ሀብታሙ ግርማ መስከረም 3/ 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
መግቢያ
የጽሑፌ ጭብጥ የጽሑፉ ርዕስ ነው። ዛሬ በውድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ደም ስንናፍቀው የኖርነውን የነጻነት አየር መተንፈስ በጀመርንበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርስ ለመነቋቆር እና ለመበጣበጥ የሚነሳበት ምክንያት የለውም፤ ነገሩ የፖለቲካ አጀንዳ ልዩነት(ቢኖር እንኳ በንግግር መፍታት ይቻላል) ሳይሆን የአመል ነው። የአመል ችግር የሚለውን የሚጠቀልል የአማርኛ ቃል የቅንነት ችግር (Lack of integrity) ነው።
ቅን አለመሆናችን ለብዙ መከራ ዳርጎናል፤ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገራዊ ችግሮቻችን መነሾ ናቸው የምላቸው ምክንያቶች የዚሁ ውጤት ናቸው።
የቅንነት ችግር ምልክቶች
የቅንነት ችግር ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፦
እውነትን ከሐሰት፤ ትክክለኛውን ከስህተተኛ ለመለየት የመንፈስ፣ የሞራልም ሆነ የአእምሮ ዝግጁነት ማጣት፣
በስሌት ሳይሆን በስሜት መነዳት፣
ለበረታው ዕውቅና ከመስጠትና በመንፈሳዊ ቅናት( rational selfishness) ተነሳስተን ከስኬቱ ሂደት ለመማር ከመሞከር ይልቅ ስኬቱን ለማሳነስ መሞከር፣
ብልጣብልጥነት፣ ጮሌነት እና የድል አጥቢያ አርበኝነት ባላጠቃን ነበር
እኛ ኢትዮጵያውያን ቅንነት ቢኖረን ኖሮ……..
በህይወት መስመራችን ጉዳያችን የሆነን ነገር የምናውቅ፣ በመሆኑም አላስፈላጊና ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችን እንደ ጉዳይ ወስደን ራስ በራሳችንን ባላደከምን፣ የምናደርገው ነገር ሁሉ በምክንያት በሆነ ነበር፤ የድርጊቶቻችን ውጤት አንዱን ይዞ አንዱን መጣል አይነት ሆኖብን ለመንግስት ብቻ ሳይሆን ለፈጣሪ እንኳ አስቸጋሪ ህዝቦች ባልሆን ነበር፤ ለተንሸዋረረ የታሪክ አረዳዳድ ባልተጋለጥን ፣ በመሆኑም የረጅም ዘመን ታሪካችን ለአንድነታችን መሠረት የሆኑ እጅግ በርካታ በጎ ሁነቶችን ያዘለ ቢሆንም ይህ የታሪክ እውነት ደብዝዞ በአንጻሩ ያለፈው በጎ ያልሆነው የታሪካችን አካል ባልደመቀ ነበር።
በታሪክ ሂደት ያሳለፍነው በርካታ መልካም እንደነበር ሁሉ መልካም ያልሆኑ ግንኙነቶች እንዳሳለፍን እንረዳ ነበር፤ በመሆኑም የምንወዳት እና የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ የምንላት አገር ህዝቦቿ በተለያዩ ምክንያቶች (ኃይማኖታዊ፣ የማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳዳር ወዘተ….) በተለያዩ ወቅቶች በአገራዊ እና አለማቀፋዊ ገፊ ምክንያቶች እርስ በርስ የተዋጉ፣ አንዱ ሌላውን ያስገበረበት ሁነቶች በርካታ መሆናቸውን በአንድ በኩል የመካድ በሌላው በኩል የማጉላት አዝማሚያ የፖለቲካችን መዘውር (pillar) ሆኖ ባልተቸገርን ነበር። ዛሬ ላይ በጎ ያልሆነውን የታሪካችን አካል እና(ወይም) ወካይ ምልክቶቹን ማንሳታችን ተገቢነቱ ካለፈው ስህተታችን ለመማር እንጂ ለመነታረክ ፣ ለመበሻሸቅ፣ የአሸናፊነት ወይም የተሸናፊነት መንፈስ በማስረጽ ባልከፋፈለን ነበር፤
በመሆኑም ዛሬ ላይ ይህን በጎ ያልሆነ የታሪክ አሻራ ጠባሳ ሰለባ ያልሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል የሆነ ብሔር፣ የሐይማኖት እና የፖለቲካ ቡድን አለመኖሩ፣ በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ የእነዚህ የማህበረብ ክፍሎች(ህዝቦች) ድምር መሆኑን ተረድተን፣ የመጥፎ ታሪካችን ሰለባ የነበሩትን ወገኖቻችንን የሚያበሳጩ፣ ሰቆቃቸውን የሚያስታውሱ ምልክቶች ለሌላኞቻችን የድል አድራጊነት፣ የአሸናፊነት፣ ምልክት ከማድረግ በተቆጠብን ነበር ፤ በአጠቃላይ ታሪካችን የመማሪያ ሳይሆን መጥፎ የታሪክ አሻራችን አገርሽቶ ሌላ መጥፎ ታሪክ ለመጭው ትውልድ ለሚያወርሱ እኩይ ድርጊቶች የሚጋብዝ፣ ትልቅ የተስፋ ጮራ የፈነጠቀውን የለውጥ ሂደት የሚቀለብስ፣ ሲከፋም የጋራ ቤታችን የምንላትን ኢትዮጵያ ምኞት ብቻ እንዳትሆን ትልቅ ስጋት ባልሆነ ነበር።
ቅንነት ቢኖረን ኖሮ……..
የአገር አንድነት እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ጨምሮ በእለት ተዕለት ግንኙነቶቻችንን የምንወያየው እና የምንከራከረው ፋይዳ ስላለው ጉዳይ ይሆን፣በእንቅሰቃሴዎቻችን ሁሉ ትልቁን ምስል ባልተጋረደብን ነበር፤
በቅርብ ታሪካችን አይተን የማናውቃቸው እንደ ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አብይ አህመድ፣ ደመቀ መኮንን፣ ሙፈሪሃት ከማል እና ሙስጠፌ መሀሙድ ኡመር አይነት ጥሩ መሪዎች አግኝተን በነቢብ እየደገፍናቸው በገቢር ግን እየወጋናቸው መሆኑን መገንዘብ ይቻለን ነበር፤ መልካም አመራራቸውን ለመደገፍ ከመጣር ይልቅ በየዕለቱ የቤት ስራ ባልሆንባቸው ነበር።
ኢትዮጵያዊያን የቅንንነትን እሴቶችን እሴቶቻቸው በማድረግ ራሳቸውንም ሆና አገራቸውን ከጥፋት ይታደጉ ዘንድ ብቸኛው አማራጫቸው ነው።
አዲሱ ዓመት ሁላችንም ቅንነትን የምንለማመድበት ዘመን ይሆን ዘንድ እመኛለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ይባርክ፤ አሜን!!!

አስተያየት ያስቀምጡ