ልብ ወለድ፣ የተውኔት ድርሰት እና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ (1850-1960ዎቹ)
Novel, Play and Journalism in Ethiopia (1850-1960’s)
ሀብታሙ ግርማ ደምሴ ሐምሌ 2011 ዓ.ም ጅግጅጋ፣ ኢትዮጵያ
Author of the Book Habtamu Girma
ሁለተኛ ዕትም በገበያ ላይ!
This book is Available for sale on:
ethiomereb.com or http://www.lulu.com/shop/habtamu-girma-demiessie/ethiopian-literary-giants-and-their-works-novel-play-and-journalism-in-ethiopia-1850s-1960s/paperback/product-24187792.html
ስለ መጽሐፉ አጠቃላይ
የመጽሐፉ ርዕስ፦ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች እና ሥራዎቻቸው
ንዑስ ርዕስ፦ ልቦለድ፣ የተውኔት ድርሰት እና ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ (1850-1960ዎቹ)
ደራሲ፦ ሀብታሙ ግርማ
ግምገማ፦ ሚለር ተሾመ (በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር)
የገጽ ብዛት፦ 319
የመጽሐፉ መጠን (ኢንች)፦ ወርድ 6 ፣ ቁመት 9
ኮፒ ራይት፦ የኢፌዲሪ የአእምሮ ንብረት ጽ/ቤት፣ 2008 ዓ.ም
ስለመጽሐፉ አጭር ግምገማ (ሚለር ተሾመ፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር)
ይህ መጽሐፍ ኢትዮጵያዊ ብዕረኞች በጸሐፊነት፣ በጋዜጠኝነት እና በተለያዩ መንግስታዊ ሹመቶች በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ ጋዜጠኝነት እና አስተዳደራዊ ታሪክ ያበረከቱትን ፈርጀ ብዙ ሚና ያሳያል፡፡ በዋናነት የጸሐፊነት እና የጋዜጠኝነት ጣምራ ተግባር በየዘመኑ ማህበራዊ-ፓለቲካዊ አውድ ያሳረፈውን ተጽዕኖ በጸሐፍቶቻችን ግለ-ታሪክ አጮልቀን እንድናይ ይረዳናል፡፡ በግለ-ታሪኩ የተካተቱት ጸሐፍት መብዛታቸው እና በተደራጀ መረጃ የተዋቀረ መሆኑ መጽሐፉን ልዩ ያደርገዋል፡፡ በውስጡ የሀገራችን ዘመናዊ የሥነ ጽሑፍ እና የጋዜጠኝነት ሙያ የታሪክ ቅኝት ተካቷል፡፡መጽሐፉ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ የጸሐፊነት እና የጋዜጠኝነት ሙያ ፈርጦችን ማወቅ፣ መመራመር እና ማጎልበት ለሚሹ ትጉዋን የምስራች ነው፡፡
ማውጫ (Content)
ክፍልአንድ፦ ሥነ ጽሁፍ በኢትዮጵያ
1.1.የኢ-ልቦለድ እና ልቦለድ ሥነ ጽሑፍ በኢትዮጵያ
1.2.የተውኔት ድርሰት በኢትዮጵያ
1.3.ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ
1.3.1.የህትመት ሚዲያ አጭር ቅኝት
1.3.2.የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አጭር ቅኝት
1.4.የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሁፍ ጥናትጨበኢትዮጵያ
1.5.የኢትዮጵያ መሪዎች እና መጻህፍቶቻቸው
ክፍልሁለት፦ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን የስነ ጽሁፍ ሰዎች አጫጭር የህይወት ታሪክ
አለቃ ታዬ ገብረማርያም፣ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፣ ፊት አውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ፣ ከበደ ሚካኤል፣ አሀዱ ሳቡሬ፣ መንግስቱ ለማ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ አቤ ጉበኛ፣ ነጋድራስ አፍወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፣ ሮማነወርቅ ካሳሁን፣ ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ፣ ኢዩኤል ዮሀንስ፣ ነጋሽ ገብረማርያም፣ ብላቴንጌታ መርስኤሀዘን ወልደቂርቆስ፣ ስንዱ ገብሩ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ መስፍን ሀብተማርያም፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ በዓሉ ግርማ፣አያልነህ ሙላት፣ ስብሐት ገብረእግዘአብሄር፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ማሞ ውድነህ፣ ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ ሀይሉ ገብረዮሐንስ(ገሞራው)
መቅድም (Preface)
ሥነ ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ literature የሚለው አቻ የአማርኛ ቃል ነው። የተጻፈ ነገር ሁሉ ሥነ ጽሑፍ ነው ማለት አይቻልም። ሥነ ጽሑፍ የገሃዱን ወይም የምናባዊውን አለም ሁነቶችን በጽሑፍ ወይም ሥነ ቃል በጥበብ መግለጽ ማለት ነው። ሥነ ጽሑፍ ልቦለድ፣ ሥነ ግጥም፣ የተውኔት ጽሁፍ እና ኢ-ልቦለድ በሚል በአራት ዘርፎች ይከፈላል። ምናባዊ ትርክት (Imaginative Literature) ልቦለድ፣ ሥነ ግጥም እና የተውኔት ድርሰት ያካትታል። በኢ-ልቦለድ (Non-fiction) ዘርፍ የሚካተቱ የሥነ ጽሁፍ ውጤቶች የዜና ዘገባ (News Reports)፣ የዳሰሳ ጽሁፍ (feature article) ፣ የግለ ታሪክ (biography) ፣ የታሪክ ዘገባ (historical accounts) ሊሆኑ ይችላሉ።
ሥነ ጽሑፍ ከጥበባዊ ፋይዳዋ ባለፈ በየዘመኑ የህዝብን አኗኗር፣ አስተሳሰብ፣ ባህልና ወግ፣ በአጠቃላይ የማህበረ ፖለቲካ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ሁነቶችን ከትባ ለትውልድ የምታስተላልፍ የታሪክ ማህደር ጭምር ናት። በአጠቃላይ ሥነ ጽሑፍ ህዝብን ከማሳወቅና ከማንቃት የማይተካ ሚና አላት።
ስለሆነም መንግስት የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ልማት ከሌሎች ልማቶች እኩል ትኩረት መስጠት ያሻዋል። ከዚህ አንጻር ህዝብ የመጻፍና የማንበብ ክህሎት ብቻ ሳይሆን ልምድም ጭምር እንዲያዳብር ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው። ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ <መንግስትና የህዝብ አስተዳደር> በተሰኘው መጽሀፋቸው እንደጻፉት ህዝብ እንዲያውቅና እንዲነቃ ማድረግ ጥቅሙ ለህዝቡ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለመንግስትም ጭምር ነው፡-
ለአስተዳደር የሚመችና አርነት ያለው ህዝብ ጤናማ የህዝብና መንግስት ግንኙነት እንዲኖር መሰረት ነው:፤ ያልሰለጠነ ህዝብ መብትና ግዴታውን ስለማያውቅ ለማስተዳደር አይመችም፤ምክንያቱም ከንግግርና ውይይት ይልቅ ጦርነት ይቀናዋልና ነው።ስለሆነም የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው ህዝቡ እንዲነቃና እንዲሰለጥን ማድረግ ነው።
በተለያዩ መስኮች ታሪካቸው ሊወሳ፣ ገድላቸው ሊነገር ከሚገቡ የአገርና ህዝብ ባለውለታዎች መካከል ኢትዮጵያዊያን ጸሀፍት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በተለያዩ የዘመን ማዕቀፍ ብቅ ያሉ ጸሀፊያን የቀደመውን ትውልድ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ከፍታና ዝቅታ መዝግበው ያቆዩ፣ የዛሬን ዕውነቶችን ከትበው ለቀጣይ ትውልድ ያኖሩ የታሪክ ነጋሪዎችም ጭምር ናቸው።
ጸሀፊያኑ በስራዎቻቸው ህዝብን ለማስተማርና ለማንቃት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፤ ራሳቸው እንደ ሻማ ቀልጠው ለህዝብ ብርሃን ሆነዋል። ታዲያ እነዚህን የሲቪል ጀግኖቻችንን ምስጋና መንፈግ አሉታዊ ተጽዕኖው ትውልድ ተሻጋሪ ነው፤ ዛሬ ላይ ሆነው ነገን እየሰሩ ያሉ ተተኪ ጸሀፍት ተነሳሽነት የሚጎዳም ጭምር ነው፤ የነገውን ትውልድ መሰረት ማሳጣት ነው፤ ይህም በታሪክ የሚያስወቅስ፣ ከሞራል አኳያም ወንጀል ነው።
ስለሆነም የአገርና የህዝብ ባለውታ ለሆኑ ጸሀፊያንና ስራዎቻቸው እውቅና ከመስጠት ባለፈ መጪው ትውልድ እነዚህን ጀግኖች እንዲያውቅ ማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም እንዲሉ በዚህች መጽሀፌ በስነ ጽሁፍ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ለመዘከር ያደረግሁት ጥረት ይህን የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት እንጂ ልዩ የሥነ ጽሁፍ ችሎታ ኖሮኝ እንዳልሆነ አንባቢያን እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ።
መግቢያ (Summary)
በዚህ መጽሀፍ በልቦለድና ኢ-ልቦለድ ሥነ ጽሑፍ ፈር ቀዳጅ የሆኑ፣ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለዘርፉ እድገት የራሳቸውን ሚና የተጫወቱ የሠላሳ አንጋፋ ኢትዮጵያዊያን የህይወት ታሪክና ስራዎቻቸው በአጭሩ ቀርቧል። በመጽሀፉ የተካተቱት የሥነ ጽሁፍ ሰዎች በርካታ የሚያመሳስላቸው ጉዳዮች አሉ፤ ከዚህ አንጻር የልቦለድና የተውኔት ድርሰት እንዲሁም ጋዜጠኝነትን በሁለገብነት የሚከውኑ መሆናቸው ዋነኛው ነው።
ይህን መጽሀፍ ለማዘጋጀት ከሰባ በላይ መጽሄቶችና ጋዜጦች፣ መጽሀፍት፣ የጥናት ውጤቶችና ጆርናሎች፣ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞች፣ ድረ ገጽ መረጃዎችን እንዲሁም ሌሎች የህትመት ውጤቶችን እንደ ማጣቀሻ ወስጄአለሁ። ከእነዚህ የህትመት ውጤቶች ጸሀፊያኑ ራሳቸው ስለ ስራዎቻቸውና የህይወት ጉዟቸው በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸውን ቃለ መጠይቆች፣ ሌሎች ጸሀፊያን በስራዎቻቸው ዙሪያ ያጠናቀሯቸው ትንታኔዎች ለማየት ሞክሬአለሁ። በግሌ ያነበብኳቸውን መጻህፍት ይዘት በራሴ አረዳድ በጥቂቱም ቢሆን ለመጻፍ ጥረት ባደርግም ቴክኒካዊና ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚያሻ በአብዛኛው ግን የስነ ጽሁፍ ባለሙያዎች የሰጧቸውን ሂሶችና ትንታኔዎችን ማካተትን መርጫለሁ። ለዚህም ምክንያቴ አንደኛ ሁሉም መጻህፍትና ተውኔቶችን የማንበብና የማግኘት ዕድሉ አልነበረኝም፤ ሁለተኛና ዋናው ጉዳይ ይህን ለማድረግ ራሱ የሀያሲነት ሙያን ይጠይቃልና በማላውቀው ሙያ ገብቼ አንባቢን ማሳሳት ስለሌለብኝ ነው።
የመጽሀፉን ጠቀሜታና አስፈላጊነት አንባቢያን የሚመዝኑት ቢሆንም እኔ ግን ይህን መጽሀፍ የማሰናዳት አስፈላጊነት ቢያንስ ከአራት አቅጣጫዎች ለማየት ችዬአለሁ። በቅድሚያ ትናንትን ያሳዩንና ለዛሬ መሰረት የጣሉ ፈር ቀዳጅ ደራሲያንና ጋዜጠኞችን የህይወት ታሪክ እንዲህ ማዘጋጀቴ በትንሹም ቢሆን ለስነ ጽሁፍ አለም ዕድገት ላበረከቱት ውለታ ማስታወሻ እንዲሆን በማሰብ ነው። ሁለተኛ የኢትዮጵያን ጸሀፍትን የግል የህይወትና የስራ ጉዞ መርምሮ እንደዚህ ማዘጋጀቱ አንባቢያን ከጸሀፍቱ የግልና የስራ ህይወት ሊማሩ የሚችሏቸው በርካታ ፍሬ ነገሮች አሉ ብዬ ስለማምን ነው። ሌላው ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት የጸሀፊያንን የስራና የህይወት ታሪክ በጋዜጦች፣ በመጽሄቶችና በመጽሀፍት ለመዘከር በተደረጉ አንዳንድ ጥረቶች የመረጃዎች መጣረስና መዛባት በስፋት ይስተዋላል። በዚህ መጽሀፍ እነዚህን ጉድለቶች ለመሙላት ተሞክሯል። ከሁሉ በላይ ግን ይህ መጽሀፍ የደራሲያኑን ስራዎችን ይዘትና ጥልቀት፣ እንዲሁም የህይወት ጉዞ በስፋት ለመዳሰስ ለሚፈልጉ ሌሎች ጸሀፊያን ምናልባትም እንደመነሻ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።
ስለ ደራሲያንና ስራዎቻቸው ከማንሳት በፊት በተለያዩ የጊዜ ማዕቀፎች የስነ ጽሁፍ ዘርፍ ከባቢን ማሳየት ተገቢነቱ አያጠራጥርም። ይህም መጽሀፉን ምሉዕ ከማድረግ ባለፈ የዘርፉን ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በማሳየት ጸሀፊያኑ ያለፉበትን መንገድ ሊጠቁመን ይችላል፡፡ በዚህም በመጽሀፉ የመጀመሪያ ክፍል በዋናነት ከ1850ዎቹ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ባለው የዘመን ማዕቀፍ በኢትዮጵያ የልቦለድና ኢ-ልቦለድ ስራዎች፣ የተውኔት ድርሰትና ጋዜጠኝነት ዙሪያ አጭር ቅኝት ለማቅረብ ሞክሬአሁ፡፡
ሠናይ ንባብ!
ሀምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም
ጅግጅጋ፤ ኢትዮጵያ

አስተያየት ያስቀምጡ