ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

ከኢትዮጵያዊነት የስነልቦና ውቅር የተፋታው የህወሃት የፖለቲካ መስመር !!!

ሀብታሙ ግርማ፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር

ማስታወሻ:- ይህ መጣጥፍ ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በሪፖርተር ጋዜጣ ለህትመት ቢበቃም፣ ጽሑፉ የተዘጋጀው ከአመት በፊት ነበር። መጣጥፉ በይዘቱ የህወሃትን የፖለቲካ አስተዳደር ዘይቤ (system of political governance) በርዕዮተ ዓለማዊ መነጽር በወፍ በረር መገምገም ነው፤ በዋናነትም የህወሃት መራሹ ኢህአዴግ አመራሮች የፖለቲካ ስብዕና መሠረታዊያንን መጠቆም ነው። መጣጥፉን በዚህ ወቅት ለአንባቢ የማድረሱ ዓላማ ሁለት ነው፥ አንድም ህወሃትን በማጥላላት ሳይሆን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ለመተቸት ነው። ሁለትም በድህረ-ህወሃት ኢትዮጵያ (Post TPLF Ethiopia) የፖለቲካ ማማ ላይ የወጣው የለውጥ አመራር ምናልባት ወጣ ገባ በበዛበት ነባራዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሰላችቶ ለፖለቲካው ብልሽት ዘላቂ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የህወሃትን መስመር ያዋጣ ይሆን ብሎ የውድቀት ቁልቁለት እንዳይጀምር ለማሳሰብ ነው። ቅዱሳን መጽሐፍት እንደሚያስተምሩን የሰው ልጅ በክፉዎች መቅናት የለባቸውምና የህወሃትን መስመር እንዳይመኘው ምክር ቢጤ ለመወርወር ነው።

መግቢያ

ካለፉት 40 ዓመታት ጀምሮ የትግራይ ህዝብ የፓለቲካ ትግል እና የሥነ መንግስት ቅርጽ የሆነው ህወሃት እንዴት የትግራይ ህዝብ ነባራዊ ሀቅ ከሆነው የታሪክ፣ ባህል፣ ሥነ ልቦና እና እምነት ያፈነገጠ እንደሆነ ብዙዎች ይኮንናሉ፤ እኔም ይህን ግምገማ እጋራለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ለሥልጣን እና ሥነ መንግስት ያለው አመለካከት አዎንታዊ ሆኖ ሳለ ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብ ማዕከላዊ መንግስት ፊት አውራሪ ሆኖ በቆየባቸው ሶስት አስርት ዓመታት ገደማ ለኢትዮጵያዊያን ባዕድ የሆነ የሥነ መንግስት ፍልስፍና እና የአስተዳደር ዘይቤ እንዲከተል የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው? ይህ መጣጥፍ ለእነዚህና ተዛማጅ ጥያቄዎች መልስ ያፈላልጋል።

የትግራይ (የኢትዮጵያ ህዝብ) ታሪካዊና ሥነ ልቦናዊ መሠረቶች

በመሠረቱ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲሁም የፖለቲካ ግንባታ ትልቅ ድርሻ የያዘ ነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ የአምስት ሺህ አመት ታሪክ ጉልህ ስፍራ አለው። በርካታ ጸሐፍት እና የታሪክ ሊቃውንት እንደጻፉት የኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ የመንፈሳዊ ስልጣኔ ነው፤ የቁሳዊ ስልጣኔ አልነበረም። የመንፈሳዊ ስልጣኔው አሻራ የሆኑት ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ የፈጣሪ መንገድ የሆኑትን ሃይማኖቶችን አለመዳፈር፣ ለህግ መገዛት፣ ሥርዓተ መንግስትን ማክበር፣ ውለታ አለመርሳት፣ ለይቅርታ እና እርቅ ዋጋ መስጠት፣ ይቅር ባይንና አስታራቂን ማክበር ከብዙ በጥቂቱ ናቸው። የተጠቀሱት መልካም እሴቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ (ለትግራይ ህዝብ) የታሪኩ፣ የባህሉ፣ትውፊቱ፣ እምነቱ፣ መሠረት የሆኑ በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ወይም ተክለ ስብዕና መገለጫዎች ናቸው።

የቀደሙት የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግስታት…….

በተለያየ ዘመን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ሥርዓረተ መንግስታት እና መሪዎች ከፍ ሲል ከእነዚህ አትዮጵያዊ መገለጫዎች ተነጥለው የማይታይ የአስተዳደር ዘይቤ ይከተሉ የነበሩ፣ ዝቅ ሲል እነዚህን መልካም እሴቶች በድፍረት የሚጨፈልቁ አልነበሩም በመሆኑም ለህዝባዊ አንድነት መሠረት የሆኑትን የበጎ ሥነ ምግባር እሴቶች ለሆኑት መከባበር፣ መተማመን፣ መተሳሰብ ዋጋ የሚሰጡ፣የኢትዮጵያ ህዝብ ለክብር እና ኩራቱ የሚጋደል መሆኑን ጠንቅቀው የተረዱ፤ ኢትዮጵያዊ ለህገ-ህሊናው የሚገዛ፣ ሰው ወዳድ፣ ካልነኩት የማይነካ፣ ከራሱ በላይ ለእንግዳው ቅድሚያ የሚሠጥ፣ ፍርድ ሲጓደል ለምን የሚል፣ ለማህተቡ (ለእምነቱ) ሟች መሆኑን በመልካም ወስደው እነዚህን ህዝባዊ እሴቶች ሊተናኮሉ(ሊሸረሽሩ) ይቅርና የፖለቲካ ፍጆታ ወይም የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ለማድረግ ድፍረት አላሳዩም።
ስልጣን የህዝብ ማገልገያ እንጂ የጭቆና መሣሪያ አይደለም የሚለውን መርህ በግላጭ ለመዳፈር አልሞከሩም፤ የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን የአገራዊ አንድነት ማረጋገጫ ማህተም እንጂ በጥበብ የመከፋፈያ መሣሪያ አድርገው አልተጠቀሙም፤ በፖሊሲዎቻቸው የመንግሥት ሥልጣን የተመሪው ህዝብ በጎ እሴቶቹን እንዲጠብቅ መሠረታዊ ተቋማት የሆኑትን፣ ማለትም ሀይማኖት ቤተሰብ እና የትምህርት ተቋማትን ቢያንስ ለማዳከም ሴራ አልሸረቡም።

ታዲያ ህወሃት ከነባራዊው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ለምን አፈነገጠ?

ዛሬ ላይ ህወሃት መራሹን መንግስት ስገመግም ከቀደሙት የኢትዮጵያ የተለየ ሆኖ አገኘሁት። ለአንባቢ ህወሃት ከትግራይ(ኢትዮጵያ) ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ስነ ልቦና በብዙ መልኩ የሚጻረር የፖለቲካ መሥመር ይከተላል ለሚለው አስረጅ ማቅረብ ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፤ ከዚህ ይልቅ ህወሃት ለምን እንዲህ አፈንጋጭ የአስተዳደር ዘዬ የይከተላል ብሎ ማጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። በእኔ ግንዛቤ ለዚህ መልሱ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ነው።
የህወሃት የፖለቲካ መሥመር አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። በህወሃት ቤት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከአይዲዮሎጂም በላይ ነው፤ ሀይማኖት ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ በእሳቤው የትኛውንም አገራዊም ሆነ ህዝባዊ ጉዳይ የመሸጋገሪያ እንጂ ግብ አይደለም። በመሆኑም የሥነ መንግስት እሳቤው መርህ መሠረት እና(ወይም) መገለጫ የሆኑት ህገ መንግስት፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ቢሮክራሲ፣ ዲሞክራሲ፣ ፖሊሲ ወዘተ…. የታክቲክ ጉዳዮች ናቸው። በመሆኑም በህወሃት የአስተዳደር ዘመን በኢትዮጵያ ግልጽ የሆነ፣ ርዕይ ያለው፣ ስትራቴጂካዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ተዓማኒ(legitmate)፣ የሚገመት (predictable) የህዝብ አስተዳደር መስመር እና ተቋማት እንዳይኖር አድርጓል።

ህወሃት ለምን በህዝብ ይጠላል?

ህወሃት በብዙ ኢትዮጵያዊያን እንዲጠላ የሆነበት ምክንያት የሚከተለው ሶሻሊስታዊ መስመር ከሰወኛ እሴቶች (human values)፣ በተለይም ከኢትዮጵያዊ እሴቶች (Ethiopian Values) በብዙ መልኩ የማይገጥም መሆኑ ነው። ይህን በዝርዝር በአዲስ መስመር ስንመለከተው
የህወሃት የፖለቲካ ኢኮኖሚው መሠረት የኢትዮጵያን ታሪክ በማይመለከተው የማርሲስት ሌኒኒስት የበዝባዥ- ተበዝባዥ አስተምህሮ መቃኘቱ ነው።
* ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ስነ ልቦና በተጻራሪ ሁሉንም የህዝብ መስተጋብር በዲያሌክቲክ ቁሳካላዊነት ለመግለጽ መሞከሩና የማህበረ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹ መነሻና መድረሻ ማድረጉ ነው።
የህወሃት የሚከተለው ሶሻሊስታዊ የአስተዳደር ዘይቤ መጠራጠርንና መከፋፈልን መሠረቱ ያደረገ፣ ህዝብን ወይም የማህበረሰብ ክፍሎችን በጠላት እና ወዳጅ (friend-foe dictum) የሚከፋፍል በመሆኑ ነው።
የህወሃት አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሶሻሊስት አስተምህሮ የተቃኘ፣ ከግለሰብ ይልቅ ቡድንን የሚያስቀድም መሆኑ ለዜግነት እሴቶች ይልቅ ቡድናዊነትን ስለሚሰብክ ነው።
* አብዮታዊ ዲሞክራሲ ታሪክን የሚረዳበት መነጽር ቁስ አካላዊነትን መሠረት ያደረገ (Historical Materialism)፣ የታሪክ ሁነቶችን የሚተነትንበት አግባብ ደግሞ ህዝብን በጠላት ወዳጅ የሚለያይ (Class Conception of History) መሆኑ ነው።
* ህወሃት የሚከተለው ሶሻሊስታዊ መስመር በዘመናት ሂደት የህዝብን የማህበረ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ፣ ስነ ልቦና እና ተክለ ስብዕና የማዕዘን ድንጋይ ለሆኑት እንደ ባህል፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ እምነት፣ ሥነ ትምህርት፣ ሥነ ምግባር የመሳሰሉት እውቅና ከመስጠት ይልቅ አፈራርሶ ሶሻሊስታዊ (ቁሳዊ) ማንነትን በህዝብ ላይ ለመጫን (Mass Inclulcation of Socialist Ideals) መሞከሩ፣
* በዚህም ሁሉንም ነገር ፖለቲካ የማድረግ ዝንባሌው ለዘመናት የፖለቲካ አይነኬ የሆኑትን ህዝባዊ (የመንፈሳዊ ወይም የሀይማኖት) ተቋማት ላይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ለማድረጉ መሞከሩ ነው።

በመጨረሻም…..

ፈጣሪ የህወሃት ሰዎች ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አጥፊ መንገድ ይመለሱ ዘንድ ልቦና ይስጣቸው ዘንድ እጸልያለሁ፤ ለትግራይ ህዝብ ደግሞ (ጠ/ሚ አብይ በመጀመሪያው የትግራይ ጉብኝታቸው ወቅት ከተናገሩት፣ አፋቸውን ልዋስና) “….ከንቐደምና” ወይም “…..እንደድሯችን” የሚል መልዕክት ለመስደድ እወዳለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ይባርክ፤ አሜን!


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading