ሀብታሙ ግርማ፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ት/ክፍል መምህር
ማስታወሻ
ይህ መጣጥፍ March 1, 2019) በ ethiopanorama.com) ጋዜጣ ታትሞ ለአንባቢያን ደርሷል።
እንደ መግቢያ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ማግስት አንስቶ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል። በዋናነትም የፖለቲካችን አይነተኛ መልክ የሆነው የሴራ እና የመጠላለፍ ፖለቲካን ለመቀየር እርምጃዎች ተጀምረዋል። ከዚህ አንጻር በተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ተከታታይ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው። ከውይይቶቹ እንደተስተዋለው መጠላለፍ እና ሴራ መለያው የሆነው ፖለቲካችን አሁንም ለመፈወስ ብዙ ርቀት መጓዝ ያሻዋል።
በዚህች መጣጥፍ አንድ በምናብ የታደምኩትን የፖለቲከኞቻችን የሙግት (ክርክር አላልኩም) መድረክ ለአንባብያን ለማካፈል ነው፤ ዓላማውም የገሃዱን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓት ህጸጾች በማሳየት የተጀመረውን ጤነኛ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መጠቆም፣ በዚያውም የችግሩን ጥልቀት እና ስፋት በመጠቆም የዚህ አገራዊ ፕሮጀክት ባለድርሻ የሆኑ ሁሉ ቀድመው ቢያውቁት(ቢያስታውሱት) ምናልባትም እንዳይታክቱ በሚል ቅን ልቦና ያዘጋጀሁት ነው።
እነሆ ምናባዊ መድረኩ….
በአዳራሹ መድረክ ላይ በሁለት የተከፈሉ ተሟጋቾች ይታዩኛል፤ ክርክሩን ለመታደም የተገኝን በርካቶች የመድረኩ ዙሪያ ገባን በሞላው “መለስ ዜናዊ ማን ናቸው?” እንበል ወይስ “መለስ ዜናዊ ማን ነበሩ? ” የሚለው ጽሁፍ ተስበናል። በግሌ የመድረኩ ጭብጥ እንግዳ ሆኖብኝ ምን ለማለት ተፈልጎ ይሆን? የሆነ የተለየ ነገር አገኛለሁ በሚል የመድረኩን መጀመር በጉጉት እጠባበቃለሁ።
እነሆ መድረኩ በይፋ ተከፈተና አንድ ወጣት ከመድረኩ ጠርዝ ሆኖ መድረኩ ክርክር እንደሆነ፣ ጭብጡም መለስ ዜናዊ ማን ናቸው ? ወይንስ “መለስ ዜናዊ ማን ነበሩ?” እንደሆነ ለታዳሚው ተናገረ።ከእርሱ በግራና በቀኝ ያሉት ሁለት ቡድኖችም ተከራካሪዎቹ እንደሆኑ፣ ደግፈው እና ነቅፈው ስለቆሙለት ሃሳብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ ከእኔ በስተግራ የምትመለከቷቸው መለስ ዜናዊ ማን ናቸው ? ማለት ይገባል የሚሉ ሲሆኑ ከበስተቀኜ የሚገኙት ደግሞ መለስ ዜናዊ ማን ነበሩ?” ማለት ያስፈልጋል ይላሉ። ቀጥሎም ወደ ግራ እና ቀኝ እያማተረ ለያዙት አቋም የሚያቀርቡት አመክንዮ በአጭሩ እንዲያስረዱ በመጠቆም መጀመሪያ ከመድረኩ በስተቀኝ ላሉት ዕድሉን ሰጠ፤ ከመሃላቸውም አንዱ ተነሳና ጉሮሮውን እንደመጠራረግ ብሎ፦
“……ታዳሚያን በእኔና በቡድኔ አባላት ስም እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁ።” እኛ ደግፈን የምንከራከረው መለስ ዜናዊ ማን ነበሩ ? መባል አለበት የሚለውን ነው።መከራከሪያችንም የህልፈታቸው ዜና ከተሰማ ሰባት ዓመታት ገደማ የሆናቸውን ሰው መለስ ዜናዊ ማን ናቸው? ብሎ ማንሳት የአማርኛ ቋንቋን ሰዋሰው (grammatic rule) የሚተላለፍ በመሆኑ ነው ካለ በኋላ ፈጠን ብሎ ተቀመጠ። “
ወዲያው ከበስተግራዎቹ አንዱ ተነሳና የቀኝ ቡድን ተሟጋችን በመንቀፍ ንግግሩን ጀመረ፦
“…….’ተቃዋሚያችን’ ጉልህ ግድፈት ፈጽመዋል፤ መለስ ዜናወን ግለሰብ ብሎ መጥራቱ በሞራልም ሆነ በተጻፈ ህግ ያስጠይቃል። በመሠረቱ ታላቁ መሪ ኢትዮጵያን በመሩበት ሃያ ሶስት አመታት ባሳዩት የላቀ አመራርና መንግስተታቸው ባስመዘገበው ሁሉን አቀፍ የማህበረ ኢኮኖሚ እድገት በአዳራሹ የታደሙት እማኝ ናቸው፤
ከአዳራሹ በተነሳው ገሚሱ ጭብጨባና ገሚስ የተቃውሞ ጩኸት እንዲሁም ማጉረምረም ንግግሩ ተቋረጠ። የግራው ቡድን ተሟጋች ከጩኸቱ አፍታ ሲያገኝ ንግግሩን ቀጠለ፦
“…….እንዲያውም ተከራካሪው ህግ ተላልፏል፤የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቁ መሪ የሚል ማዕረግ ሰጥቷቸው መጠሪያቸው መሆን እንደሚገባ የደነገገውን ተላልፏል።”
ብሎ ሙግቱን በወቀሳና በክስ አሳክሮ ቀጠለ።
“……..እንግዲህ እኔና ሌሎች ጓዶቼ የምንቆመው መለስ ዜናዊ ማን ናቸው? የሚለውን ደግፈን፤ መለስ በህይወት የሉም የሚለውን ነቅፈን ነው።መከራከሪያችንም ‹መለስ ዜናዊ› የሚለው ስም በየጋዜጣው፣ መጽሀፍት፣ የማህበራዊ ሚዲያው፣ በመንግስትም ሆነ በኢህአዴግ እንዲሁም በተቃዋሚ የሚዲያ አውታሮች አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ እያለ ዛሬም እኮ የፖለቲካችን ወግ ማሞቂያ መሆኑ የዛሬም እውነት ነው።”
ከክርክር ጓዶቹ አንዱ ከመቀመጫው ምንጭቅ ብሎ ተነሳና፦
“……. የባልደረባዬን ሃሳብ ለማጠናከር ያህል እንዲያውም’ኮ ‹ከአይን የራቀ ከልብ ይርቃል› ይሏልና የአገሬ ሰው ህልፈታቸው ቢሆን ኖሮ ከልብ ይርቁን ነበር “
ብሎ በተነሳበት አኳኋን ተቀመጠ
ወዲያው ከሙግቱ ታዳሚዎች መካከል አንድ ዕድሜያቸው ጠና ያሉ ግለሰብ ቆፍጠን ባለ ግን በጨዋ ድምጸት ንግግራቸው አዳራሹን ተቆጣጠሩት፦
“…..በቅድሚያ ከመድረኩ መሪ ይሁኝታ ሳላገኝ ለመናገር በመነሳቴ ሁላችሁንም ይቅርታ። ‘መለስ ሞተዋል፤ አልሞቱም ‘ የክርክር ሂደት ምን መምሰል አለበት የሚለው የክርክር አግባብ ካልተበጀለት ጉንጭ አልፋ ክርክር ይሆናል። ከተከራካሪዎቹ እንደተረደዳሁት የክርክርራቸው አግባብ መሠረት የሌለው መሆኑን ነው። ከክርክሩ ፋይዳ ያለው አንዳች ነገር ለማውጣት ያህል የክርክሩን ሂደት መቃኘት ካስፈለገ የክርክሩ ጭብጥ ሚዛን መድፋት፣ ከክርክሩ ለህዘብ የሚጠቅም አንዳች ፍሬ መጠበቅ መቻል፣ ጉዳዩ የህዝብ ጉዳይ መሆኑ፣ በአጠቃላይ ስለ ክርክሩ ተገቢነትና አስፈላጊነት ማንሳት ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ዋናው ጉዳይ የክርክሩ ሂደት የተገራ መሆኑ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የክርክሩ መገራት የክርክሩን ጭብጥ ፋይዳና አግባብ፣ ለዲሲፕሊንና ለክርክር መርሆኖች የማስገዛት ግዴታዎችን ይጥላል፤ ተከራካሪዎቹን ለተስማሙበት እንዲገዙ ግዴታ ይጥላል፣ ለሚፈጸም መተላለፍ ወይም ጥፋት እንዲቀጡበት መነሻ ይሆናል፤ በአጠቃላይ የክርክሩ ሂደት በመደማመጥ እና በመከባበር እንዲሆን ያደርጋል፡፡ “
እኚህ ተናጋሪ በንግግራቸው ሰፋ ያለ ጊዜ ቢወስዱም ታዳሚው የተሰላቸ አይመስልም፤ የንግግራቸው መልዕክት የሁሉም ታዳሚ እንደሆነ በግልጽ ይስተዋላል። ነገር ግን ወዲያ ከመድረክ በሁለት ጎራ ተከፍለው የሚታዩት ሁሉም ማለት ይቻላል በሰውየው አስተያየት የተበሳጩ እንደሆኑ በፊት ገጽታቸው በግልጽ ይነበባል።
አንደበተ ርቱዕ የሆኑት ተናጋሪ ሃሳባቸውን ሰብሰብ ሐማድረግ እየሞከሩ ንግግራቸውን ቀጠሉ፦
…..እንግዲህ ክርክሩ መገራት አለበት ሲባል ሁለት ነው። በመጀመሪያ የክርክሩ ጭብጥ አግባብ በግልጽ መቀመጥ አለበት፤ ሁለተኛ ተከራካሪዎቹ ለክርክር መርሆች መገዛት አለባቸው። ይህ ሲባል የሚፈልጉትን ብቻ መርጠው መስማት የለባቸውም፤ ቢያንስ የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን በተቃራኒ ያለን ሃሳብ ለመስማት ዝግጁነት ያስፈልጋቸዋል፤ አንዱ ሌላውን ሊረታበት የሚችልበት ማስረጃ (ጽንሰ ሃሳብ ፣ ሃልዮት እና/ወይም የፖለቲካ ርዕዮት ሊኖረው ይገባል፤ ይህም ክርክሩ በምክንያትና በውጤት እዲቃኝና አሰልቺ እንዳይሆን ደርገዋል፡፡ መደማመጥ ካልተቻለ፣ የሃሰብ የበላይነትን ለመቀበል፣ ካልሆነ እንካ የሃሳብ ልዩነትን አክብሮ ለማስከበር የሚስችል ስብዕናን ይጠይቃል፡፡
እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ቢያንስ ሁለት ተደጋጋፊ ውጤቶች ይከሰታሉ፡፡ አንደኛው ሁለቱም ተከራካሪዎች ቢያንስ የተነሱበትን ነጥብ ከነቀፌታ ከመታደግ በቀር ሌላኛውን ለማሳመን መረጃ ቢኖራቸው እንካ ማስረጃ የሚያገኙ አይመስልም፤ በውጤቱም ጉንጭ አልፋ ከመሆን በቀር ለራሳቸው ለተከራካሪዎቹ ምንም አይነት ስትራቴጂያዊ ጥቅም ሆነ ግብ አያስገኝም። ይህ ሙግት ምክንያትም፣ውጤትም፣መቋጫም እንዲኖረው የሚያደርገው መሰረት ወይም መነሻ ወይም አግባብ አይኖረውም። በውጤቱም ክርክሩ አስፈላጊነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፤ ታዳሚን ያሰለቻል፣ ያስቆጣል፣ ሲከፋም ለመንጋ ውዝግብ (mass confusion) ይዳርጋል፤ ተራ ጭቅጭቅ ሆኖ ይቆያል እንጂ ርትዕ አይኖረውም፡፡”
ብለው ንግግራቸውን በጽሞና ያዳመጧቸውን የአዳራሹን ታዳሚ በማመስገን ቋጩ።
መድረኩ ቀጥሏል፤ ነገር ግን የክርክሩ ተዋንያን የእኚህን በሳል ሰው ምክረ ሀሳብ ከመጤፍ የቆጠሩት አልነበረም፤ እንዲያውም ከታዳሚያኑ አስተያየት ለመቀበል አለመፈለጋቸው በገሃድ ይስተዋላል። በግራም ሆነ በቀኝ ተሰይመው የሚሟገቱት ቡድኖች የሚያነሱት ነጥብ ሁሉ የሚፈልጉት እንጂ ቆመንለታል የሚሉት የክርክር ጭብጣቸውን የሚያስረዳ አይደለም፤ በመድረኩ ላይ መደማመጥ የሚባል ነገር የለም።
ጊዜ በነጎደ ቁጥር በአዳራሹ የታደመት ተከራካሪዎቹ ለራሳቸውም ሆነ ቆመንለታል ለሚሉት ሃሳብ ግልጽ ወይንም የታመኑ አልመስል እያላቸው እንደሆነ የሚጠቁሙ ፍንጮች እየታዩ ናቸው፤ በታዳሚው የፊቱ ገጽ ላይ በክርክሩ ሂደት መሰላቸቱ ጎልቶ ይነበባል፡፡ ተከራካሪ ወገኖቹ የጋበዟቸውን ታዳሚዎቻቸውን ስሜት ለማንበብ ይቅርና በአካል አብረዋቸው ስለመኖራቸው ለማወቅ የሚችሉ እና/ወይም ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም፤ የህዝቡን ፊት አንብበው አጸፋ ለመመለስ የሚያስችል አቅል ወይም ተነሳሽነት ያላቸው አይመስልም፤ አልያም እንግዶቻቸውን ንቀው አይተው እንዳላዩ ቸል ብለው አልፈውታል፡፡
አብዛኞቹው ታዳሚያን ከጭብጥ አንጻር የጠበቁትና ያገኙት የሞት እና የህይወት ያህል ርቆባቸዋል፤ በተከራካሪዎች ቅንነት ማጣት አልያም የመሳለቅ ሙከራ ወይም ንቀት ክፉኛ የበገኑት በንዴት ከአዳራሽ ውልቅ ብለው መውጣትን መርጠዋል፤ እናም አብዛኛው የአዳራሹ ክፍል ባዶ ሆኖ ይታያል፡፡ በአዳራሹ መቆየት የመረጡት ጥቂቶች የተከራካሪዎቹ ቲፎዞዎች ሳይሆኑ አልቀረም፤ ይህ ቡድን የሚነቅፈው ወይም የሚደግፈው ሃሳብን ሳይሆን በመድረኩ ላይ የተሰየሙትን ግለሰቦች ነው፤ በመሠረቱ ግቡን ያደረገው የክርክሩን ዘዋሪዎች ተገን በማድረግ የግል ጥቅሙን ለማሳካት ነው። በአዳራሹ የቀሩት ጥቂቶች የመቆየታቸው ምክንያት አልገለጥ ብሏቸው እና/ወይም የመሰላቸታቸው ጣራ ከአዳራሽ ሊያስወጣቸው ጫፍ ደርሳል፡፡
“መለስ ሞተዋል፤ አልሞቱም” የክርክር ሂደት እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት መልክ
የአዳራሹ ክርክር ሂደት መልክና ገጽታ፤ መነሻና መድረሻ በስሪቱ ልሂቃዊነት(elitism) እንጂ የህዝብ ተሳትፎ ኢምንት የሆነበትን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት መልክ በደንብ የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ የክርክሩ ጭብጥ የሚያከራክርና የሚያወያይ ውስብስብ ሆኖ ሳይሆን፣ በዚህም ለመረዳት እና ለማስረዳት አስቸጋሪ ሆኖ ሳይሆን በቅንነት እጦት ብቻ ከብዶን ያከበድነው የፖለቲካ አጀንዳዎቻችንን ይወክላል፡፡
የክርክሩ ሂደት በተለያየ አሰላለፍ የሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃኖቻችንን የህዝብን ሃይልና ክብር በአግባቡ ሳመዝኑ የህዝብን አንገብጋቢ ችግሮች የምር የፖለቲካ አጀንዳቸው ሳይሆን እርስ በርስ በመጠላለፍ ባክነው ሃገርና ህዝብን የሚያባክኑ የሆነበትን የፖለቲካ ስርዓቱ አሳዛኝ ገጽታን ይገልጻል፡፡ የክርክሩ ሂደት የፖለቲካ አጀንዳ የህዝብ አጀንዳ ሳሆን ተገዳዳሪን ለማደናቀፍ የሚሰነዘር የታክቲክ መሰናክል የሆነበት፣ የክርክር (የመተገገል) መነሻ መሰረት የሌለው፣ በዚህም የፖለቲካ ጽንፈኝነት የሚስተዋልበት፣ የሃሳብ የበላይነት ወይም የህዝብ ጉዳይ ሳይሆን የግለሰቦች ወይም የፖለቲካ ቡድኖች ጠልፎ የመጣል አቅም ወይም ሸፍጥ አሸናፊ የሚያደርግበት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስርዓት ምስልን ያሳየናል።
በአዳራሹ የታደሙት በመድረክ ላይ ሆነው ለክርክር በተቀመጡት ላይ የነበራቸው ሚና አናሳ(ወይም የሌለ) መሆኑ፣ ማለትም ታዳሚው ተከራካሪዎችን መዳኘት፣ መገሰጽ፣ ማረም የማይችልበት መሆኑ በፖለቲካ ተማጋቾች (አክቲቪዝቶችና) እና ሌሎች አካላት አሳታፊነቱ አነስተኛ ነው ብለው ወቀሳ ለሚሰነዝሩበት የፖለቲካ ስርዓታችን አንደኛ ገጽ የሚወክል ነው፡፡ ቅይማቱን፣ቅሬታውን፣ ንዴቱን፣ ብሶቱን ለመግለጽ እድል ተነፍጎኛል በሚል ራሱን ከአዳራሹ ማግለል የመረጠው ታዳሚ ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቁ ብሎ የደመደመውን ዜጋ ይወክላል፤ በቲፎዞነት በአዳራሹ መታደምን የመረጠው ጉምቱ ፖለቲከኞችንና የሚመሩትን የፖለቲካ ቡድን ተገን አድርጎ የግል ጥቅሙን የሚያሳድዱትን ለመግለጽ ነው፡፡ ከአዳራሹ ለመውጣት አያመነታ ያለው ስብስብ ከዛሬ ነገ ለውጥ ይመጣል ብሎ ሲጠብቅ የኖረ፣ ነገር ግን በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ትዕግስቱና ተስፋው በመማጠጥ ላይ ያሉትን ይገልጻል፡፡
በመሰረቱ የምናባዊው ክርክር ከመድረክ ሆነው የሚዘውሩት ተማጋቾች የክርክር ጭብጡን፣ ማለትም “መለስ ሞተዋል፤ አልሞቱም” የተረዱት እና/ወይም ለመረዳት የፈቀዱት ጉዳዩን ከመደገፍ አንጻር እና/ወይም ጉዳዩ ከሚመለከተው ህዝብ ጥቅም አንጻር አይመስልም፡፡ ዛሬ የህልፈታቸው ሰባተኛ ዓመት በሆነበት ወቅት መለስ ዜናዊ ማን ናቸው መባሉን ባለማወቅ ይሁን በሌላ ምክንያት የሰዋሰው ህግ ይጥሳል ብለው ሙግት የገጠሙቱ አንድም ጤንነታቸው የሚያጠራጥር ወይም ክርክሩን ለፌዝ ወይም ለራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ሲሉ ጊዜ የመግዣ ወይም ሃሳብ ማስቀየሪያ የተጠቀሙት እንደሚሆን ይታመናል።
በተቃራኒ ሆነው ለሚሞግቱትም እንዲያው ነው፤ ዛሬም ሆነ ለመጪው ጊዜ የመለስ አስተምህሮ አሁንም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የደህንነትና መከላከያ መመርያ መሆኑ መለስ ቢያልፉም እሳቤያቸው ግን ህያው ነው ብለው ቢሞግቱ መከራከሪያቸውን ውሃ የሚቋጥር ሊያደርገው አቅም ቢሆነውም ለምን?እንዴት? በምን መልኩ? ወዘተ ሊነግሩን አልቻሉም ወይም አልፈለጉም። ምክንያቱ የቅንነት፣የመረዳትና የመተንተን ብቃት፣ ዝግጁነት፣ ከወገንተኝነት ነጻ መሆን ችግር ይሁን በሌላ በራሱ ግራ አጋቢ ወይም አጨቃጫቂ ነው። ያም ሆነ ይህ በበርካታ ምክንያቶች ክርክሩ ርትዕ የሚኖረው አይመስልም፡፡
ይህን አሰልቺ ክርክር ለመታደም በአዳራሹ የተገኙት በጣም ያልታደሉ ናቸው!
በእርግጥ ዛሬ ሰባተኛ የሙት ዓመታቸውን ለማሰብ ወራት ብቻ በቀረበት ወቅት መለስ ዜናዊ ማን ናቸው ወይስ መለስ ዜናዊ ማን ነበሩ አይነት ሙግት ማንሳቱ ከላይ ከላይ የሞኝ የሚመስል ግን ውስጡን ዘለቅ ብለን ስንፈትሸው ግን ብልህ እንካ ባያስብል ሞኝ ግን አያስብልም፡፡ የተቃርኖው ልክ በህይወት እና በሞት ያህል የሰፋ ይመስላል፤ የክርክሩ ሂደት ከላይ በተጠቀሰው አግባብ ቢገራ ኖሮ ግን የተቃርኖው ልክ በእጅጉን ይጠብ ነበር፤ እንዲያውም የሃሳብ ልዩነቱ ይመጣ የነበረው ከጭብጡ ግርድፍ አረዳድ ሳይሆን ውስጡ ከያዘው ወይም ለመጠቆም ከሚሞክረው ጉዳይ አንጻር ነው፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ነገሩን ያወሳሰቡትና ያልተገባ ጽንፍ ፈጥረው ተቸግረው ታዳሚውን የሚያስቸግሩት ራሳቸው ተከራካሪዎቹ ናቸው፤ አብዛናው ተግባራቸው የሚያመላክተው እንዲያውም ወደ ክርክሩ መድረክ ሲወጡ በአላማቸው ጭብጣቸውን ለማስረዳት ወይም ለመከላከል አይደለም።
ጉዳየቸው አቶ መለስና እሳቤያቸው ቢሆንማ አቶ መለስ ምትሃት ሆነውባቸው ዛሬ ህልፈታቸው ከሆነበት ከአምስት አመት በሃላ በህይወት አሉ-ሞተዋል የሚሉት ሁለት ቡድኖች የፌዝ ጨዋታ አይሞክሩትም ነበር፤ ሞተዋል ብለው የሚሞግቱት ፌዘኛ ባይሆኑ ኖሮ የሞተ ሰው ተነሳ ሲባሉ ለሙግት የመቀመጥ ወኔ ይቅርና መልስ ለመስጠት እንኳ ባለመፈለግ ጨዋታውን ይዘጉት ነበር፡፡ በህይወት አሉ የሚሉትን መለስ ሟች የማይሆኑበትንና በዚህም ከሰው ልጅ የሚለዩበትን ተዓምር ተገልጦላቸው ለታዳሚው ለማብሰር ሲሰናዱ ጊዜው አልበቃ ብሏቸው ይሆናል ብለን ቀድመን በምክንያት እንሳለቅባቸው፤ የክርክሩ ጭብጥ መሆን የነበረበትን ለመረዳት የሚያስፈልገው ቅንነት ብቻ ነው፤ ታዳሚው ይገባው የነበረው በጉጉት ይጠብቅ የነበረው መለስ ሞተዋል-አልሞቱም ሲባል ከእሳቤዎቻቸው አንጻር እንጂ ከእስትንፋሳቸው መቆም ወይም መቀጠል መሆኑን መግለጽም በራሱ በጣም አናዳጅ ብቻም ሳይሆን የፌዘኞቹ ቲፎዞ መሆንም ጭምር ነው፡፡
ርትዕ አልባ የሆነው ክርክር አገራዊ መግባባት እንዳይኖርና የጥላቻ ፖለቲካ ስሩን የሰደደደበትንና ያን ያህል የገነነ ልዩነት ሳይኖር ነገር ግን ልሂቃኑ እንዲሆኑ ስለፈለጉ ብቻ ጽንፍ ይዘው የሚታዩ የፖለቲካ ልዩነቶችን የሚያሳይ፣ በዚህም ሃገራዊ መግባባትን ለማምጣት ጋሬጣ የሆነበትን መነሾዎች ያመላክታል፡፡ በክርክሩ ሂደት ከሁሉም የከፋ ተጽዕኖ የሚኖረው ያለተገራ መሆኑ የፖለቲካው ታዳሚዎችን፣ ማለትም ዜጎችን ከፖለቲካ አዳራሹ ማራቁ ነው፡፡ በእርጥም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ የሚል እምነት መያዙ የፖለቲካ ልሂቅነትን የሚያጎለብት መሆኑ ነው፡፡

አስተያየት ያስቀምጡ