ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

ጅግጅጋ በዚያች ቀውጢ ቀን

በወሳኝ ወቅት የተገለጠው የሶማሌ ወንድሞቻችን ኢትዮጵያዊ አብሮነት

ሀብታሙ ግርማ

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር

አንባቢያን እንዲያስታውሱት፦ የዚህ መጣጥፍ አላማ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በተለይ በጅግጅጋ እና አከባቢዋ የደረሰውን አስነዋሪ ድርጊት አንደኛ አመት ስናስታውስ ነገሩን የምንረዳበትን አጠቃላይ አውድ ማሳየት፣ በመሆኑም በተለይ በአደጋው ቀጥተኛ ተጠቂ የሆንን ሁሉ በዳያችንን በአግባቡ እንድንለይ ለማሳሰብ ነው። ከዚህ አንጻር አንባቢያን በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነስቶ እንደማያውቅ እንድናስታውስ (እንድንገነዘብ) ማስቻል ነው። በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ገዢዎች ሕዝቡን ከፋፍለው ለመግዛት እንዲያመቻቸው አንዱን ጠላት ፣ሌላውን ወዳጅ በማድረግ ህዝብን እየማገዱ ስልጣናቸውን ሲያደላድሉ የኖሩበትን አስቀያሚውን የኢትዮጵያ የሥነ መንግስት ታሪክ በማስታወስ የሐምሌ 28ቱ ድርጊትም መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር መሆኑን አንባቢ እንዲገነዘብ ነው። የመጣጥፉ ዓላማ በዋናነት ሀምሌ 28/2010 እንደተስተዋለው የኢትዮጵያ ህዝብ የመሪዎቹን ሴራ ተቋቁሞ ለዘመናት በአብሮነት የመኖሩን እውነት በዚያች ጥቁር ቀን ከሶማሌ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን በታየው አብሮነት ለመግለጥ ነው።

ይህ መጣጥፍ የተዘጋጀው የሐምሌ 28/2010 ዓ.ም ጥቃት በተፈጸመ ሶስተኛው ወር፣ ጥቅምት 28/2011 ዓ.ም ነበር። መጣጥፉ በሪፖርተር ጋዜጣ ለንባብ በቅቷል (ከታች የተመለከተውን ሊንክ ይጫኑ)። አሁን ደግሞ የአደጋው አንደኛ አመት በማስመልከት መጠነኛ የርዕስ እና ይዘት ቅርጽ ማሻሻያ ከማድረግ በቀር በአብዛኛው እንደወረደ የተዘጋጀ ነው። https://www.ethiopianreporter.com/index.php/article/13810

እንደ መግቢያ

ኢትዮጵያዊያን አስራ ሶስቱን የአመቱን ወራቶች በልዩ መገለጫቸው ማንሳታቸው የተለምዶ ነው፤ ለምሳሌ በደገኛው ነዋሪ ዘንድ የሐምሌ ወር በነጎድጓድ በታጅቡ ጥቁር ደመናማ ቀናት ይታወሳል፤ ይህ ግን ለምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል፣ በተለይ ለሶማሌ ምድር አይሰራም። ሶማሌዎች Heeg-Heeg በሚል የሚጠሩት ባለአሸባሪ ድምጽ ያለው ነጎድጓድ እና ሐምሌ ወር ትውውቃቸው እምብዛም ነው። ያሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር የመጨረሻ ሶስት ቀናት ግን ባልተለመደ ሁኔታ መላው የሶማሌ ክልል በአስገምጋሚ ነጎድጓድ ተመታ፤ ነጎድጓዱ የተፈጥሮ አልነበረም፣ ራሱን ‘Heego ወይም ነጎድጓዶቹ’ ብሎ የሰየመው የተደራጀ ቡድን የጎሰመው የእልቂት ነጋሪት እንጂ።
ከሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የዘለቀው ይህ ሰው ሰራሽ ነጎድጓድ የበርካታ ንፁሃንን ህይወት በልቷል፤ የታዳጊ ልጃገረዶች፣ ወጣት ሴቶች እና እናቶችን የሴትነት ክብር ደፍሯል፤ የግለሰቦች እና የመንግስትን ንብረት አውድሟል። በአጥፊዎቹ ላይ ክስ የመሰረተው የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤት ባሰማው የክስ ጭብጥ የጥፋት ሐይሎቹ ድግስ የብሔር እና(ወይም) የሐይማኖት ግጭት በማስነሳት እልቂት ማምጣት ነበር፤ ነገር ግን በፈጣሪ መልካም ፍቃድ እና ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ይዘን በቆየነው መንፈሳዊ እና ማህበራዊ እሴቶቻችን ሊከሰት ይችል የነበረው ከባድ ጥፋት ቀንሷል።
የዚህ መጣጥፍ አላማ የደረሰውን ውድመት እያስታወሱ ለማላዘን፣ ወይም በአዋሽ ማዶዎቹ አፍ ‘ሒራር ለመጥራት’ አይደለም፤ ችግሩ ከተከሰተ ከዘጠና ቀናት በኋላ ያ ጥቁር ቀን ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ ለመሻር የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን መገምገም እንዲሁም ጉዳቱን ለመቀነስ ፈጣን እልባት የሚያሻቸውን ጉዳዮች ነቅሶ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡ ለማሳሰብ ነው።

መንግስታዊ ማፈናቀል በሶማሌ ክልል አልተጀመረም!

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በጽሑፎቻቸው ደጋግመው እንዳስነበቡን፣ እኔም አጥብቄ እንደምደግፈው፣ የተለያዩ ብሔር፣ ሀይማኖት እና ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊን ከልዩነቶቻቸው ጋር ባንድ አገር ልጅነት የቆዩት ሶስት ሺህ ዓመታትን ከተሻገረው መንፈሳዊ ስልጣኔያቸው በወረሱት እሴቶቻቸው ነው። ኢትዮጵያዊያን የጥበብ መጀመሪያ ተብሎ በቅዱሳን መጻሕፍት የምናገኘው ትልቅ ሀብት የሆነውን ፈሪሃ እግዚአብሔር መታደላቸው በነቢብም ሆነ በገቢር የምናስተውለው ሀቅ ነው። የዚህ መገለጫ አንዱ ኢትዮጵያዊያን በችግሮቻቸው ወቅት አብሮ የመቆም የቆየ ታሪክ ወይም ማንነት ባለቤት መሆናቸው ነው። በእርግጥም ችግርን በጋራ መጋፈጥ የኢትዮጵያዊነት ልቡ ነው።
ነገር ግን ይህ እንቁ ኢትዮጵያዊ ሀብት ባለፉት 25 ዓመታት ያውም መንግስት ነኝ በሚል አካል በተደጋጋሚ ጥቃት ተሰንዝሮበታል።
በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ መንግስታዊ ማፈናቀል ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመው በ1990 ዓ.ም ገደማ በኤርትራዊያን ወገኖች ላይ ነበር። በወቅቱ ‘አንድን ቡድን ለይቶ ማጥቃትና ማፈናቀል ዘርን ለይቶ ማጥራት ወይም ethnic cleansing ነው፤ መዘዙም ትውልድ የሚተላለፍ የተስቦ ያህል ነው’ ብለው የሞገቱ በርካታ ምሁራን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሰሚ ጆሮ አላገኙም ነበር።
የሚገርመው ነገር መንግስታዊ ማፈናቀሉ ከተፈፀመ ሰባት አመት እንኳ ሳይሞላ (በ1997ቱ የምርጫ ዋዜማ ወቅት) ኢህአዴግ አይኑን በጨው አጥቦ ተበዳይ ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ይዳኘኝ አለ፤ የአዞ እንባውን እያፈሰሰ የክስ ጭብጡን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰማ፤ እንዲህ ሲል፥ ‘የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ፍረድ፥ ጽንፈኛ ቀኝ ዘዘመም የፖለቲካ ቡድኖች ስብስብ የሆነው ቅንጅት ለአንድት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ‘ትግሬ ወደ መቀሌ’ የሚል በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ዘመቻ እየደሰኮረ ነው፤ የአብሮነትህ መሠረት የሆነውን እሴትህን ለፖለቲካ ቁማር አውሎታል።
ለኢህአዴግ ክስ ምላሽ እንዲሆን ቅንጅት ይህን ብሎ ነበር፦ ኢህአዴግ አሸናፊ ሀሳብ ስላልነበረውና ምርጫውን ለማሸነፍ የግድ ክስ ማብዛት ነበረበት፥ እናም የኢትዮጵያዊያንን የስነ ልቦና መሠረት እንደሆነ በሚያውቀውና ህዝቡ በማይደራደርበት ጉዳይ ላይ የሐሰት ክስ ለማቅረብ ተገደደ።
ፍርዱን ለጊዜው እንተወውና ኢህአዴግ ከሳሽ ሆኖ በቀረበበት ወቅት የሚመራው መንግስት በኤርትራዊ ወንድሞች ላይ ለፈጸመው በደል ይቅርታ አልጠየቀም ነበር፤ እናም ክስ ለመሰንዘር የሞራል መሠረት አልነበረውም፤ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት እንኳ መንግስታዊ ማፈናቀሉ መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል።

የሶማሌ ወንድሞቻችን እገዛ አይረሳም!

በ2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ሁለት ብሔር ተኮር መንግስታዊ ጥቃቶችና ማፈናቀሎች ተፈጽመዋል፤ በሁለቱም አስቀያሚ ቀናት የማፈናቀሉ ዕዝ ከነበረችው ጅግጅጋ ከተማ ነበርኩ። የመጀመሪያው በመስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ወገኖች ላይ የተቃጣ ነበር፤ ሁለተኛው ብሔር ተኮር መንግስታዊ ጥቃት ከሐምሌ 28 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የዘለቀው ነው።
አምባገነን በሆነ ሥርዓት ህዝብ መንግስትን የመውቀስም ሆነ የመተቸት፤በሰላማዊ መንገድ መብቶቹን መጠየቅ አይችልም፤ ለምን ወገኖቻችን ይፈናቀላሉ ብሎ በተደራጀ ሁኔታ ቢጠይቅ ቅጣቱ የከፋ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን የማንነታቸው እሴት የሆነውን አብሮታቸውን የሚንድ ድርጊት የአምባገነኖች አርጩሜ ሳያስበረግጋቸው ተቃውመዋል። ለአብነት በኦሮሞ ወገን መፈናቀል ወቅት ተቃውሞ ያሰማ አንድ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ለአስራ አንድ ወራት በጅግጅጋ በሚገኘው የኢ.ሶ.ክ.መ ማዕከላዊ የስቃይ አምባ ያለምንም ክስ ሆነ ፍርድ ማቋል።
ሐምሌ 28 ቀን የሶማሌ ወገኖቻችን የኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ዳግም የተገለጠበት ቀን ነበር። በዚያ ጥቁር ቀን ወንድም የሶማሌ ህዝብ የአብዲ መሀሙድ ኡመር መንግስት ጡንቻ ሳያንበረክከው ጥቃቱ ለተሰነዘረባቸው ወገኖቹ መሸሸጊያ ሆኗል። የሶማሌ ወንድሞቻችን እገዛ በእውነቱ እጅግ ትልቅ፣ ግን ብዙ ያልተባለለት ነው። የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅን ጨምሮ ጎረቤቶቹን፣ የስራ ባልደረቦቹንም ሆነ የቅርብ ጓደኞቹን ከአጥፊዎች የታደጉት ሶማሌ ወገኖች ናቸው። በግሌ የሶማሌ ግቢ ተከራይቶ የሚኖር ወይም ከሶማሌ ኢትዮጵያውያን ተጎራብቶ እየኖረ የተዘረፈም ሆነ ሌላ ጥቃት የደረሰበት አልሰማሁም።
በህዝቡ ዘንድ ተደጋግሞ እንደተነገረው የጥፋት ድግሱ ዓላማ የተፈጸመው አሥር በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው፤ ታዲያ እልቂቱ በዘጠና በመቶ ቀነሰ ከተባለ ምክንያቱ (የፈጣሪ እገዛን ሳይዘነጋ) በታላቁ የሶማሌ ህዝብ በጎነት ነበር ማለት ይቻላል።

ለሙስጠፌ መሀሙድ ኡመር አስተዳደር ተገቢው ድጋፍ ይደረግ!

ሙስጠፌ መሀሙድ ኡመር የሶማሌ ክልል ሆነው ከተሾሙ ሁለት ወራት ብቻ ነው፤ ከቀደመው አስተዳደር የተረከቡት የፋይናንስ፣ የሰው ሐይልም ሆነ የቢሮክራሲ መዋቅር አልነበረም፤ መንግስት የማዋቀር ሥራ እንደአዲስ ነው እየሰሩ ያሉት። የሶማሌ ክልል ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁነቶች፣ የቀደመው የክልሉ አስተዳደር ባህሪያት እና የደረሰው ጥፋት እጅግ ከፍተኛ መሆን፣ እንዲሁም ችግሮቹ በአፋጣኝ ምላሽ የሚሹ መሆናቸው ተዳምረው አዲሱን የክልሉ አስተዳደር ከባድ ጫና ውስጥ የሚከቱ ናቸው፥ በመሆኑም የፌዴራል መንግስት ልዩ ድጋፍ ሊያደርግ ይገበዋል።

በመጨረሻም…….

የአዋሽ ማዶ ሰው ነገር ማብረድ መለያው ባይሆን ኖሮ፤ ጠንካራ የመረዳዳት ማህበራዊ እሴት (Social Capital) ጥሪት ሆኖት የደረሰበትን ሰብዓዊ፣ ስነ ልቦናዊ እንዲሁም ቁሳዊ ጥቃት እንዲቋቋም ባያግዘው ከደረሰው አደጋ አንጻር ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ይከሰት እንደነበር አእምሮ ያለው ሁሉ የሚያገናዝበው ነው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የወንድም ሶማሌ ወገኖቻችን በችግሩ ወቅት ከተጎጂ ወገኖች ጎን መሆናቸው የመንፈስ ብርታት ሆነውታል። የሶማሌ ወገኖች የክፉ ቀን አለኝታ መሆናቸዉ በተጎጂዎች ዘንድ የተጠቂ ስነ ልቦና (victimhood mentality) እንዳይኖር፣ በዚህም በዕለት ዕለት እንቅሰቃሴዎች ስሜታዊነት እና ጥላቻ ቦታ እንዳይኖራቸው፣ ህዝቡ በአስተውሎት እንዲጓዝ ያደረጉ ናቸው።
ፈጣሪ ቸር ወሬ ያሰማን!!!


Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading