ሀብታሙ ግርማ
ነሐሴ 30 ቀን፣ 2011 ዓ.ም
ጅግጅጋ፣ኢትዮጵያ
መግቢያ
የ 2011 ዓ.ም የኮሌጅ መግቢያ ውጤት ከታወቀበት ሀምሌ መጨረሻ ቀናት ጀምሮ እስካሁን ለአንድ ወር ያህል እንዳወዛገበ ቆይቷል፡፡ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ለውዝግቡ መቋጫ የሚሆን መግለጫ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የክልላዊ መንግስታት ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም ለህብረተሰብ ሳይንስ (Social Science) መስክ ተፈታኞች ጂኦግራፊ፣ ለተፈጥሮ ሳይንስ (Natural Science) መስክ ተፈታኞች ደግሞ የፊዚክስ የትምህርት ዓይነቶች ብቻ በልኬት ስሌት ውስጥ እንደሚገቡ፤ በመሆኑም ለሁለቱም የሳይንስ መስክ እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ እና ጠቅላላ ዕውቀት (Scholastic Aptitude Test) የትምህርት ዓይነቶች ይወሰዱና በጠቅላላው ከአራት መቶ (400) ተደምሮ የሚገኘው አዲሱ የውጤት ልኬት ነው፡፡
የመንግስት የትምህርት አካላቱ በሰጡት መግለጫ ይህ ቀመር ያስፈለገው በሌሎቹ የትምህርት መስኮች የታየው የተጋነነ ውጤት መስተዋል ነው ቢሉም ይህ ለተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው ምክንያትም ሆነ መልስ የሚሆን አይመስልም፡፡ ከዚህ ይልቅ የተደረገው የውጤት መግለጫ ለውጥ ተፈታኝ ተማሪዎቹ በቀድሞው ስሌት ያገኙት ነጥብ ከአዲሱ ቀመር ስሌት ውጤታቸው አንጸር በማነጻጸር የሚያነሱት ጥያቄ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህም ‘አዲሱ ስሌት ከቀድሞው አንጻር ትርጉም ያለው ተፈታኝ ቁጥር ኮሌጅ የመግባት/ አለመግባት ሁኔታን የመቀያየር ሁኔታን ይፈጥር ይሆን?’ የሚል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ለዚህ እርግጠኛ መልስ ለማፈላለግ ቢያንስ የሁሉም ተፈታኞች ውጤትን ማወቅ ይጠይቃል፡፡
ይሁንና በግርድፉም ቢሆን እያንዳንዱ ተማሪ ከራሱ አንጻር በአዲሱ ስሌት (ከ 400 የታረመው ለማለት ነው) እና በቀደመው ስሌት(ከ 700 የታረመው ለማለት ነው) መሰረት የሚኖርን የውጤት ልዩነት በማየት ተቀራራቢ መልስ ማግኘት ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህም ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸው ከአዲሱ አንጻር አቻ ግምት በመቀመር ነው፡፡
ለዚህ ቀመር የስነ ልኬት (Measurment) ባለሙያዎች የራሳቸው ስታትስቲካዊ ስሌት እንደሚኖራቸው እሙን ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ ከላይ የተነሳው ጉዳይ ምላሽ የሚያገኝበት፣ ቤት ያፈራውን ቀመር ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡
ተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው በዚህ ወቅት ሊኖሩበት የሚችለውን ውጥረት (tension) በመገመት ይህ አጭር ጽሁፍ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ያፈላልጋል፦
ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸው ከአዲሱ ቀመር ስሌት ውጤታቸው አንጻር የሚኖረው አቻ ግምት ምን ያህል ነው?
አዲሱ ቀመር የተማሪዎችን ውጤት ምን ያህል ይቀይረዋል?
በአዲሱ ስሌት መሰረት የኮሌጅ የመግቢያ መቁረጫ ነጥብን መገመት ይቻላል?
አንባቢም ሆነ ተፈታኝ ተማሪዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር……
በቅድሚያ አንባቢያን እንዲገነዘቡ የምፈለገው ከዚህ በታች በጽሑፌ ያስቀመጥኩት ግርድፍ ሂሳባዊ ስሌት እንጂ ስታስቲካዊ አይደለም፡ የተሸለ እርግጠኝነት ያለው ስሌት በስታትስቲካዊ መሣሪያ (Statistical tool) ይገኛል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሂሳባዊ ስሌቱ (Mathematical Result) ከስታትስቲካዊ ስሌቱ እምብዛም ይርቃል ማለት አይደለም፡፡
ተማሪዎች ሊገነዘቡ የሚገባው ነገር የፈተናውን ጉዳይ ፖለቲካዊ ቅርጽ ሰጥተው ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት የሚጥሩ አካላት (ቡድኖች) ሊኖሩ እንደሚችሉ አውቀው የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የፈተና ውጤት መግለጫ ቀመር መለየቱ ውጤታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥታል ወይ የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ይዘው በምክንያት መመርመር ነው ያለባቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አላማም ተማሪዎች ይህን ግንዛቤ ወስደው ነገሩን በምክንያት እንዲመረምሩ መነሻ ይሆን ዘንድ ነው፡፡
ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸው ከአዲሱ ቀመር ስሌት ውጤታቸው አንጻር የሚኖረው አቻ ግምት ምን ያህል ነው?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የቀደመው ውጤታቸውን ወደ አራት መቶ መቀየር አለባቸው፤ ለዚህም የመቀየሪያ ክፋይ (conversion factor) 400/700 (0.5714) ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸውን በ 0.571 ማብዛት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ቀድሞ ከ700 በታረመው መሰረት 356 ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ ከ400 የታረመው አቻ ውጤት (equivalent result) 203 ገደማ ነው፡፡
በመሆኑም ሰባቱም ትምህርት ቢያዝ ወይም በአዲሱ ውጤት አለካክ ልዩነቱ ምን ያህል ነው?
አዲሱ ቀመር ያገኙት ውጤት ታሳቢ የሚሆነው ከላይ የተገለፁት የአራት ትምህርቶች ውጤት ድምር ከአቻ ውጤት ውጤት አንጻር የቁጥር (absolute) ልዩነት ወይም ፐርሰንታዊ (percentile) ልዩነት ማስላት ይችላሉ፡፡
አዲሱ ቀመር የተማሪዎችን ውጤት ምን ያህል ይቀይረዋል?
ለምሳሌ ከ700 በታረመው መሰረት 356 ውጤት ያመጣ/ች ተማሪ አዲሱ ቀመር ውጤቱን ምን ያህል ቀይሮታል?’ ለሚለው መልሱ፡-
በቅድሚያ ከአራት መቶ (400) የታረመው አቻ ውጤት (equivalent result) ማግኘት፡፡ ለዚህ ደግሞ 356 በ 0.571 ማብዛት ፡፡ ውጤቱም 203 ገደማ ይሆናል፡፡
እንበልና ይህ/ች ተማሪ በአዲሱ ልኬት መሰረት በአራቱም የትምህርት ዓይነቶች ያስመዘገበው 196 ነው፡፡ ስለዚህ አዲሱ ልኬት ከአቻ ውጤቱ አንጻር ያለው የውጤት ልዩነት (በፐርሰንት) ሲሰላ፡- -3.5% ነው።
በመሆኑም ይህ ተማሪ አዲሱ ውጤት አለካክ ከቀደመው አለካክ አንጻር ውጤቱን በ3.5 ፐርሰንት ቀንሶታል ማለት ነው፡፡
በአዲሱ ስሌት መሰረት የኮሌጅ የመግቢያ መቁረጫ ነጥብን መገመት ይቻላል?
በመሰረቱ ለዚህ ጥያቄ የቀደመው አለካክ ስሌትም እንካ መልስ የለውም፡፡መልሱ ከአጠቃላይ የተማሪዎች ውጤት እና ከዩኒቨርሲች የመቀበል አቅም አንጻር ይወሰናል፡፡ ለአንዳንድ ተፈታኞች (ለሴቶች፣ በታዳጊ ክልል ለተፈተኑ፣ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች) የሚሰጥ ልዩ ድጋፍም ታሳቢ ይደረግ፡፡ ስለዚህ እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡
ነገር ግን እንደ አጠቃላይ የኮሌጅ ቅበላ ዝቅተኛ ነጥብ (ይህ በመንግስት ድጎማ በዩኒቨርሲቲ የሚማሩትን ማለት አይደለም) ግምታዊ ስሌት ለመስጠት እንችል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አምና በነበረው የኮሌጅ የቅበላ ዝቅተኛ ነጥብ (ከ 700) 295 ነበር፤ ይህ ከዘንድሮው ስሌት አንጻር አቻ ግምቱ ምን ያህል ይሆናል ብለን ብንጠይቅ መልሱ 295 በ 0.5714 በማብዛት የምናገኘው ውጤት ነው፡፡ ይህም 169 ገደማ ይሆናል፡፡ የዘንድሮ የኮሌጅ የቅበላ ዝቅተኛ ነጥብ በቀደመው አለካክ (ከ 700 በሚታረም) 300 ቢሆን፣ በአዲሱ የውጤት መግለጫ መሰረት የሚኖር አቻ ውጤት 171 ገደማ ነው ማለት ነው።
በመጨረሻም ለተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው መልካሙን እንዲገጥማቸው ምኞቴ ነው

አስተያየት ያስቀምጡ