሳትፎ የነበራቸው አለቃ ታዬ በተለይም ለአማርኛ ቋንቋና ስነ ጽሁፍ ዕድገት መሰረት ካኖሩ ፋና ወጊ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ናቸው፤ በመንፈሳዊ፣ ታሪክ፣ የህይወት ታሪክ፣ ፍልስፍናና ስነ ምግባር ዘውግ የሚካተቱ በርካታ መጻህፍትንም አዘጋጅተዋል፡፡ ከሥራዎቻቸው መካከል፦
‹ስዕለ ኢየሱስ› (1886)፣ ‹ወንጌል ዘዮሀንስ› (1902)፣ ‹መዝሙረ ክርስቶስ፣ ወመልክዐ ኢየሱስ፣ ወመልክአ መድሃኔአለም›(1903) ‹የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ› (1920)፣ ‹መጽሀፈ ሰዋሰው›፣ ‹ፀወነ ነፍስ›፣ ‹መዝገበ ቃላት› ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በ1890 ዓ.ም ገደማ በኤርትራ፣ ምጽዋ ከተማ ለህትመት የበቃው መጽሐፈ ሰዋሰው የግዕዝ አቻ የአማርኛ ቃላት ፍቺን ጨምሮ የግዕዝ-አማርኛ ሰዋሰውን በአንድ ላይ ይዟል። ለረጅም ዘመናት የጽሁፍ ቋንቋ ሆኖ የቆየው ግዕዝ ቦታውን ለአማርኛ ቋንቋ ከለቀቀ በኋላ በግዕዘ ፊደላት የተከተቡ ጥንታዊያን መጻህፍትን ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ ስለነበር መጽሀፈ ሰዋሰው ይህን ችግር በትልቁ ያቃለለ ነው።
በ1920 ዓ.ም በአስመራ ከተማ የታተመው የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ አለቃ ታዬ በጀርመን አገር ቆይታቸው ወቅት የጻፉት እንደሆነ ይታመናል፡፡ መጽሐፉ ዳግማዊ ምኒልክ ስለኢትዮጵያ ታሪክ እንዲጽፉ ባዘዟቸው መሰረት የተጻፈ ሳይሆን እንዳልቀረ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ ‹የህይወት ታሪክ› በተሰኘው መጽሀፋቸው ጠቅሰዋል።
ሌላው የአለቃ ታዬ የስነ ጽሁፍ ትሩፋት ‹መዝገበ ቃላት› ይሰኛል፡፡ አንዳንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮችን የነቀፉበት ይህ ስራ ከባድ ውግዘት ያስከተለባቸው እንደሆነ ይነገራል፤ የህትመት ብርሃንም አላየም፡፡
‹ፀወነ ነፍስ› ጸሎትና መልካም ምግባርን የሚሰብክ፣ በተጨማሪም ድንግል ማርምን ክብር ያሳንሳል እያሉ ለሚኮንናቸው መልስ የሰጡበትም ጭምር ነው፡፡ በ182 ገጾች የተቀነበበው ይህ መጽሀፍ ‹ክብረ ድንግል› በሚለው አርዕስት ስር በ18 ገጾች ድንግል ማርያምን ያወድሳል።
አለቃ ታዬ ‹የጉዞ ማስታወሻ› የተሰኘች አነስተኛ ስራም አላቸው፡፡ ይዘቷም በአውሮፓ ጉዟቸው ባለፉባቸው አገራት እንዲሁም በጀርመን የተመለከቱትንና ያጋጠማቸውን የከተቡባት፣ በአውሮፓ አገራት የስልጣኔ ደረጃ የተሰማቸውን ስሜት፣ እንዲሁም ሀገራቸው ኢትዮጵያ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረች ትዝብታቸውን ያሰፈሩባት ናት።
አለቃ ታዬ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ አገራቸው ከስልጣኔ ማማ እንድትወጣ ሳይታክቱ የተቻላቸውን ከማበርከት ቦዝነው አያውቁም፤ የኋላ ቀርነታችን ምንጩ በህዝባችን ውስጥ ስር ሰደው የኖሩት አጓጉል ባህሎችና ልማዶች፣ ደካማ የስራ ባህልና ለለውጥ ያለን ፍላጎት አናሳ መሆን እንደሆነ ይጠቅሳሉ። በተለይም በጀርመን ሳሉ መፍትሄ የሚሉትን ለንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምኒልክ ሳይታክቱ በደብዳቤ ያሳውቁ ነበር፤ ‹Empress Tayitu and Menilek› የተሰኘውና አለቃ ታዬ ከአጼ ምኒልክ ጋር የተለዋወጧቸውን ደብዳቤዎች ከያዘው መጽሀፍ አንዱ ደብዳቤ እንዲህ ይነበባል፦
‹‹…….የአዳም ልጆች ዓለሙን ሁሉ የፈጠረ አድልዎ የሌለበትን አንድ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ላንዱ ወገን ሕዝብ ሙሉ ፣ላዱ ወገን ጎዶሎ ልብ አልፈጠረም፤በፍጥረቱም የአዳምን ልጆች ሁሉ አስተካክሎ እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፤ እንዲህ ከሆነ ስለምን የአውሮፓና የእስያ ሰዎች ከአፍሪካ ክፍልም ጥቂቶች ብልሃተኞች ሲሆኑ እኛ ሀበሾች መጽሐፍ ቢማሩ ኮቸር ለቃሚ . . .ብርና ወርቅ ቢሠሩ ቀጥቃጭ ቡዳ እንጨት ቢሠራ አናጢ እንጨት ቆርቋሪ . . . ቆዳ ቢፍቅ ጥንበ በላ ፋቂ እየተባለ ለሥራው ሁሉ ስም እየተሰጠ ስለሚሰደብ የጥበብ ሥራ ከጊዜ እየቀዘቀዘ ጠፋ፤ ስለዚህ ጉዳይ ጃንሆይ አስበውበት እንዲህ ያለው ስድብ ሁሉ ባዋጅ እንዲከለከል . . . ሰዎች እንዲያከብሩ ቢያደርጉ . . . በሌላ መንግሥት ስምና ምልክት የተቀረጸ ገንዘብ ከመገበያየት በጃንሆይ መልክና ስም የተቀረጸበትን ገንዘብ እንዲወጣ ቢያደርጉ ነጻ መንግስትም ራሱንም የቻለ የተሟላ ይሆናል።››
አጼ ምኒልክም ይህን የአለቃ ታዬ ምክር ቸል ብለው አልተውትም፤ ይህ ደብዳቤ ከደረሳቸው ከአራት ወራት በኋላ የትምህርትን አስፋላጊነት እንዲሁም የሥራን ክቡርነት ያካተተውን አዋጅ አወጁ፤ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችንም በአዲስ አበባና በሀረር ከተሞች አስገነቡ።
በዘርፈ ብዙ ዕውቀትና ክህሎት የሚደነቁት አለቃ ታዬ የነበራቸው ተራማጅ አስተሳሰብ እና የሃይማኖት አመለካከታቸው ከዘመኑ መኳንንትና መሳፍንት ጋር እንዳይስማሙ ያደረገ በመሆኑ ለአገራቸው መስራት የሚችሉበትን ዕድል ሳያገኙ ቀርተዋል። በእርግጥ ይህ በጣም የሚያስቆጭ ነው። ከአለቃ ታዬ ጋር አንድ ዘመን የሚጋራው ኢትዮጵያዊው ምሁር ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ› በተሰኘው መጽሃፉ ይህን ቁጭቱን ገልጾ ነበር፤ እንዲህ ሲል፦
‹‹……..እስከ ዛሬ ሰ,ድረስ ሳይወዱ ሩቅ አገር ተሰደው ወይም (ወደ ኢትዮጵያ) ከሚመጡ ፈረንጆች ጥቂት ተምረው ያገራቸውን መንግስት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችን ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክ፣ መናፍቃን የሌላ መንግስት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ፣ ሲከሰሱም እናይ የለምን? የነዚያን መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቁጠር? የሚከተሉት የሁለት ሰዎች ስም ግን እንዲወሱ የግድ ነው፡፡ እነሱም ከንቲባ ገብሩና አለቃ ታዬ ናቸው፡፡ ሶስት ኣመት ሙሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ እንደነዚህ ሁለት ሰዎች አድርጎ መንግስቱን የሚወድ አላየሁም፡፡ ይህ ደግነታቸው ግን እስከዛሬ ድረስ አልታወቀላቸው ይመስለኛል፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የነሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጵያ መንግስት ለወዳጁ አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቆርጣልና፡፡››
መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የ20ኛው ክ/ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሃፋቸው አለቃ ታዬ የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታይ አልነበሩም ቢሉም የዘመኑ መሳፍንትና መኳንንት በሚያናፍሱባቸው ወሬ ምክንያት አስከሬናቸው እንኳ ማረፊያ እንዲያጣ ሆኖ ተንገላቷል፡፡ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ጣልቃ ገብተው አስከሬናቸው በመካነ ስላሴ ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ የሀይማኖት መሪዎቹን ቢጠይቁም አልሆነላቸውም ነበር፡፡ ሁኔታውን በቅርብ የሚያውቁት አለቃ ክንፈ የተባሉ ሰው በግል ማስታወሻቸው እንዲህ አስፍረዋል፡-
‹‹…..ነሀሴ 15 ሀሙስ ቀን የቡርስታንት ዋና ተከራካሪ የነበሩ የአለቃ ታዬ ሞቱ፤ ከስላሴ እንቅበር ቢሉ፣ ወገናችን አይደለምና አናስቀብርም አሉ፡፡ ከንግስትም ቃል ቢመጡ በጭካኔ እምቢ ብለው ከለከሉ፡፡ በኦቶሞቢል ወስደው ጉለሌ ከካቶሊክ መቃብር ቀበሯቸው፡፡››

አስተያየት ያስቀምጡ