ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

የመደመር ጽንሰ ሃሳብ እና አካታች ካፒታሊዝም (Inclusive Capitalism) በዛሬይቱ ኢትዮጵያ

ሀብታሙ ግርማ (በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር)

መግቢያ

አንድ አመት ተኩል ዕድሜ ያስቆጠረው የአገራችን ሁለንተናዊ ማሻሻያ ጅምር ከሚተችባቸው ነጥቦች አንዱ ለውጡን ለመምራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ (roadmap) የለውም የሚል ነው፡፡ የለውጡ አመራሮች የለውጡ መዘውር የመደመር መርህ መሆኑን ቢናገሩም ይህ የመደመር እሳቤ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ገጽታዎች በተብራራ መልኩ ሳይቀመጥ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለመደመር ፍልስፍና መጽሃፍ እያዘጋጁ እንደሆነ ከመነገሩ ውጪ ቢያንስ ህዝብ የሚያውቀው ሰነድ እስካሁን የለም፡፡ ነገር ግን በዚህ መጣጥፍ ጸሃፊ እምነት የዶ/ር አብይ አህመድ ያለፉት 18 ወራት የስልጣን ጊዜ የአመራር ፍልስፍና እና ያከናወኗቸው መንግስታዊ ተግባራትን ከገመገምን የአመራር መርሃቸው የሆነው የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ርዕዮተ ዓለማዊ መሰረት እንዳለው፣ ይህም አካታች ካፒታሊዝም እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ለመሆኑ የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ምንድነው? ከተለምዷዊው ካፒታሊዝም (conventional capitalism) የሚለየው በምንድነው? ይህ መጣጥፍ ለእነዚህ እና ተዛማጅ ጉዳዮች መልስ ያፈላልጋል፡፡

የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ምንነት እና ግቦች

አካታች ካፒታሊዝም የህዝብን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ምግባራዊ ጉድለቶችን ለማስተካከል መንግስት ፣ የግሉ ዘርፍ እና ማህበረሰቡ በጥምረት የሚሰሩበትን ምጣኔ ሀብታዊ (economic)፣ ፖለቲካዊ (political)፣ ማህበረሰባዊ (sociological)፣ ስነ ባህላዊ (anthropological)፣ ስነ ምግባራዊ እና ሞራላዊ (ethics and moral) አስተምሮችን ባንድ ያቀፈ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በ1947 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በአገረ አ,ሜሪካ urban Land Institute በሚል ርዕስ በታተመ አንድ ሰነድ ላይ ነው፡፡ በቅርብ አመታት አለን ሃሞንድ እና ፕራህላድ የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብት በምርምር ስራዎቻቸው የአካታች ካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ በስፋት እያዲተዋወቅ ያደረጉ ናቸው፡፡ የአካታች ካፒታሊዝም መነሾዎች ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ድህነት እና የማህበራዊ ፍትህ እጦት የጅምር ካፒታሊስት አገራት መሰረታዊ ችግሮች ናቸው የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው በኢኮኖሚ ስርዓቱ የግል ዘርፉ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም (ለአብነት ያህል በድህነት አዘቅት ውስጥ የሚማቅቁ ዜጎችን፣ ሴቶችን) ማገዝ እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡ በመሰረቱ አካታች ካፒታሊዝም አላማው ተለምዷዊው ካፒታሊስት ስርዓት (conventional capitalist system) የሚያመጣውን የኢኮኖሚ ፍትህ እጦትና የሚስከትለውን ማህበራዊ ቀውስ ለማርገብ ነው፡፡ የማህበረራዊ ተጠቃሚነት እና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ዋነኛ የኢኮኖሚው ዘርፍ ግቦች ናቸው፡፡ በመሆኑም የግልም ሆነ የመንግስት ተሳትፎ ይህን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በአካታች ካፒታሊዝም አስተምህሮ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻውን ዜጎች በህይወታቸው ትርጉም እንዲገኙ አያደርግም፣ በመሆኑም ማበረሰባዊ፣ ባህላዊ፣ መንፈሳዊ ጉዳዮችም ከኢኮኖሚ ህይወታቸው የተነጠለ ሳይሆን እንዲያውም የተጎዳኘ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ የአካታች ካፒታሊዝም ግብ የኢኮኖሚ እድገት ዘላቂ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ለዜጎች መንፈሳዊና ቁሳዊ ልማት ትኩረት አድርጎ ይሰራል፡፡

የአካታች ካፒታሊዝም ከተለምዷዊ ካፒታሊዝም የሚለየው በምንድነው?

የካፒታል ክምችት እና ሃብት ማፍራት ተለምዷዊ ካፒታሊዝም ዋነኛ ግቦች ናቸው፡፡ በመሆኑም ማህበራዊ ፍትህ በዚህ ሂደት ሊቀረፍ የሚችል፣ ዋነኛ የኢኮኖሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚው ዘርፍ መርህ በነጻ ገበያ መርህ ይመራል ፤ የኢኮኖሚው ባለድርሻዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በግለኝነት እና ፉክክር ጽንሰ ሃሳብ ይመራሉ፡፡ የአካታች ካፒታሊዝም ከተለምዷዊው ካፒታሊዝም የሚለየው ዋናው ሰብዓዊ ተጠቃሚነትን ዋናው ምሰሶው ማድረጉ ነው፡፡ በተለምዷዊው ካፒታሊዝም ዋነኛ የኢኮኖሚ መዘውር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሲሆን በአካታች ካፒታሊዝም የግል እና የመንግስት ክፍለ ኦኮኖሚ በጥምረት እና በቅንጅት የሚሰሩበት ነው፡፡ ተለምዷዊው ካፒታሊዝም መሰረቱ በፉክክር እና በነጻ ገበያ የተመራ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተሻለ የኢኮኖሚ ብልጽግና መጣል የሚል ነው፡፡ የገበያ መጓደል (market failure) ሲጋጥም ራሱ ገበያ ይፈታዋል የሚል ነው፡፡ የአካታች ካፒታሊዝም መነሻ የገበያ መጓደል (market failure) እና የመንግስት መጓደሎች (Government failure) የፈጠሩትን ማህበረሰባዊ ሚዛን መዛባትን (social imbalance) ማስተካከል ነው፡፡ በዚህም በገበያ የማይፈቱ የገበያ ጉድለቶችን መንግስት ይፈታል፤ በመንግስት መጓደል የሚከሰቱ ችግሮች ሲከሰቱ ገበያው (የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ) ይፈታዋል፡፡ የማህበረሰቡ ስነ ምግባራዊና ሞራል መዛባት ለማስተካከል ደግሞ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ተቋማት ከመንግስት እና ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር በጥምረት ይሰራሉ፡፡

በአካታች ካፒታሊዝም የግለኝነት አስተሳሰብ እና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሚና

በመሰረቱ የካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ መነሻ (micro foundation) የሰው ልጅ የስነ ልቦና ውቅር ነው፡፡ የሰው ልጅ በህይወት እንቅስቃሴው ሁሉ (ለኢኮኖሚያዊ ስኬቱም ሆነ ውድቀቱ) የውሳኔው ውጤት ነው፡፡ በውሳኔው ሂደት ደግሞ የፉክክር እና የትብብር ስሜቶች የተለያየ ውጤት (የተጽዕኖ ደረጃ) ቢኖራቸውም የፉክክር ስሜት ግን በተጽዕኖውም ሆነ የውሳኔውን ውጤት በመወሰኑ ረገድ የጎላ ነው፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ በኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎቹ ሁሉ የግል ዓላማውን ለማሳካት በፉክክር መንፈስ ይመራል፡፡ የዚህ አስተምህሮ መሰረት በተብራራ ሁኔታ ያስቀመጠው እንግሊዛዊው የምጣኔ ሃብት ሳይንቲስት አዳም ስሚዝ ነው፡፡ አዳም ስሚዝ በ 1776 ዓ.ም (እ.ኤ..አ) ‘An Inquiry into the Nature and Cause of Wealth of Nations’ በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ እንዳሰፈረው የፉክክር መንፈስ የሰው ልጅ የብልጽግናው መሰረት ነው፤ የሰው ልጅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በፉክክር መንፈስ የሚመራ ከሆነ ለኢኮኖሚ ብልጽግና ቁልፍ የሆኑት የስራ ክፍፍል (division of labor)፣ የቁጠባ ባህል (saving culture)፣. ለፈጠራ እና ራስን ለመለወጥ መጣር (innovative mindsets and zeal for self-development) የመሳሰሉትን እሴቶችን ያዳብራል፡፡ የፉክክር መንፈሱ አይሎ መቀማማትን እንዳያስከትል፣ ማለትም ከልክ ያለፈ ግለኝነትን (greed) እንዳይኖር የገበያ ሃይል የራሱ የማረሚያ ስርዓት (corrective mechanism) አለው፡፡ አዳም ስሚዝ ይህን የማይታየው የገበያ ሃይል (invisible hand of the market) ይለዋል፡፡ በኢኮኖሚ ህይወታቸው ከልክ ያለፈ ግለኝነት (greedy behavior) ባህሪ ያላቸው ግለሰቦች (የቢዝነስ ሰዎች) ሃላፊነት በማይሰማቸው መልኩ መንቀሳቀሳቸው አደጋው ለራሳቸው ነው፤ የገበያ ሃይል ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን በሚነካ መልኩ ቅጣት ስለሚጥልባቸው እንዲታረሙ ይገደዳሉ፡፡ በተለምዷዊው ካፒታሊዝም ስርዓት የመንግስት ሚና ይህ የገበያ ሃይል ስራውን እንዲከውን ምቹ ተቋማዊና ህጋዊ ማዕቀፍ ማበጀት፣በኢኮኖሚ ስርዓቱ ውስጥ የገበያ መርህ መተግበሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የገበያ ልማትን ማፋጠን፣ የገበያ ስርዓት መርህን የሚጥሱ ይፋዊም ሆነ ድብቅ የኢኮኖሚ አደረጃጀቶችም ሆነ አካሄዶችን መከታተል፣ መቆጣጠር እና እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በተለምዳዊው ካፒታሊዝም የሚያነሳው የሰው ልጅ የፉክክር መንፈሱ ከትብብር መንፈሱ አይሎ ይገኛል የሚል እሳቤ ስላለው የኢኮኖሚ ሃልዮትም ሆነ ተዛማጅ ፖሊሲዎቹ ፉክክርን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው አካታች ካፒታሊዝም የሰው ልጅ በአጠቃላይ የህይወት መስመሩ በተለይም በኢኮኖሚ ህይወቱ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ለውሳኔው መነሻም ሆነ መድረሻ የሚሆነው ፣ ማለትም የፉክክር እና የትብብር ዝንባሌዎች ተጽዕኖዎች አሉበት የሚል ነው፡፡የኢኮኖሚ አስተሳሰቦቹም ሆነ እና ፖሊሲዎች የዚሁ ስነ ልቦናዊ ውቅር ነጸብራቆች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሰዎች በኢኮኖሚ ህይወታቸው በውሳኔዎቻቸው ሁለቱንም ሃይሎች ከግምት ያስገባሉ፡፡ ከዚህ የምንወስደው ነገር የግለኝነት አስተሳሰብ ግለሰባዊ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም በመስጠትም ውስጥ ይኖራል የሚል አመክንዮ አለው፡፡ ከዚህ አንጻር የሰው ልጅ ለሌሎች ጥቅም ዋጋ መክፈልን (altruism) ምክንያታዊ ማድረግ ያሻል የሚል እምነት በመያዙ የጥንታዊው ግሪክ ስልጣኔ ዘመን የነበረውን የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች መነሻዎችን ይጋራል፡፡ የዘመኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፈላስፋ የነበረው አርስቶትል የግለኝነትን ዝንባሌ (individualistic motive) ጽንሰ ሃሳብን ሲያብራራ ለሌሎች ጥቅም በማሰብ (altruistic motive) እና በግለኝነት ዝንባሌዎች ተጻራሪ አይደሉም፤ ይልቁንም ለሌሎች ጥቅም ማሰብ ምክንያታዊ ግለኝነት (rational selfishness) ነው ይለዋል፡፡ አርስቶትል ለዚህ አስረጅ የሚያደርገው የሰው ልጅ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች የህይወት መስመሮቹ ከውሳኔዎቹ ጀርባ ቁሳዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እርካታ መሻት ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ለሌሎች ጥቅም የግል ፍላጎትን መገደብ በራሱ ግለኝነት ነው፤ ምክንያቱም የመንፈሳዊ እርካታን ያስገኛልና፡፡ አካታች ካፒታሊዝም ሰዎች በኢኮኖሚ እንቅስቃሴቸው በግል ታጥረው ከሚጓዘው በጋራ ቢንቀሳቀሱ የተሸለ ማህበረ ኢኮኖሚ ብልጽግና ላይ ይደርሳሉ የሚል አስተምህሮ አለው፡፡

በአካታች ካፒታሊዝም የመንግስት ሚና

በአካታች ካፒታሊዝም መንግሥት ከላይ የተጠቀሱት ግቦች እንዲሳኩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የመንግስት ሚና በዚህ በኩል ማህበረሰቡን የትብብር እና የአብሮ መስራትን መረዳዳትን እሴቶች የሚያጠነክሩ ተግባራትን እና ተቋማት የመገንባት፤ የማጠናከር ሚና አለው፡፡ በቀጥታ በኢንቨስትመንት እና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች ከሚያደርገው ኢንቨስትመንት በተጨማሪ የህብረተሰቡን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ወይም የቁሳዊ እና መንፈሳዊ ደህንነነቱን የሚያሳድጉ የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን እና ማበረታቻዎች ያዘጋጃል፡፡ በመሆኑም ዜጎች አቅማቸውን ያህል የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ እንዲሰማሩ ያስተምራል፤ የቢዝነስ ሰዎች ደግሞ ከትርፋቸው ለማህበራዊ ሃላፊነት የሚወጡትን እንዲያሳድጉ ይመክራል፡፡ የመንግስት የመሰረተ ልማት ግንባታ አስፈላጊነት መነሾም የማህበረሰቡ ትርጉ ለው የህይወት መሻሻል እንዲሳይ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስራ አጥነትን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን የተፈረጠረው ስራ የሰራተኞችን የስራ ደህንነት እና ዋስትና የሚያረጋግጥ፤ ለኑራቸው በቂ መሆኑን ማረጋገጥ፤ በመንግስት ዘርፍ ደግሞ የማህበረ ኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶች ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት ከማስፈን ባለፈ የእያንዳንዱን ህዝብ ኑሮ የሚሻሽሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያሻል፡፡ ለምሳሌ የቤት ልማት ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ከባቢው ለኑሮ ምቹ ማድረግ፤ የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የትምህርት ከባቢው ለመማር ምቹ እንዲሆን መስራት፤ የጤና ተቋማት ከመገንባት በተጓዳኝ ህብረተሰቡ ሊጠብቅባቸው የሚችሉ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥራዊ ዘዴዎችን ማላመድ፣ ማስተማር፣ ማስረጽ ያስፈልጋል፡፡ ለአብነት የአመጋገብ ስርዓቱን እንዲለውጥ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ህብረተሰባዊ ባህል እንዲሆን መስራት፤ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና አረንጋዴ ልማት ናቸው፡፡ የማህበራዊ ሰላምን ከመጠበቅ አካያ የህዝብ ደህንነትን በፖሊሳዊ እና በደህንነት መዋቅር ከማጠናከር ጎን ለጎን የግጭት መንስዔ የሆኑ ልዩነቶች በውይይት የሚፈቱበትን ሃገር በቀል ተቃማትን ማጠናከር፣ የተለያዩ ህብረተሰባዊ አደረጃጀቶች ካሉ ማጠናከር፣ ከሌሉ ደግሞ እንደፈጠሩ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የህዝብን ስነ ምግባር እና ሞራል የሚያንጹና እንደ ሃይማኖት ተቋማት፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቶችን እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት እንደነዚህ አይነት ህዝባዎ ፋይዳ ላቸው ተግባራት እና ስነምግባር እሴቶችን እንዲጎለብቱ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ ያደራጃል፤ ዜጎችን ማህበረሰባዊ ፋይዳ ባላቸው በጎ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ከመቀስቀስ ባለፈ የተለያዩ ማበረታቻዎችም ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ የግል ባለሃብቶች እና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ማህበረሰባዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፎች እንዲሳተፉ ከመቀስቀስ ባሻገር፣ የተለያዩ የማበረታቻ ድጋፎች መስጠት አንዱ ነው፡፡ ሌላው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተደራጀ እና በቅንጅት ለማህበረሰቦች እንዲደርስ የማስተባበር ሚና መጫወት እንደ አንድ የመንግስት ተግባር በመውሰድ የቢሮክራሲው አካል ያደርጋል፡፡ በአካታች ካፒታሊዝም ሌላው የመንግስት ሚና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች እና የበጎ ፍቃድ የሚሰጡ ዜጎች በተለያዩ የዜግነት እና ማህበራዊ መንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው፡፡ እንግዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል በኢትዮጵያ ስልጣኑን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ እያከወናቸው ያሉ መንግስታዊ ተግባራት ፍኖተ ካርታ የላቸውም የሚለው እምብዛም አያስኬድም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚከተሉት የመደመር ፍልስፍና (መርህ) እንደሆነ ስልጣን ከያዙበት ማግስት ጀምሮ ቢገልጹም ለዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ መነሻቸውን እስካሁን ይፋ ባያደርጉም ከከተሉት የአመራር ፍልስፍና እና የእስካሁ ተግባራቶቻቸው የሚነግረን የአካታች ካፒታሊዝም አራማጅ መሆናቸውን ነው፡፡

ቸር እንሰንብት !!!


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading