ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Find articulated views on the Fabrics of Ethiopian society & the world at large. There is no limit of topics of address: culture, lifestyle, history, art, literature, politics and economy. Habtamu Girma's page shares opinions, viewpoints, and/or commentaries on issues that matters for us all!!!

ሩህ ሚዲያ የተለያዩ የዲጂታል የብዝሃ-መገናኛ አማራጮችን በመጠቀም በአፍሪካ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አስተዳደርና ፖሊሲ፣ ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ጂኦ-ኢኮኖሚክስ፣ ጂኦ-ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ በእውቀትና በዕውነት የተቀረጹ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስን ዓላማው ያደረገ ሚዲያ ነው፤ ዓላማውም በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ የሚኖረን ግንዛቤ በጥናትና በዕውቀት የተደገፈ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ነው፤ በሩህ ሚዲያ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳቦች እና የፖሊሲ እርምጃዎችን በቀላሉ ህዝብ በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል // Ruh Media is aimed at addressing contextual factors associated to African economy, politics, geo-economics, natural resource conservation & management, climate change and energy transition issues. Ruh Media produces original contents capturing the human stories behind statistics, and showing how continental (African) and Ethiopian specific developmental aspirations translate into community-level change // የሩህ ሚዲያ ድህረ ገጽና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ይጎብኙ፤ ይወዳጁ!

የኢትዮጵያ ታሪክ እና የታሪክ ጸሀፍት (ምሁራን) ግምገማ ********

ሀብታሙ ግርማ
ነሐሴ፣ 2007 ዓ.ም
ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ

መጽሐፍ ዳሰሳ (Book Review) በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› መጽሀፍ ላይ

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ማህበር (Ethiopian Economics Association). የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ማስተባበሪያ (ቻፕተር ) ባሰናዳው የፓናል ውይይት የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ

  1. መግቢያ
    1.1 ስለ ደራሲውና ስለ መጽሀፉ አጠቃላይ
    በአማርኛ ቋንቋ ከሚጽፉ እጅግ ጥቂት ኢትዮጵዊያን ምሁራን መካከል አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚጽፋቸው በሳል ጽሁፎችና በሚያነሳቸው አዳዲስ ጉዳዮች የምሁርነትን ልክ ያሳዩን ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በየሁለት አመቱ ልዩነት ማለት ይቻላል በተከታታይ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ መጽሀፍትን አስነብበውናል፡፡ዘንድሮም (ማለትም በ 2007 ዓ.ም) ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› በሚል አዲስ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡
    ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› በአስር ምዕራፎችና በ280 ገጾች የተደራጀ ሲሆን በግራፊክ አሳታሚዎች ለህትመት በቅታል፡፡ ‹አዳፍኔ› ፕሮፌሰሩ በ2005 ዓ.ም ያሳተሙት ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሀፋቸው ተከታይ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ለዚህም ሁለት አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ከጭብጥ አካያ ብዙ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹አዳፍኔ› ከያዛቸው አስር ምዕራፎች ውስጥ ሶስቱ (ይህም የመጽሀፉን ዘጠና ስድስት ገጾች ወይም 40 በመቶ ያህል ይሸፍናል ማለት ነው) በ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ላይ በተለያዩ ጸሀፍት ለተሰነዘሩ ትችቶች ምላሽ የሰጡበት( በመጽሀፉ እንደተገለጸው የ‹ ትችቶች ትችት›) ነው፡፡
    በዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ አተያይ የመጽሀፉ ዋነኛ መገለጫዎች(መልኮች) ሁለት ናቸው፤ እነዚህ ሁለት መገለጫዎችም የመጽሀፉ ውበቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሀፉ በይዘቱ ሰፋ ያለ መሆኑ ነው፤ ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሁለተኛው መጽሀፉ በቅርጹና አቀራረቡ የራሱ የሆነ አዲስ ቀለም ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ይነካል፤ ታሪክ፣ ባህል፣ ስልጣንና አገዛዝ (ፖለቲካ)፣ኢኮኖሚክስ፣ ስነ መንግስትና አስተዳደር (አገር፣ ህዝብና መንግስት)፣ ሀይማኖት፣ ትምህርትና ዕውቀት እንዲሁም ዕውነት፣ ስነ-ልቦና፣ ፍልስፍና እና ሌሎች የጥናት ዘርፎች ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጽንሰ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ ሌላው የመጽሀፉ መልክ ለጥናትና ምርምር፣ ለጥልቅ ውይይትና ክርክር የሚጋብዙ ሀሳቦችን ማንሳቱና በዚሁ በተቃኘ አቀራረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡
    1.2 የመጣጥፉ ዓላማ
    ወጣቱ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍ ዙሪያ ያለውን አተያይ ከሁለት አመታት በፊት ገደማ በአንድ መጣጥፉ አስነብቦናል ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል በመጣጥፉ ካነሳቸው በርካታ ቁም ነገሮች አንዱ የክሽፈት ታሪክ እንጂ የታሪክ ክሽፈት የሚባል ሊኖር አይችልም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፋቸው ‹የትችቶች ትችት› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ለዚህ መልስ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን መልሱ አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይህ ሲባል ግን ፕሮፌሰሩ መልስ አልሰጡም ለማለት ሳይሆን የተሰጠበት አግባብ የተደራጀና ግልጽ አይደለም፤ እንዲያውም የአዳፍኔ ዋነኛ ጭብጥ በክሽፈት ታሪክና በታሪክ ክሽፈት ዙሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሀሳቦቹ እዚህም እዚያም ተበታትነው የቀረቡ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አንባቢ የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረው ያደርጋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
    በዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ እምነት የክሽፈት ታሪክ እና የታሪክ ክሽፈት የሚሉት ሁለት ሀሳቦች ብዙ ጉዳዮችን ያዘሉ በመሆናቸው በጥልቀት መታየት አለባቸው፡፡ በመሆኑም አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ስለ ክሽፈት ታሪክና ስለ ታሪክ ክሽፈት ያነሳቸውን ሀሳቦች በማሰባሰብ ለማቅረብ ተሞክራል፤ መጽሀፉ ከአደረጃጀት አንጻር በዚህ ሁኔታ ቢቀርብ መልዕክቱን በይበልጥ ለመረዳት ያስችላል ፤ በመጽሀፉ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በአንባቢያን የሚቀርቡ የውይይትም ሆነ የክርክር ሀሳቦች ቅርጽ እንዲይዙ ለማድረግም ያግዛል፡፡ የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ የታሪክ ክሽፈት፡ ከኢትዮጵያ አንጻር በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የደራሲውን እይታዎችን አጠቃሎ በማቅረብ ለውይይት እንዲመች ማድረግ ነው፤ በመጽሀፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ትዝብት ማስፈር የሚለው ሌላው የመጣጥፉ ግብ ነው፡፡
    1.3 የመጣጥፉ ይዘት
    የመጣጥፉ ይዘት የተቃኘውም ከላይ ለማንሳት ከሞከርኩት ዓላማ አንጻር ነው፡፡ በዚህም በዚህ አጭር ጽሁፍ ለሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ተሞክራል፡፡
     የታሪክ ምንነትና ዓላማ ምንድነው?
     የታሪክ ክሽፈትና የክሽፈት ታሪክ ማለት ምን ማለት? ቁርኝታቸውስ እንዴት ነው ?
     የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር እንዴት ይታያል ?
     ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ተጠያቂው ማነው ?
     የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈቶችና መዘዞች ምንድናቸው ?
     ከታሪክ ክሽፈት ለመውጣት ምን ማድረግ ያሻል ?
     የመጽሀፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች
    በቅድሚያ ግን ስለታሪክ እና ተያያዥ ጉዳዮች አንዳንድ ሀሳቦችን በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
  2. ስለ ታሪክ ምንነት፣ ባህሪያትና ዓላማ
    2.1 ስለታሪክ ምንነትና ዓላማ
    የታሪክ ፍልስፍና ዘይቤ አባት በመባል የሚታወቀው አውግስሚኖስ የታሪክ ምንነትና ዓላማ ሲገልጸው እንዲህ ነው፡-
    ታሪክ መንግስት መቆሙንና መፍረሱን፣ ህዝቦች ማደጋቸውንና መውደቃቸውን ያትታል፡፡ይህም የሚሆንበት ምክንያት አምላክ ባቀደው መሰረት የሰው ዘር ወደ እውነተኛው ብርሃን ለመምራትና ለማዳን ሲል ነው፡፡
    የፕሮፌሰር መስፍን የታሪክ ምንነትና ዓላማ አረዳድም ከአውግስሚኖስ ጋር በይዘቱ አንድ ነው፣ ቅንቃው ቢለወጥም፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ማለት ፡-
    “…..ለአንድም ሰኮንድ የማያቃርጥ የኑሮና የአናናር ጅረት ነው፡፡ ……..ታሪክ አንድ ህዝብ የስራ መዝገብ ነው፡፡” ገጽ 98-99
    የታሪክ ዓላማ ደግሞ ህዝቡ ያለፈውን ዘመን ከፍታና ዝቅታ አስታውሶ፣ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ በጎ ጎኖች ትምህርት ወስዶ፣ ከችግሮቹ ተምሮ በኑሮው መሻሻል እንዲያሳይ ማድረግ ነው (ገጽ 28፣ ገጽ29 )፡፡
    በአጠቃላይ፡-
    • ታሪክ ማለት የትናንት ዕውነትን (በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ) መመርመር ነው፡፡
    • የታሪክ ዓላማ የሰው ልጅ የትናንት በጎ ተግባራቱን አዳብሮ፣ ከስህተቱ ደግሞ ተምሮ የዛሬና የነገ ህይወቱን እንዲያቀና ማድረግ ነው፡፡ በዚህም አውግስሚኖስ የታሪክን አስፈላጊነትና ዓላማ ከመለኮታዊ ሀይል ዓላማ ጋር ያዛምደዋል፡፡ በዚህም የታሪክ ዓላማ የፈጣሪ አላማ ነው፡፡
    በተለይ ሁለተኛው ሀሳብ ከታሪክ አረዳድ አንጻር ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን በጉዳዩ ላይ ትንሽ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
    2.2 ስለ ታሪክ ባህሪያት
    በግሌ የታሪክ ባህሪ ከአምላክ ባህሪ ጋር ይመሳሰሉብኛል፡፡ ታሪክ አምላካዊ ባህሪዎችን ሁሉ ይወርሳል፡፡ ታሪክን ከአምላከዊ ባህሪ ጋር ለማንጸር ያደረግሁት ጥረት ያልተመቻቸው እንደኔ እንደኔ የአምላክን ባህሪ የማያውቁ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ለመሆኑ የአምላክ ባህሪያት ምንድናቸው ? የታሪክ ባህሪያትስ ?
    በመሰረቱ የአምላካዊነት መሰረት ሀቅ ነው፤ የታሪክ መሰረቱም አንዲሁ ሀቅ (እውነት) ነው፡፡ ፈጣሪ የሰው ልጆችን ጨምሮ በአጠቃላይ በፍጡራን ላይ ፍጹም ስልጣን አለው፤ ታሪክም ይህ ስልጣን አለው ፡፡ የፈጣሪ ዓላማ የሰው ልጆቸ ሁሉ በቀና መንገድ እንዲያልፉ ማስተማር ነው፤ የታሪክ ዓላም እንደዚሁ ነው፡፡ ወደር የለሽ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት አምላካዊ ባህሪ ነው፤ ዓላማውም ሰዎች በራሳቸው ከጥፋት መንገድ እንዲታቀቡ፣ ካለፈው ስህተታቸው እንዲታረሙ ጊዜ መስጠት ነው፡፡ የታሪክ መንገድም ይህ ነው፡፡ በመሰረቱ ዕውነትን(ታሪክን) መበረዝ ወይም ማጥፋት የሚቻል ሊመስለን ይችላል፡፡ መሪዎችም ይህን ለማድረግ የቻሉ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን በጥልቀት ከመረመርነው አልቻሉም፡፡ የፈጣሪን ትዕግስት ዓላማ ያልተረዱም በስህተት ላይ ስህተት ላይ እየፈጸሙ በመጨረሻም ከነጭራሹ የፈጣሪን ስልጣን ሲመኙ፣ ሲብስም ህልውናውንም ሲክዱ መቀበሪያቸውን ጉድጋድ እያበጁ እንደሆነ ሳይታወቃቸው፣ የትዕግስቱ መብዛትም በቆፈሩት ጉድጋድ እንዲቀበሩ ያደረጋቸዋል፡፡ የታሪክም መንገድ ይህ ነው፡፡ ታሪክ ከስህተት ለመማር እድል ይሰጠናል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ግን በቆፈሩት ጉድጋድ ይቀበራሉ፡፡ በታሪክ ማህደር እንደተዘከረው በታሪክ ላይ የዘመቱ ሁሉ መጨረሻቸው መጥፋት ነበር፡፡ በእርግጥም በዘመናት ሂደት ያለፉ፣ ታሪክ ላይ ያመጹ አገዛዞችና ነገስታት አነሳስና አወዳደቅ ለመረመረ ይህ ይገለጥለታል፡፡ ታዲያ የፈጣሪ የቅጣት በትር ፍጹም ፍትሃዊ እንደሆነው ሁሉ የታሪክ ቅጣትም ጊዜ ወይም ቦታ የማይቀይረው፣ ለማንም የማይወግን ፍጹም ፍትሃዊ ነው፡፡ ትናንትም ይሁን ዛሬ በታሪክ ላይ ያመጹ ሁሉ በጥፋታቸው ልክ ተቀጥተዋል፤ ነገም እንዲሁ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡
  3. የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት
    3.1 የታሪክ ክሽፈት ሲባል……
    እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ የታሪክ ክሽፈት ሲባል፡-
    “…… ምንም ያልተመዘገበ ነገር መኖሩ፤ ታሪኩ ከበላ-ጠጣ-ተነሳ- በላ-ጠጣ-ተኛ….. የማያልፍ ሲሆን ወይም በላ-ጠጣ-ተኛ-ተነሳ-ተራበ-ተጠማ ብቻ ሲሆን (ነው) “ገጽ 99
    ከዚህ ገለጻ እንደምንገነዘበው የታሪክ ክሽፈት ምንነት ሁለት ምሰሶዎች አሉት፡፡ አንደኛ የታሪክን ምንነት አለመገንዘብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የታሪክን አላማ አለመገንዘብ ነው፡፡ ምንም ያልተመዘገበ ነገር መኖሩ ከሚለው ሀረግ የምንረዳው የታሪክ ክሽፈት ፕሮፌሰሩ ትክክለኛ የታሪክ አረዳድ (ከላይ ለማሳየት እንደሞከርሁት ) ብለው ባስቀመጡት ልክ ሳይሆን ሲቀር ወይም የህዝብ የዘመናት የኑሮ ውጣ ውረድ ሳይመዘገብ ሲቀር ነው፡፡ ታሪኩ ከበላ-ጠጣ-ተነሳ- በላ-ጠጣ-ተኛ ወይም በላ-ጠጣ-ተኛ-ተነሳ-ተራበ-ተጠማ ብቻ ሲሆን የሚለው ሌላኛው የታሪክ ክሽፈት ምሰሶ የሚያመለክተው የታሪክ ዓላማን ከመሳት አንጻር ነው፤ ካለፈው ዘመን በጎና በጎ ያልሆኑ ተግባራት ትምህርት መቅሰም ሳይቻል ሲቀር ነው ፡፡
    3.2 የክሽፈት ታሪክ ሲባል….
    የክሽፈት ታሪክ ማለት በመጽሀፉ ገጽ 28 ላይ እንደተመለከተው በዘመናት ሂደት የህዝብ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ከመሻሻልና ከማደግ ይልቅ ቁልቁል ሲወርድ፤ የሃለኛው ትውልድ ከቀደመው ትውልድ በአንጻራዊነት የተሻለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ህዝቡ የመንፈሳዊና ቁሳዊ ብልጽግናው እየከዳው ሲሄድ የሚያመላክት ነው፡፡
    3.3 የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት ቁርኝት…….
    በአዳፍኔ መጽሀፍ ተደጋግሞ እንደተነሳው በኢትዮጵያ ህዝብ የትውልድ ቅብብሎሽ ህዝቡ በመንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሀብቱ ከመሻሻል ይልቅ እየተዳከመ የመጣ ህዝብ ነው፡፡ ይህም የክሽፈት ታሪክ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የክሽፈት ታሪክ ምን ወለደው ለሚለው የፕሮፌሰሩ መልስ ይህ ነው፡-
    “….በዋናነት የመክሸፍ ምንጩ ሀለት ይመልሰለኛል፤ አንደኛው ትናንትን አለማስታወሰ ይመስለኛል፤ ሁለተኛው ነገን አለማሰብ፤ ትናንትን አለማስታወስ ማለት ታሪክን አለማወቅ (ነው) ….. ክብርና ኩራትን ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብና ሳንመዝን ለማይገባው (መስጠት ነው) ፤ በውጤቱም የሰራው እየተረሳና እየኮሰሰ፣ ያልሰራው እየተወሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤……… ስለዚህም መስራት የማያስከብርና የማያከብር ይሆናል፡፡” ገጽ 73
    ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የታሪክ ክሽፈት ለክሽፈት ታሪክ ሰበብ መሆኑን ነው፡፡ እናም በታሪክ ክሽፈት ውስጥ የከሽፈት ታሪክን እናያለን ማለት ነው፡፡
  4. የታሪክ ክሽፈት ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር
    4.1 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ማሳያዎች …..
    ኢትዮጵያ የሶሰት ሺህ ዓመት ያላት አገር ናት፡፡ እንዲያውም በ2012 ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹The Hidden History of Ethiopia and Jews> በተሰኘው መጽሀፋቸው የኢትዮጵያ ታሪክ እስከ አራት ሺህ ዓመት ይደርሳል; ምን ይመስላል› ፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ታሪክ የትናንታን ኢትዮጵያ በጊዜና በቦታ ርቀት የሚስቃኝ ነው ወይስ….. ታሪካችን በይዘቱ የህዝቡን የዘመናት የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ በተማላ ሁኔታ የሚዘግብ ነው ወይስ…..የኢትዮጵያ ታሪክ አገሪቱና ህዝቦቻ በዘመን ሂደት ያለፉበትን ከፍታና ዝቅታ ትክክለኛ ምስል ያሳየናል ወይስ……. ከታሪክ ማህደራችን የትውልዶችን ሽግግር ማየት እንችላለን ወይስ……..፣ የታሪክ ትርክቱ ተዓማኒነት እስከምን ድረስ ነው….. የሚሉትን ጉዳዮች መመርመሩ የኢትዮጵያን የታሪክ የክሽፈት መንገድ የሚጠቁመን ይሆናል፡፡
    ከአደፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ታሪክ በጊዜና ቦታ ርቀት፣ በይዘት ጥልቀት እንዲሁም በተዓማኒነት ሚዛን ሲለካ ብዙ ጎዶሎዎች ያሉት መሆኑ የክሽፈቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ከመጽሀፉ በመጠቃቀስ ለማሳየት ልሞክር፡
    ሀ) ከጊዜና ቦታ ርቀት አንጻር የኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ምስል በአግባቡ አያሳይም፡-
    “የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው ከመሃሉ ወይም ከአሁኑ ነው፡፡” ገጽ 97
    ለ) ከይዘት ጥልቀት ሚዛን አካያ ከፈተሸነው ታሪካችን ጎዶሎ ነው፡፡ የነገስታትና የጦርነት ጉዳዮችን እንጂ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ የኑሮ ውጣ ውረድ ከታሪክ ድርሳናት አናገኝም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን ሲገልጹ፡-
    “….ኢትዮጵያዊያን ብዙ የምንኮራበት ታሪክ አለን፡፡ ዞሮ ዞሮ የኩራታችንና የክብራችን ታሪክ አገራችንን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክለን ከማቆየታችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በትምህርትና በምርምር፣ በስነጽሁፍና በስነትበብ፣ በዕውቀትና በፍልስፍና ኑሮነ ለማሻሻል በሚያስፈልጉ ዘዴዎች ፣ በመመላለሸና በመገናኛ ዘፈዴዎች፣ በምህንድስና በእጅቨ ስራ……ወዘተ ምንም ዓይነት እድገትና መሻሻል አለማሳታችን ታሪካችን አያወሳም፡፡ “ገጽ 28
    ሐ) የተመዘገበው ታሪካችን ጥሩ ጥሩውን ብቻ እንጂ ድክመቶታችንን የሚያሳየን አይደለም (ገጽ 28)፡፡
  5. ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ ማነው?
    5.1 አዳፍኔና የታሪክ ከሽፈት……..
    ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ ናቸው የሚላቸው ሶስት አካላት በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞች(መሪዎቸ)፣ ህዝቡ እንዲሁም የታሪክ ጸሀፊያን (ምሁራን)ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጀርባ ሆኖ የታሪክ ክሽፈቱን የሚያፋጥነው ደግሞ አዳፍኔ ነው፡፡ ለታሪክ ክሽፈት ተባባሪ የሆኑት ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካላት እንዴት ለታሪከ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ አደረጉ የሚለውን ከመቃኘታችን በፊት የአዳፍኔን ምንነትና ባህሪያት ማወቁ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ አዳፍኔ ማነው?
    5.1.1 አዳፍኔ ማነው?
    በመላው ዓለም በተለይም በአፍሪካ መሰረቱ ሰፊ እንደሆነ የሚነገርለት አዳፍኔ ትውልዱ የትና መቼ እንደሆነ እርግጡን መናገር ባይቻልም ወደ ኢትዮጵያ ምድር የገባው በ1928 ዓ.ም ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡ አዳፍኔ በአካሉ ከአንድ ሰው ጉልበት የማያልፍ ትንሽ ነገር ነው(ገጽ 245)፡፡ አዳፍኔ መካካል ይወዳል፤ ከአንገቱ ላይ አብለጭላጭ ጌጥ ጠፍቶ አያውቅም፤ ይህ የአንገት ሀብል የተዋቀረው በቅርጻቸውና በመልካቸው ጉራማይሌ ከሆኑ ቀለበቶች ነው፡፡ እነዚህ የሀብሉ ቅንጣቶች የየራሳቸው መጠሪያ አላቸው፤ ተራ ጸሀፊ፣ ተራ ወታደር፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ህግ፣ ዳኛ፣ የምክር ቤት አባል፣ አስተዳዳሪ፣ የቀበሌ ሰራተኛና አስተዳደር፣ ወዘተ….. ይሰኛሉ፡፡
    አዳፍኔ እጅግ የሚወዳቸው ሁለት ልጆች አሉት፡፡ የበኩር ልጁ ፍርሃት ይባላል፤ ተከታዩ ደግሞ መክሸፍ የሚል መጠሪያ አለው፡፡ ፍርሃትና መክሸፍ ለአዳፍኔ ሁለመናው ናቸው፤ ቆሞ የሚሄደው፣ የሚተነፍሰው በእነርሱ ነው፤ ያለነሱ አዳፍኔ ምንም ማለት ነውና አብዝቶ ይንከባከባቸዋል፡፡ በእርግጥ አንገቱ ላይ ያንጠለጠለው ሀብል ሊያጌጥበት አይደለም፤ የልጆቹ ዘብ እንጂ፡፡ እናም አዳፍኔና የሰንሰለቱ ቀለበቶች ታዲያ ውል አላቸው፡፡ ውላቸው ግን ለአዳፍኔ የወገነ ነው፤ የጌታና የሎሌ፡፡ በውላቸው መሰረት ቀለበቶቹ ልጆቹን (ፍርሃትና መክሸፍን) ይንከባከባሉ፤ ለአገልግሎታቸውም ከአዳፍኔ ምንዳ ይቆረጥላቸዋል፡፡ አዳፍኔ በህይወቱ አብዝቶ የሚፈራው ነገር ቢኖር እውነትን ነው፡፡ እውነት የልጆቹ ዋነኛ ጠላት ነው፤ እናም የዕውነት ምንጮች የሆኑት እምነትና እውቀት የዘወትር ስጋቱ ናቸው፡፡ እውነትን ለማጥቃትም የእምነት(ሀይማኖት) እና የትምህርት ተቃማትን ከቻለ ደልሎ ወደራሱ ለማስገባት ካልቻለ ደግሞ በሀይል ለማስገበር ዘወትር ይተጋል፡፡ ለዚህም ጭፍሮቹ ከእርሱ ፍላጎት በተቃራኒ እንዳይሄዱና ከእውነት እንዲጠብቁት ታማኝነታቸውን ለማግኘት ሁለት ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ አንደኛው በጥቅም መደለልና ህልውናቸው በእርሱ መኖር ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ አምነው እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ሌላኛው ዘዴው ደግሞ ወደ እውነትን መንገድ የሚወስደውን መንንድ መዝጋት ነው፤ ለዚህም ጭፍሮቹ እንዳይነቁና እንዳይሰለጥኑ ሌት ተቀን ነቅቶ ይጠብቃል፡፡ ጭፍረቹ አብዝቶ ከሚፈራው እውነት ሊጠብቁት ካልቻሉ አዳፍኔ ለክፉ ቀን መከታ ይሆኑኛል በሚል የሚቀልባቸው ሁለት አካላት አሉ፡፡ እነዚህም የመከላከያና የደህንነት ሀይሎች ይባላሉ፡፡ የአዳፍኔ አይን በመሆናቸውም ሁልጊዜ እንክብካቤው አይለያቸውም፡፡
    እንግዲህ ከላይ በስሱም ቢሆን የተዋወቅነው አዳፍኔ ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ሚናው የላቀ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ተባባሪ የሆኑትና ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካላት የአዳፍኔ ውጤቶች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፈን እንደሚሞግቱት አዳፍኔ በታሪክ ክሽፈታችን ውስጥ ራሱን የሚገልጥበት ዋናው መንገድ ታሪካችን በጎ በጎውን ብቻ ነጋሪ፤ የትናንት ውጣ ውረዳችንን የሚያዳፍን መሆኑ ነው፡፡
    “…….. (ታሪካችን) አለማደጋችንና አለመሻሻላችን ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ጉድለታችንን ታሪካችን አለመዘገቡ የሚያሳፍር ታሪካችን ነው፤ ……….. በኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ በብዙ ምዕተ ዓመታት ግዙፍ ቦታ የያዘ መስለኛል፡፡ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የማውቀው አንድም ጥናት የለም፡፡” “ገጽ 28 እና ገጽ 50
    5.1.2 የኢትዮጵያ ታሪክና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞች (መሪዎቸ)
    ፕሮፌሰር መስፍን በ‹አዳፍኔ› መጽሀፋቸው ደጋግመው እንዳነሰት ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ በረጅም ዘመን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞችና አገዛዙ ያበቀላቸው ገዢዎች ናቸው፡፡ መገለጫውም ታሪክን ለመበረዝ፣ ለመፈብረክና ለማማፋት ያደረጋቸው የጥፋት ዘመቻዎች ናቸው፡፡ ታዲያ አገዛዙ ለታሪክ ክሽፈቱ ተጠያቂ የሚሆንባቸው አግባቦች ምንድናቸው? ለሚለው መሰረታዊ ጉዳይ መጽሀፉ ሶስት ጉዳዮችን ያነሳል፡፡ እነዚህም፡-
    • ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል
    • ህዝቡ ለታሪክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ
    • የታሪክ መረጃዎችን፣ ምልክቶችን፣ በመደበቅ፤ የታሪክ ጥናትና ምርምርን በማሳነስ
    5.1.2.1 ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል……..
    የኢትዮጵያን የታሪክ ክሽፈት በመሰረታዊነት የሚገልጸውም የአገዛዙና የታሪክ ዓላማ ልዩነት ነው፤ አገዛዙንና ታሪክን ከቃኘን ዓላማቸው ለየቅል ነው፡፡ የታሪክ ዓላማ የአገርና የህዝብ ኣላማ ነው፤ የታሪክ ዓላማ የእውነት ዓላማ ነው፡፡ የአገዛዙ ዓላማ ደግሞ ግለሰባዊ ነው፤ ፖለቲካዊ ነው፡፡ የታሪክ ምንነት እንዲሁም ዓላማ የሚወሰነው አገዘዛዙና መሪዎቹ የህዝብ ተቀባይነት ለማግኘትና ስልጣናቸውን ለማራዘም እንዲጠቅማቸው በሚያስችላቸው መልኩ ነው፤ በሌላ አገላለጽ ታሪክን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ያውላሉ፡፡ ትክክለኛው የታሪክ ትርክት ከአገዛዙ ኣላማ የሚጋጭ ከሆነ ለእነርሱ በሚስማማ መልኩ ታሪኩን ይበርዛሉ፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ አዲስ ታረክን ይፈበርካሉ፤ ካልሆነም ታሪክን ያጠፋሉ፡፡
    “………ቀደም ያለው (አገዛዝ) የሰራውን በሃላ መታው ያፈርሰዋል ወይም ይደብቀዋል፤ ታሪክን የአገርና የህዝብ አድርጎ በመመልከት ፋንታ የግል በማድረግ ታሪክ ያለባህሪው እንዲያትርና በሰው እድሜ እንዲለካ ያደርጋል፤ ታሪክ የሚከሽፍበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡” ገጽ 133
    5.1.2.2 ህዝቡ ለታሪክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ
    ሁለተኛው የአገዛዙ ሀጢአት ደግሞ ህዝቡ ለታሪክ ትክክለኛ ምንነት፣ እንዲሁም ዓላማ ያለው ግንዛቤ የተዛባ እንዲሆን ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያውን ማስፈጸሚያ መሳሪያ ለማድረግ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ለታሪክ ምንነት፣ ዓላማና ግምት የተሳሳተ ከሆነ አገዛዙ እንዳሻው ወይም ሲፈልግ ታሪክን ሊበርዝ፣ ሊፈበርክ፣አልያም ሊያጠፋ ይቻለዋል፡፡
    በረጅም ዘመን የኢትዮጵ ታሪክ አገዛዙና ሀይማኖት፣ በተለይም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በህዝቡ ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ የነበራት ሚና የላቀ ነበር፡፡ ከታሪክ ክሽፈት አካያም የሁለቱም አስተዋጽኦ ተደጋጋፊ ነው፡፡
    “………አገዛዙና ሀይማኖት የሰውን ልጅ ተቃርጠው፣ ለሁለት ገንጥለው ሥጋውን ለአገዛዙ ነፍሱን ደግሞ ለሀይማኖት አድርገው ተካፍለዋል፤ አንዱ ሥጋውን የበደለ ለነፍሱ ሲል፣ ሌላው ከሰው መርጦ ለሹመት እያለ የመሳፍንትና መካንንት አደግዳጊዎችን ያጠናክራል፡፡” ገጽ 64
    አላማው ህዝቡ የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ እንዲኖረው ማድረግ ሲሆን፤ መሳሪያው ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ ነበር፡፡ በመጽሀፉ እንደተገለጸውም፡-
    “…………ከአጤ ምኒልክ ዘመን በፊት በኢትዮጵያ ት/ቤት በመባል ሚታወቀው በክርስቲያንና እስላም ካህናት የሚካሄደው ነበር………….የባህላዊው ትምህርት ዓላማውና ስርዓቱም ከቤተ ሀይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ……. (ዓላማውም)ሰዎችን ወደ እግዚአብሄር እንዲቀርቡ ለማድረግ ሲሆን አቀራረቡም ከጸሎት ወይም ከልመና የማያልፍ ነው፤ ይህም ማለት በበጎ ተግባር ላይ ሳይሆን፣ ወይም ለግል ኑሮ እያንዳንዱ ሰው ያለበትን ሃላፊነት በማስታወስ ሳይሆን መለመንን እንደችግር መፍቻ በማድረግ ነው፡፡” ገጽ 63፣ ገጽ 65
    ባህላዊው የትምህርት ስርዓት ህዝቡ ኑሮው በአምላክ ፍቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ፣ በትናንት ድሉም ሆነ ተግዳሮቶቹ ሚናው ዜሮ እንደሆነ ይሰብካል ፡፡ ይህ በመሆኑም ህዝቡ ታሪክን የሚረዳው “……በእግዚአብሄር ፍቅርና ጥላቻ መስመር (ነው)” (ገጽ 181)፤ ስለሆነም የትናንቱን ከፍታም ሆነ ዝቅታ ማስታወስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው የታሪክ አረዳድ ትክክለኛውን የታሪክ ምንነትና ዓላማ የሚሽር ነው፡፡
    5.1.2.3 የታሪክ መረጃዎችንና ምልክቶች በመደበቅ፣ ጭራሹኑ እንዲጠፋ ለማድረግ በመሞከር
    ያለፉት ዘመናት በጎ ስራዎች እንዳይመዘገቡ፣ ጭራሱንም እንዳይታወቁ ለማድረግ መሞከር ሌላኛው አገዛዙ በታሪክ ላይ ያደረሰው ጥፋት ነው፡፡ ይህን ለማሳየት በመጽሀፉ የተጠቀሰው ዋናው አስረጅ ከ1933 ዓ.ም በሃላ የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው፡፡ በቅርቡ ታሪካችን ታላቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የአርበኞች ታሪክ ተደብቆ አንዲቀር የተደረገውም በአጼ ሀይለስላሴ መሰሪነት እንደሆነ ተጠቁማል፡፡ ከፋሺስት ቅኝ አገዛዝ አገራቸውንና ህዝባቸውን ነጻ ለማውጣት በዱር በገደሉ የተዋጉ፣ የተጋደሉ አርበኞች የአገዛዙ ኢላማ ሆነው፣ በክፉ ቀን ለባንዲራቸው ያደረጉት ተጋድሎ ተረስቶ የውርደት ካባ እንዲለብሱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይባስ ብሎም ለስደትና ለሞት የተዳረጉ ታላላቅ አርበኞች ነበሩ ( ገጽ 124-125፣ ገጽ 142፣ ገጽ 157 )፡፡
    5.1.3 የኢትዮጵያ ህዝብና የታሪክ ክሽፈት
    የኢትዮጵያ ህዝብ ለታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ሁለት ምክንያቶች ያላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ህዝቡ ለታሪክ የሰጠው ቦታ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ስለታሪክ ምንነትና ዓላማ ከሰጠው የተሳሳተ ትርጋሜ የመነጨ ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኮነንበት አግባብ ደግሞ ታሪኩን ጽፎ ለትውልድ እንዲተው እንዲያስችለው ዋነኛ መሳሪያ የሆነው የፊደል (ጽሁፍ) ጥበብ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረ ቢሆንም ህዝቡ ግን ይህን ታላቅ አጋጣሚ አልተጠቀመበትም
    እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን በእግዚአብሄር ፍቅርና ጥላቻ መስመር ነው (ገጽ 181 )
    ይህ የታሪክ አረዳድ የሚያሳየው ያለፈው ዘመን ተግባራት ሁሉ የተከናወኑት በሰው ፍቃድ ሳሆን በፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ስለሆነም የዛሬው የሰው ልጅ ተግባራት የነገ ታሪኩ እንደሆነ አልተረዳውም፡፡ ይህ የታሪክ የተሳሳተ የታሪክ ምንነት ግንዛቤ ታሪክን መሰረታዊ አላማና አስፈላጊነትን ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ በውጤቱም፡-
     ህዝቡ ለታሪክ ትምህርትና ዕውቀት አስፈላጊነት ዝቅተኛ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የዛሬን ሁነቶች መዝግቦ ለነገው ትውልድ የማየቆት ልማድ አያዳብርም
     በዚህም ህዝቡ ለታሪክ መረጃዎችና መዛግብት ዝቅተኛ ግምት ይሰጣል፤ በመሆኑም የታሪክ መረጃዎች ተጠብቀው እንዳይዳብሩ ተጠብቀው እንዲቆዩ የህዝቡ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ይሆናል፡፡
    5.1.4 የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፊያንና የኢትዮጵያ ታሪክ
    ዛሬ ላይ የምናገኘው የኢትዮጵያ ታሪክ ማህደር በአገር ውስጥ (ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው) እና በውጭ አገር የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት የተደራጀ ነው፡፡ የታሪክ ጸሀፍቱ ታሪክን ሲጽፉ ታዲያ ለኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ዕድገት በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ታሪክ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ማወደስ ያስፈልጋል፡፡ በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍም ይህ ተጠቅሳል፤ ይህ ሲባል ግን ጸሀፍቱ ሁሉ ታሪክን ለመጻፍ ሲሞክሩ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ስነ-ጽሁፍ እንዲዳብር ቀናኢነት ነበራቸው ብሎ መውሰድ ተሳሳተ ነው፡፡
    በእርግጥም የታሪክ ጸሀፍት እንዴት ለታሪክ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ፕሮፌሰሩ የሰጡትን ትንታኔ ለመረዳት በኢትዮጵያን ታሪክ ዙሪያ የጻፉ ምሁራንን (ጸሀፍትን) ማንነት መመርመር ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ጸሀፍቱ ታሪክን ለመጻፍ ሲነሱ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ወይስ……..? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡
    ከዚህ አንጻር በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍ እንደተጠቆመው ጸሀፍቱ ኢትዮጵያዊያን ወይስ የውጭ ዜጎች‹፤ በሁለቱም ጎራ ያሉ ጸሀፍትን የድሮ ወይስ የአሁን ብሎ መከፋሉ በስራዎቻቸው ሚዛናዊነት፣ ተዓማኒነት፣ ጥራት ወዘተ……. ላይ የራሱ እንድምታ አለው፡፡
    5.1.4.1 የውጭ ጸሀፍትን በተመለከተ
    የድሮ የውጭ ጸሀፍት ሲባል……
    የድሮ የታሪክ ጸሀፍትን ማንነት በመጽሀፉ በገልጽ ማግኘት አልቻልሁም፡፡ ሁለት ነገሮችን ማወቅ መልሱን ለማግኘት ቁልፍ ነው፡፡ አንደኛው የጸሀፍቱ ማንነትና ስራዎች ሲሆን ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ የተጀመረው መቼ ነው፣ በዘመኑ የነበሩ ጸሀፍት ማንነትና ታሪክን ከመጻፍ አካያ የነበራቸው መለያ ባህሪያትስ የሚለው ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት የድሮዎቹ የውጭ ጸሀፍት መለያ ያሉት ግዕዝን የተማሩ፣ ከኢትዮጵዊያን ጋር ቀርበው ለማወቅ የቻሉ፣ የኢትዮጵያዊያዊያንን ቃንቃና ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ የሚል ነው፡፡ይህ ቢያንስ ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ፍንጭ ሰጥቶኛል፡፡ ለሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ ግን መጽሀፉ ያለው ነገር የለም፡፡ እናም ፐሮፌሰሩ የድሮ ጸሀፍት ሲሉ እነማንን ነው› ለሚለው መልስ ለማግኘት መረጃ ማፈላለግ ነበረብኝ፡፡ ካገላበጥካቸው ስራዎች ውስጥ ግን ታዬ አሰፋ እና ሽፈራው በቀለ የተባሉ ምሁራን በጋራ ያሳተሙትን The Study of Amharic Literature: An Overview የሚለው ጥናት አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
    “……..ከ1870ዎቹ ጀምሮ በአማርኛ ስነ ጽሁፍ ላይ በርካታ ለውጦች መታየት ጀመረ ፡፡ ይህንንንም ከሶስት አቅጣጫዎች ማየት የቻላል፡፡ የመጀመሪያው በርካታ የውጭ ጸሀፍት በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ላይ ጥናት ለማድረግ የተነሳሱበትና ተሳትፎ ማድረግ የቻሉበት መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ኢጣሊያዊው ኮንቲ ሮሲኒ፣ ጀርመናዊው አውግስቶ ዲልማን፣ ፈረንሳዊው ዞተንበርግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሁለተኛ ይህ የዘመን ማዕቀፍ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ጥራት ያላቸው የስነ ጽሁፍ ስራዎች መታየት የጀመሩበት ነበር፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በቀደመው የኢትዮጵ የስነ-ጽሁፍ ክምችት ውስጥ እምብዛም ያልነበሩት ታሪካዊና ፊሎሎጂካዊ ( ) ዘውግ ያላቸው መጻህፍት በስፋት ተጽፈዋል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ የትምህርት ተቃማት በተለይም በጀርመንና ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ጥናት ማዕከላት ተቃቁመዋል፡፡ ጸሀፍቱም የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ እንደመረጃ የሚጠቅማቸው ድርሳናት በግዕዝ ቃንቃ የተጻፉ ስለነበሩ ቃንቃውን ማወቅ ነበረባቸው፡፡ በዘመኑ የአውሮፓ ታላላቅ የትምህርት ተቃማት ግዕዝ ቃንቃ በስፋት መሰጠት ተጀምሮ ነበር፡፡” (ገጽ 28)
    በፕሮፌሰር መስፍን እይታ መሰረት በዋናነት የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ዘመቻ ተጀመረው በፋሺስት ወረራ ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ዓላማዋን ለማሳካት እንዲያግዛት የኢትዮጵያን ታሪክ መበረዝ እንደ ዋነኛ መሳሪያ ተጠቅማለች፡፡
    ከላይ ከተመለከተው እንደምንረዳው ከዘመን አካያ ስናየው ፕሮፌሰር መስፍን የድሮዎቹ የውጭ ጸሀፍት የሚላቸው ከ1870ዎቹ እስከ 1920ዎቹ የተነሱትን ነው፤ ዓላማቸውም ዕውቀትን ለማስፋፋት ነበር፡፡
    የኃለኞቹ የውጭ የታረክ ጸሀፍት ሲሉ……..
    ፕሮፌሰር መስፍን የሃለኞቹ የታሪክ ጸሀፊያን የሚላቸው ከ920ዎቹ ጀምሮ የተነሱትን ነው፡፡ በተለይም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ታሪክን እንደዋነኛ መሳሪያ ተጠቅማለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል መንሳታቸው ለመላው ነጮች ሽንፈት ነው ብለው የሚያምኑ አውሮፓዊያን ጸሀፍት የኢትዮጵያን ታሪክ በመበረዝና፣ አዳዲስ የታሪክ ትርክቶችን በመፈብረክ ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተግተዋል፡፡
    የኃለኞቹ የታሪክ ጸሀፊያን ዓላማቸው ታሪክን በሚዛናዊነት መጻፍ፣ ዕውቀትን ለማስፋፋት አይደለም፤ ይልቁንም ቁሳዊ ፍላጎታቸው ለማማላት፣ ታሪክን እንዲጽፉ በገንዘብ የሚረዳቸውን ተቃም ለማስደሰት፣ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ነው፡፡
    የውጭ አገር የታሪክ ምሁራንና የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት
    በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍ እንደተመለከተው ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በማስተማርም ሆነ በጥናት እና ምርምር ዋነኛ ተዋናዮች የነበሩት የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ የውጭ ዜጎች ታሪካችንን መጻፋቸው ክፋት ባይኖረውም (ገጽ 212) በስራዎቻቸው ግን ትክክለኛና የተማላ ታሪክ አንዳናገኝ የሚያደርጉ ቢያንስ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህንንም ፕሮፌሰር መስፍን የገለጹት እንዲህ ነው፡-
    “………ከአንድ አገር ሰዎች ከራሳቸው የሚፈልቅ መረጃ ወይንም ዕውቀት ከዚያ አገር ህዝብ በራቀ መጠን ጉልበቱ ይቀንሳል፤ የአገሩ ሰዎች መረጃውን በመተርጎሙና በማጠናቀሩ በኩል የተሻሉ በመሆኑ (ነው)፡፡ ……….. (የውጭ የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት) የጎሳ ስሜትን በመቀስቀስ…ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሆነዋል፡፡” (ገጽ 212፣ ገጽ 214)
    ከታሪክ ክሽፈቱ አንጻር የድሮዎቹና የአሁኖቹ የውጭ ጸሀፍት ስራዎች አደገኛነት ይለያያል፡፡ በዚህም የድሮዎቹ ስራዎች ከአሁኖቹ የተሻለ ተ”ዓማኒነት አላቸው፡፡ ለዚህ ምክንያት ተብሎ በመጽሀፉ የተጠቀሰው የሚከተለው ነው፡-
    “………..የዱሮዎቹ ግዕዝ ሳይቀር እየተማሩ በግእዝ የተጻፉትን ሁሉ በየቃንቃቸው ይተረጉሙ ነበር፤ እነዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ ያጠኑ የነበረው የየሀገራቸውን ምሁራን ዕውቀት ለማበልጸግ ነበር፤ የሃለኞቹ ምንደኞች ናቸው፡፡” ገጽ 213
    5.1.4.2. ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት
    ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍትን የድሮዎቹና የአሁኖቹ ሲሉ በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ለዚህም መሰረት ያደረጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ጸሀፍቱ ያለፉበት የትምህርት ስርኣት ሲሆን ሌላው ደግሞ የጸሀፍቱ ግለሰባዊ(ቤተሰባዊ) ማንነት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የጸሀፍቱን ስራዎች ተዓማኒነት የሚወስኑ ናቸው፡፡
    የድሮዎቹ ጸሀፍት
    ከጸሀፍቱ ማንነት አንጻር በተነጻጻሪነት የድሮዎቹ ጸሀፍት ከጥቅመኝነት የራቁ፣ ዓላማቸውም ዕውቀትን መመርመር ነበር፡፡ እነዚህ የታሪክ ጸሀፍት በአብዛኛው በባህላዊው የትምህርት ስርዓት ያለፉ ናቸው፡፡ በዚህም ከተበላሸው የዘመናዊው ትምህርት ስርዓት የጸዱ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ ለመጻፍ ችለዋል፡፡ በተስተካከለ የታሪክ ትምህርትና ጥናት ያለፉ የሚላቸውን ምሁራን ለመጥቀስ ሞክረዋል፡፡እውነተኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማወቅ የፈለገ ሁሉ የፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ እና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ስራዎች ሊያነብ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ (ገጽ98)
    የአሁኖቹ ጸሀፍት
    የሃለኞቹ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ታሪክን በአግባቡ እንዳይጽፉ ያደረጉ ምክንያቶች ሁለት እንደሆኑ ፕሮፌሰሩ ይሞግታሉ፡፡ አንደኛው የታሪክ ጸሀፍቱ ያለፉበት መንገድ የተበላሸ መሆኑ ነው፡፡ሁለተኛው ደግሞ አብዛናው ጸሀፍት የባንዶች ልጆች መሆናቸው ነው፡፡
    ያለፉበት የትምህርት ስርዓት የተበላሸ መሆኑ
    ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚገልጹት አብዛኛው የዛሬው ጸሀፍት ታሪካቸውን ሳይቀር የተማሩት በውጭ ምሁራን ነው፡፡
    “…..የእኔ ትውልድ ከውጭ አገር ሰዎች ተማረው የኢትዮፕያ ህዝብ ከነባህሉ የአረብ ተወላጅ ተደርጎ ነው፤ የእኛ ነው የምንለው ነገር ሁሉ ከአረብ ያገኘነው መሆኑን እየነገሩን እኛም በተራችን ያንኑ ለተከታዩ ትውልድ ስናስተላልፍ ቆየን፤ የሴም ቃንቃ፣ ነገረ መንግስት፣ እረሻ፣ ጽህፈት፣ ወዘተ…..ሁለም ነገር ከባህር ማዶ ያገኘነው እየተደረገ ተማርን፤ እኛም በበኩላችን አስተማርን፡፡” ገጽ 116
    በዚህ አይነት የትምህርት ስርኣት ያለፉ የታሪክ ጸሀፍት የአገራቸውን የሚንቁ፣ በአንጻሩ ነጭ አምላኪ ሆነዋል፡፡ የዛሬዎቹ ጸሀፍት ከአገራቸው ታሪክ መረጃዎችና ምንጮች ይልቅ በውጭ ምንጮች ላይ ማተኮራቸው፣ የአገር ውስጥ የታሪክ ምንጮችን እንደማስረጃ አድርጎ ለመውሰድ አለመፈለግ የዚህ ነጸብራቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ እንዲያውም ‹ተረት› የሚላቸውን እንደክብረ ነገስት፣ ፍትሃ ነገስት ያሉትን እንደታሪከ ምንጮች አድርጎ መውሰድ ባይቻል እንካ ቢያንስ ለመመርመር ሲሞክሩ አይታይም (ገጽ 231)፡፡
    የጸሀፍቱ ግለሰባዊ ማንነት
    አብዛኞቹ የዛሬ ጸሀፍት የባንዶች ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ጸሀፍት የወላጆቻቸውን የባንዳነት ሃጢኣት ንስሃ ገብተው ለመንጻት ከመሞከር ይልቅ ሃጢያታቸውን ለመሸፋፈን ታሪክን በመበረዝ ለመሸሽ ሞክረዋል፡፡
    “…………….በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን ታሪክ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው እንደሚመች እያደረጉ በመተርጎም የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ታሪክ ያበላሻሉ፤ እያበላሹም ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮፕያን ታሪክ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተለየ ባለመሆነኑ ከመቶ ዓመታት አይበልጥም የሚባለው የባንዶች ልጆች የፈጠሩት የሻዕቢያና የወያኔ ተረት ነው፤ ባንዳዎች ያልነበሩ የኤርትራና የትግራይ ሰዎች ይህንን የፈጠራ ታሪክ አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም የብዙዎቹ አባቶች በኢትዮፕዊነታቸው ኮርተው በአርበኝነት የሞቱ ወይም የተጎዱ ይሆናሉ፡፡” (ገጽ ——)
    ፕሮፌሰሩ ሁሉንም የታሪክ ጸሀፍት በጅምላ አልወቀሱም፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ህጸጾች የጸዱ ናቸው፣ በዚህም የኢትጵያን ታሪክ ለማወቅ የፈለገ ሁሉ ስራዎቻቸውን ሊያነብ ይገባል ያላቸውን እንደ ፕሮፌሰር አለም እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የመሳሰሉ ምሁራንን አወድሰዋል (ገጽ 98) ፡፡
    ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ክሽፈት
    ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት በሶስት መልኩ ለታሪክ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እነዚህም ለታሪክ ያላቸው የተዛባ ግንዛቤ፣ ታሪክን በሚዛናዊነት አለመጻፍ እና ታሪክን ሲጽፉ ለአገር ውስጥ የታሪክ ድርሳናትና የታሪክ ምንጮች አነስተኛ ግምት መስጠታቸው ነው፡፡
    የተዛባ የታሪክ ግንዛቤአቸው
    እንደፕሮፌሰር መስፍነ እምነት አብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ታሪክ “ለአንድም ሰኮንድ የማቃርጥ የሰው ልጆች የአናናር ጅረት መሆኑን አልተረዱትም (ገጽ 98)፡፡ ከዚያ ይልቅ ታሪክን እንደ ተረት…መነሻ የሌለው፣ አቅጣጫ የሌለውና ዓላማ የሌለው አድረገው በጊዜ በታጠረ ብቅ ጥልቅ ውስት የሚነገር ተረት አድርገውታል……..(ታሪክን) በሁለት እግሩ ብቻውን ቆሞ የሚሄድ ነፍስ ያለው ነገር አድርገው ይወስዱታል”፡፡ (ገጽ 50፣ ገጽ 98)
    የታሪክ ጸሀፍት በሚዛናዊነት ታሪክን አለመጻፍ
    ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት በብዙ መልኩ በገለልተኝነት ታሪክን ለመጻፍ አልቻሉም፡፡
    “………(ጸሀፊያኑ) ለስልጣን በማጎብደድና ለጥቅም በመገዛት ሁነትን ሁሉ በአገዛዙ መነጽር ብቻ እያዩ ያንኑ ስህተት ለተከታታይ ትውልዶች እያስተላለፉ ስህተቶቹ እንዳይታረሙ ያደርጋሉ፡፡” ገጽ 30
    የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፍትና የታሪክ የመረጃ ምንጮች ከታሪክ ክሽፈት አንጻር
    ታሪክ በተማላና በትክክለኛ ሁኔታ እንዲጻፍ የታሪክ የመረጃ ምንጮች ተዓማኒነት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ታሪክን ለመጻፍ ሲነሱ እንደዋና ግብኣታቸው አድርገው የሚጠቀሙት የውጭ ጸሀፍት ስራዎችን ወይም ውጭ ምንጮችን ነው፡፡ አገር በቀል የሆኑ የታሪክ ድርሳናትን የማሳነስ ሁኔታ በጸሀፍቱ ይታያል (ገጽ 212፣ 232)፡፡ ጸሀፊያኑ ለዚህ የሚያቀርባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የአገር ውስጥ የታሪክ ድርሳናት ማገኘት አስቸጋሪ ነው የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ ነባር የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፍትና ስረዎች የሚዛናዊነት ጉድለት ይታባቸዋል የሚለው ነው፤ ሚዛናቸውን የሚያጋድለው ዋናው ነገር ደግሞ ጸሀፍቱ ለሚወክሉት ብሄር አድልተው መጻፋቸው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
    ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚከራከሩት ኢትዮጵዊያን የታሪክ ጸሀፍት ወደ ውጭ ምንጮች እንዲዞሩ በምክንያትነት የሚያቀርባቸው ሁለቱ ምክንያቶች መሰረተ ቢስ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ መረጃዎች አነስተኛ መሆን ለሚለው ያሉትን መቼ ለመመርመር ሞከርን; ፍላጎቱም የለንም ሲሉ መልሰዋል፡፡ ወደ ውጭ ምንጭ ማማተሩ እንደምክንያት ለሚነሳው ሁለተኛው ጉዳይ የሰጡት ምላሽ ደግሞ የኢትዮጵያ ጸሀፍት ስራ ሚዛን ያጋደለው ጸሀፍቱ ከጥቅመኝነት፣ ጥገኘነትና ከፍርሃናትና ስጋት ነጻ አለመውጣታቸው እንጂ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሀፍት የዘር ሀረጋቸው ለሚመዘዘበት ጎሳ አድልተው ይጽፋሉ የሚለው ጉዳይ አሳማኝ እንዳልሆነ ፍንጭ ይሰጣሉ (ገጽ 232)፡፡
    በቂ የአገር ውስጥ ታሪካዊ መረጃዎች ከሌሉ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የውጭ የታሪክ ጸሀፍት ስራዎችን እንደመረጃ ወስዶ ታሪክ መጻፉ ጉዳት የለውም ፡፡ ጸሀፍቱ ወደ ውጭ መረጃዎች ፊታቸውን ሲያዞሩ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ስላለባቸው ጉዳዮች ጽፈዋል፡፡
    አንደኛ የጸሀፍቱን ማንነት ከመመርመር አንጻር ነው፡፡ በድሮዎቹና በአሁኖቹ የውጭ አገራት የታሪክ ምሁራን መካከል ልዩነት አለ፤ የድሮዎቹ የሚጽፉት ዕውቀትን ለማበልጸግ ሲሆን የአሁኖቹ ግን ምንደኞች ናቸው፡፡ ስለሆነም የድሮዎቹን ጸሀፍት ስራዎች እንደማጣቀሻ መውሰዱ የተሸለ ነው፡፡ ሁለተኛ የውጭ ጸሀፍት ታሪክን ሲጽፉ ዓላማ አድርገው የሚነሱት እውነተኛ ታሪክን ለመጻፍ ነው ወይስ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ አላቸው ብሎ መጠራጠር ያሻቸዋል፡፡ይህን ሳይመረምሩ እንደወረደ ስራዎቹን አምኖ ተቀብሎ እንደማጣቀሻ መውሰድ አደገኛ ነው (ገጽ 213)፡፡
    ሶስተኛ የውጭ ስራዎች እንደምንጭ መውሰድ የመረጃው ጥራት(ተዓማኒነት) ያሳንሳል፡፡ ይህም የሚጻፈው ታሪክ ተዓማኒነት የጎደለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህን ሲያብራሩም፡-
    “……….ከአንድ አገር ሰዎች ከራሳቸው የሚፈልቅ መረጃ ወይንም ዕውቀት ከዚያ አገር ህዝብ በራቀ መጠን ጉልበቱ ይቀንሳል፤ የአገሩ ሰዎች መረጃውን በመተርጎሙና በማጠናቀሩ በኩል የተሻሉ በመሆኑ (ነው)፡፡” (ገጽ 212፣ 213)
    ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ኢትዮጵየያዊያን ጸሀፍት ወደ ውጭ ምንጮች አብዝተው ማማተራቸው ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ጸሀፍቱ የባንዶች ልጆች መሆናቸው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በትክክለኛ የትምህርት ስርዓት አለማለፋቸው ነው፡፡

6 የታሪክ ክሽፈቱ ያመጣብን መዘዞች
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን እምነት የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት አገሪቱንና ህዝቦቻን ብዙ ዋጋ አስከፍላል፡፡ በአዳፍኔ መጽሀፍ በተለያየ መንገድ የተገለጹ ሀሳቦችን ከሰበሰብናቸው የታሪክ ክሽፈቱ መዘዞች ሶስት ናቸው፡፡
 ከኢትዮጵያ አንድነት አንጻር
 ኢትዮጵያ በቁሳዊ ስልጣኔ ሃላ ቀር እንድትሆን ከማድረግ አንጻር
 ከኢትዮጵያ መንፈሳዊ ስልጣኔ (ሉዓላዊነት) አንጻር
6.1 የታሪክ ክሽፈትና የኢትዮጵያ አንድነት
በመጽሀፉ እንደተገለጸው የህዝብ አንንነትነ የአገር መሰረት የሆነው ህዝቦች በክፉ ጊዜ አንድ መሆን፣ መተባበርና ለአገራቸው ክብርና ሉኣላዊነት ቀናኢነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መሰረትም ይኸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ከታሪክ ክሸፈቱ ጋር አብሮ እየከሸፈ ይገኛል፡፡ በዚህም
“……..የአንድ ትውልድ ስህተት ወደሌላ ትወልድ እየተላለፈ ለብዙ ትውልዶች የስህተት ምንጭ (እየሆነ) ታሪካችንንና የኢትዮያን ህዝብ ህዝብነት (በመበከል) ዛሬም እንደቆላ ቁስል እነዘነዘን (ነው)፡፡” ገጽ 29
በመጽሀፉ እንደተብራራው የታሪክ ክክፈቱ አገር እንዲፈርስ በር ከፍታል፤ ለወደፊቱም በር መክፈቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ የቀረበው ደግሞ የታሪክ ክሽፈቱ አንዱ ማሳያ የሆነው የኢትዮጵን ታሪክ ከመሃሉ ወይም ከአሁኑ የመጀመር የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ኤርትራ የኢትዮጵያ መሰረት መሆናን ማስካድ ለጊዜውም ቢሆን ተችላል ( ገጽ 97)
የኢትዮጵያ ታረክ ክሽፈት ሌላኛው ገጽታ የሆነው የትናንቱን የኢትዮጵያን ዕውነት መካድ የወደፊቱን የኢትዮጵያ አንድነት የሚያናጋ ነው፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የቀረበው ደግሞ በቀዳማዊ ሀይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ ስልጣን (ታስቦበት የተደረገ ባይሆንም) በመንግስት ስልጣን ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች ስብጥር የመሆኑ ዕውነት ተቀብሮ ያለፈው ስርዓት የአንድ ብሄር ( የአማራ ብሄር) የበላይነት እንደነበር ተደርጎ የሚነገረው የበሬ ወለደ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋና የፖለቲካ ገጽታ የሆነው ጎሰኝነት መሰረቱም ይህ ሀሰተኛ የታሪክ ትርክት ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ጎሰኝነትና እንዲያብብ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲቀጭጭና አገር የመበታተን አደጋ ላይ እንዲወድቅ መሰረት ሆናል፡፡
ይህንን ሁኔታ ፕሮፌሰር የገለጹት በዚህ መንገድ ነው፡-
……..ችግሩ ሁሉ ከአገዛዝ ጋር የተየያዘ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለ…….የአጼ ሀይለ ስላሴና ደርግ አገዛዝ የ‹‹አማራ›› ሆነው በመፈረጃቸው ውግዘቱ ሁሉ ያንን ቃንቃ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ተወረወረ፤ አስተሳሰቡ ቀላል በመሆኑ ዛሬም የወያኔን አገዛዝ የትግሬ አገዛዝ የሚያደርጉት አሉ፤……(ይህ)ከተዛባ አሰተሳሰብ የሚመነጭ ስህተት ነው፡፡ ገጽ 39
6.2 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈትና ቁሳዊ ስልጣኔ
የኢትዮጵያ የታረክ ክሽፈት ሌላኛው ገጽታ ህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ዋጋ እንዳይሰጥ ማድረጉ ነው፤ ይህም ከትናንቱ ህይወቱ ትምህርት ወስዶ የነገ ህይወቱን ለማሻሻል እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ የብልጽግናና የለውጥ መሰረት የሆኑ እሴቶች፡ ለአብነትም ጠንካራ የስራ ባህል፣ ትጋት፣ ለገንዘብና ለጊዜ ዋጋ አለመስጠት፣ በጋራ የመስራትና የመተባበር ባህልን በኢትዮጵዊያን ዘንድ ብዙም ቦታ የላቸውም፡፡
“……….ዳገቱን እንዴት እንደወጣንና ቁልቁለቱን እንዴት እንደወረድን በትክክልና በዕውነት (እንድንገነዘብ)፣ ክብርና ኩራት ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብነና ሳንመዝን ለማይገባው (እንድንሰጥ)፣ በውጤቱም የሰራው እየተረሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ተውልድ ይተላለፋል፡፡…..ስለዚህም መስራት የማስከብርና የማያከብር ይሆናል፤……..ሳይሰሩ ለመክበርና ለመከበር መጣር ባህል ይሆናል፡፡”ገጽ 73-74
6.3 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈትና መንፈሳዊ ስልጣኔ (የአገር ሉዓላዊነት)
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን እምነት የኢትዮጵያ ስልጣኔ መንፈሳዊ ስልጣኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሳይከሽፍ የቆየውም ለዚህ ነው፡፡ ምንም እንካን ኢትዮጵያ በቁሳዊ ሀብትና ዘመናዊነታ ሃላ የቀረች ቢሆንም ድህነታ ግን ለውጭ ወራሪዎች እጅ እንድትሰጥ አላደረጋትም፡፡ ለዚህ ምከንያቱ የመንፈሳዊው ስለጣኔ መገለጫ የሆኑትና ለዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሆነው የኖሩት አርቆ አሳቢነት፣ ሀይማኖተኝነትና ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ መልካም ስነ ምግባር፣ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ለክብርና ኩራት ቅድሚያ መስጠት፣ ለአገር ነጻነትና ሉዓላዊነት መስዋዕትነት ተጋድሎ ማድረግ ወዘተ…. ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ መንፈሳዊ ስልጣኔ እስከመጨረሻው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አልተቻላቸውም፡፡
የታሪክ ክሽፈቱ አንዱ ውጤት የሆነው የህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ያለው ዝቅተኛ ግምት ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በእጅጉ በኢኮኖሚ ወደሃላ አስቀርታታል፡፡ ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ በአዳፍኔ መጽሀፍ የተገለጸው በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ሀይል ኢትዮጵዊያን አርበኞችን በማይጨው የጦር አውድማ ድል መንሳቱ ነበር፡፡ ለዘመናት ተከብሮ የኖረው የአገር ሉኣላዊነት ተደፈረ፡፡ኢጣሊያ ጦር ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ፣ በምድርና በአየር በወገን ጦር ላይ መኣቱን ሲያወርድ ፣ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ግን ከሃምሳ አመታት ቀደም ብሎ በአድዋ ጦርነት ታጥቀው የዘመቱትን ባህላዊ መሳሪያዎች ነበር፡፡ በዚህም፡-
“………ኢትዮጵያ ያለችበትን በታም ዝቅተኛና ቆሞ ቀር ደረጃ በተግባር አስመሰከረች፤ይህ አዲስ ዕውነት የኢትዮጵ ህዝብ ለዘመናት የነበረውን አልበገር ባይነት ከነኩራቱና ክብሩ ገፈፈው፤ የመንፈስ ሃይሉ ደቀቀ፤ አንገቱን ደፋ፡፡” ገጽ 133
በአጠቃላይ ከአምስቱ ዓመታት የፋሺስት ወረራ በሃላ በኢትዮጵያን የመንፈሳዊ ስልጣኔው የከሸፈ ይመስላል፡፡ ለግል ጥቅም ሲባል ያልተገቡ አገርን በገንዘበ መለወጥ ወይም ባንዳነት፣ ህዝቡ የአገርን ችግር በአገር ቤት ከመጋፈጥና ለመፍታት ከመጣር ስደትን መምረጡ፣ ኢትዮጵያዊ ክብርና ኩራት እተመናመነ መሄዱ፣ አርበኝነት ቦታ ሲያጣ ባንዳነት መወደሱ ወዘተ.…… ማሳያ ናቸው፡፡ በውጤቱም ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሉኣላዊነት አደጋ ላይ ወድቃል፡፡
በአጠቃላይ የታሪክ ክሽፈቱ መዘዞች በተለይም ባለፉት 85 ዓመታት ጎልተው ታይተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ያቀረቡትን ትንታኔ ጠቅለል ባለ ሁኔታ በሚከተለው ምስል ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡

  1. የኢትዮጵያ ታሪክን ከክሽፈት ቁልቁለት እንዴት መታደግ ይቻላል?
    7.1 ህዝቡን በተመለከተ
    የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት አዘቅት ይላቀቅ ዘንድ ህዝቡ የራሱን ሚና መወጣት እንዳለበት ለዚህም በመጽሀፉ መጨረሻ ላይ የምናገኛቸው አስር መፍትሄዎችን መከተል አለበት፡፡
    7.2 አገዘዙን በተመለከተ
    በመጽሀፉ ላይ አገዛዙ ማድረግ ያለበት ነገር በቀጥታ አልተገለጸም፡፡ይሁንና አገዛዞች ከቀደመው አገዛዝ ስህተቶች መማር፣ መልካም ጎኖች ደግሞ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው በተዘዋዋሪ ይመክራሉ፡፡

    7.3 የታሪክ ጸሀፍትን በተመለከተ
    በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊያን ጸሀፍትን በተመለከተ ሊስተካከሉ የሚገባውና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እንዲህ ይመክራሉ፡-
  2. ስለታሪክ ያላቸውን አረዳድ የተዛባ አረዳድ ማስተካከል፡፡ ይህ ከሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ ከይዘት እና ከጊዜ ጥልቀትና ስፋት አንጻር ያለው ውስንነት ይታረማል፡፡ በዚህም፡-
    ሀ. የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነትና የነገስታት ታሪክ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ከዚያ ውጭ ያሉ ርእሰ ጉዳዮች ማለትም የህዝቡ ማህበረ-ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮች፤ ስለኢትፕያ ስነጽሁፍ፣ ቃንቃዎችና ሌሎችም በርካታ ታሪካዊ ጉዳዮች የታሪካችን አካል ማድረግ ይቻለል፡፡
    ለ. የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ አመት ወይስ የሶስት ሺህ አመት የሚለው ክርክር እልባት ሊያገኝ ይችላል፡፡ በእርግትም ኢትዮጵያ ሶስት ሺህ አመት ዌም ከዚ በላይ እድሜ ያላት አገር እንደሆነች ለመረዳት ያስችላል፡፡
    ሐ. የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት አንዱ መገለጫ የሆነው በጎ ታሪክን ብቻ ጽፎ የማቆየትና ያለፍንባቸውን ውጣውረዶችና ችግሮቻችንን የመዝለሉ ጉድለት ሊቀረፍ ይችላል፡፡
  3. ያለፉበት የትምህርት ስርኣት ችግር ያለበት መሆኑን መገንዘብና ከችግሩ ለመንጻት ንስሃ መግባት ሌላው መፍትሄ ነው፡፡ በመጽሀፉ እንደተመለከተው፡-
    ….የውጭ ሊቃውንቱ ትናት ልዩ ጥቅም ቢኖረውም ባይኖረውም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚያደርጉት ትናት በጭራሽ ልንቃወም አንችልም፤ የምቃወመው እነሱ አኛን እንደፈለጉ አድርገው ሊቀርጹን የሚያደርጉት ሙከራ ነው፤ እኛም እነደጥቁር ሰሌዳ የእነርሱን ነጭ ጠመኔ የበህርይ አድርገን መቀበላችን ነው፡፡ ገጽ 213
  4. ከጥቅመኝነት፣ ከጎሰኝነት፣ ከፍርሃትና ስጋት ራሳቸውን ነጻ ማውጣት አለባቸው፡፡

1. መግቢያ።

1.1 ስለ ደራሲውና ስለ መጽሀፉ አጠቃላይ በአማርኛ ቃንቃ ከሚጽፉ እጅግ ጥቂት ኢትዮጵዊያን ምሁራን መካከል አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚጽፋቸው በሳል ጽሁፎችና በሚያነሳቸው አዳዲስ ጉዳዮች የምሁርነትን ልክ ያሳዩን ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በየሁለት አመቱ ልዩነት ማለት ይቻላል በተከታታይ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ መጽሀፍትን አስነብበውናል፡፡ዘንድሮም (ማለትም በ 2007 ዓ.ም) ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› በሚል አዲስ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡ ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› በአስር ምዕራፎችና በ280 ገጾች የተደራጀ ሲሆን በግራፊክ አሳታሚዎች ለህትመት በቅታል፡፡ ‹አዳፍኔ› ፕሮፌሰሩ በ2005 ዓ.ም ያሳተሙት ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሀፋቸው ተከታይ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ለዚህም ሁለት አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ከጭብጥ አካያ ብዙ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹አዳፍኔ› ከያዛቸው አስር ምዕራፎች ውስጥ ሶስቱ (ይህም የመጽሀፉን ዘጠና ስድስት ገጾች ወይም 40 በመቶ ያህል ይሸፍናል ማለት ነው) በ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ላይ በተለያዩ ጸሀፍት ለተሰነዘሩ ትችቶች ምላሽ የሰጡበት( በመጽሀፉ እንደተገለጸው የ‹ ትችቶች ትችት›) ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ አተያይ የመጽሀፉ ዋነኛ መገለጫዎች(መልኮች) ሁለት ናቸው፤ እነዚህ ሁለት መገለጫዎችም የመጽሀፉ ውበቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሀፉ በይዘቱ ሰፋ ያለ መሆኑ ነው፤ ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሁለተኛው መጽሀፉ በቅርጹና አቀራረቡ የራሱ የሆነ አዲስ ቀለም ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ይነካል፤ ታሪክ፣ ባህል፣ ስልጣንና አገዛዝ (ፖለቲካ)፣ኢኮኖሚክስ፣ ስነ መንግስትና አስተዳደር (አገር፣ ህዝብና መንግስት)፣ ሀይማኖት፣ ትምህርትና ዕውቀት እንዲሁም ዕውነት፣ ስነ-ልቦና፣ ፍልስፍና እና ሌሎች የጥናት ዘርፎች ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጽንሰ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ ሌላው የመጽሀፉ መልክ ለጥናትና ምርምር፣ ለጥልቅ ውይይትና ክርክር የሚጋብዙ ሀሳቦችን ማንሳቱና በዚሁ በተቃኘ አቀራረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡ 1.2 የመጣጥፉ ዓላማ ወጣቱ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍ ዙሪያ ያለውን አተያይ ከሁለት አመታት በፊት ገደማ በአንድ መጣጥፉ አስነብቦናል ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል በመጣጥፉ ካነሳቸው በርካታ ቁም ነገሮች አንዱ የክሽፈት ታሪክ እንጂ የታሪክ ክሽፈት የሚባል ሊኖር አይችልም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፋቸው ‹የትችቶች ትችት› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ለዚህ መልስ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን መልሱ አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይህ ሲባል ግን ፕሮፌሰሩ መልስ አልሰጡም ለማለት ሳይሆን የተሰጠበት አግባብ የተደራጀና ግልጽ አይደለም፤ እንዲያውም የአዳፍኔ ዋነኛ ጭብጥ በክሽፈት ታሪክና በታሪክ ክሽፈት ዙሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሀሳቦቹ እዚህም እዚያም ተበታትነው የቀረቡ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አንባቢ የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረው ያደርጋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ በዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ እምነት የክሽፈት ታሪክ እና የታሪክ ክሽፈት የሚሉት ሁለት ሀሳቦች ብዙ ጉዳዮችን ያዘሉ በመሆናቸው በጥልቀት መታየት አለባቸው፡፡ በመሆኑም አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ስለ ክሽፈት ታሪክና ስለ ታሪክ ክሽፈት ያነሳቸውን ሀሳቦች በማሰባሰብ ለማቅረብ ተሞክራል፤ መጽሀፉ ከአደረጃጀት አንጻር በዚህ ሁኔታ ቢቀርብ መልዕክቱን በይበልጥ ለመረዳት ያስችላል ፤ በመጽሀፉ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በአንባቢያን የሚቀርቡ የውይይትም ሆነ የክርክር ሀሳቦች ቅርጽ እንዲይዙ ለማድረግም ያግዛል፡፡ የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ የታሪክ ክሽፈት፡ ከኢትዮጵያ አንጻር በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የደራሲውን እይታዎችን አጠቃሎ በማቅረብ ለውይይት እንዲመች ማድረግ ነው፤ በመጽሀፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ትዝብት ማስፈር የሚለው ሌላው የመጣጥፉ ግብ ነው፡፡ 1.3 የመጣጥፉ ይዘት የመጣጥፉ ይዘት የተቃኘውም ከላይ ለማንሳት ከሞከርኩት ዓላማ አንጻር ነው፡፡ በዚህም በዚህ አጭር ጽሁፍ ለሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ተሞክራል፡፡  የታሪክ ምንነትና ዓላማ ምንድነው?  የታሪክ ክሽፈትና የክሽፈት ታሪክ ማለት ምን ማለት? ቁርኝታቸውስ እንዴት ነው ?  የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር እንዴት ይታያል ?  ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ተጠያቂው ማነው ?  የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈቶችና መዘዞች ምንድናቸው ?  ከታሪክ ክሽፈት ለመውጣት ምን ማድረግ ያሻል ?  የመጽሀፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በቅድሚያ ግን ስለታሪክ እና ተያያዥ ጉዳዮች አንዳንድ ሀሳቦችን በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ 2. ስለ ታሪክ ምንነት፣ ባህሪያትና ዓላማ 2.1 ስለታሪክ ምንነትና ዓላማ የታሪክ ፍልስፍና ዘይቤ አባት በመባል የሚታወቀው አውግስሚኖስ የታሪክ ምንነትና ዓላማ ሲገልጸው እንዲህ ነው፡- ታሪክ መንግስት መቆሙንና መፍረሱን፣ ህዝቦች ማደጋቸውንና መውደቃቸውን ያትታል፡፡ይህም የሚሆንበት ምክንያት አምላክ ባቀደው መሰረት የሰው ዘር ወደ እውነተኛው ብርሃን ለመምራትና ለማዳን ሲል ነው፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን የታሪክ ምንነትና ዓላማ አረዳድም ከአውግስሚኖስ ጋር በይዘቱ አንድ ነው፣ ቅንቃው ቢለወጥም፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ማለት ፡- “…..ለአንድም ሰኮንድ የማያቃርጥ የኑሮና የአናናር ጅረት ነው፡፡ ……..ታሪክ አንድ ህዝብ የስራ መዝገብ ነው፡፡” ገጽ 98-99 የታሪክ ዓላማ ደግሞ ህዝቡ ያለፈውን ዘመን ከፍታና ዝቅታ አስታውሶ፣ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ በጎ ጎኖች ትምህርት ወስዶ፣ ከችግሮቹ ተምሮ በኑሮው መሻሻል እንዲያሳይ ማድረግ ነው (ገጽ 28፣ ገጽ29 )፡፡ በአጠቃላይ፡- • ታሪክ ማለት የትናንት ዕውነትን (በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ) መመርመር ነው፡፡ • የታሪክ ዓላማ የሰው ልጅ የትናንት በጎ ተግባራቱን አዳብሮ፣ ከስህተቱ ደግሞ ተምሮ የዛሬና የነገ ህይወቱን እንዲያቀና ማድረግ ነው፡፡ በዚህም አውግስሚኖስ የታሪክን አስፈላጊነትና ዓላማ ከመለኮታዊ ሀይል ዓላማ ጋር ያዛምደዋል፡፡ በዚህም የታሪክ ዓላማ የፈጣሪ አላማ ነው፡፡ በተለይ ሁለተኛው ሀሳብ ከታሪክ አረዳድ አንጻር ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን በጉዳዩ ላይ ትንሽ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ 2.2 ስለ ታሪክ ባህሪያት በግሌ የታሪክ ባህሪ ከአምላክ ባህሪ ጋር ይመሳሰሉብኛል፡፡ ታሪክ አምላካዊ ባህሪዎችን ሁሉ ይወርሳል፡፡ ታሪክን ከአምላከዊ ባህሪ ጋር ለማንጸር ያደረግሁት ጥረት ያልተመቻቸው እንደኔ እንደኔ የአምላክን ባህሪ የማያውቁ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ለመሆኑ የአምላክ ባህሪያት ምንድናቸው ? የታሪክ ባህሪያትስ ? በመሰረቱ የአምላካዊነት መሰረት ሀቅ ነው፤ የታሪክ መሰረቱም አንዲሁ ሀቅ (እውነት) ነው፡፡ ፈጣሪ የሰው ልጆችን ጨምሮ በአጠቃላይ በፍጡራን ላይ ፍጹም ስልጣን አለው፤ ታሪክም ይህ ስልጣን አለው ፡፡ የፈጣሪ ዓላማ የሰው ልጆቸ ሁሉ በቀና መንገድ እንዲያልፉ ማስተማር ነው፤ የታሪክ ዓላም እንደዚሁ ነው፡፡ ወደር የለሽ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት አምላካዊ ባህሪ ነው፤ ዓላማውም ሰዎች በራሳቸው ከጥፋት መንገድ እንዲታቀቡ፣ ካለፈው ስህተታቸው እንዲታረሙ ጊዜ መስጠት ነው፡፡ የታሪክ መንገድም ይህ ነው፡፡ በመሰረቱ ዕውነትን(ታሪክን) መበረዝ ወይም ማጥፋት የሚቻል ሊመስለን ይችላል፡፡ መሪዎችም ይህን ለማድረግ የቻሉ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን በጥልቀት ከመረመርነው አልቻሉም፡፡ የፈጣሪን ትዕግስት ዓላማ ያልተረዱም በስህተት ላይ ስህተት ላይ እየፈጸሙ በመጨረሻም ከነጭራሹ የፈጣሪን ስልጣን ሲመኙ፣ ሲብስም ህልውናውንም ሲክዱ መቀበሪያቸውን ጉድጋድ እያበጁ እንደሆነ ሳይታወቃቸው፣ የትዕግስቱ መብዛትም በቆፈሩት ጉድጋድ እንዲቀበሩ ያደረጋቸዋል፡፡ የታሪክም መንገድ ይህ ነው፡፡ ታሪክ ከስህተት ለመማር እድል ይሰጠናል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ግን በቆፈሩት ጉድጋድ ይቀበራሉ፡፡ በታሪክ ማህደር እንደተዘከረው በታሪክ ላይ የዘመቱ ሁሉ መጨረሻቸው መጥፋት ነበር፡፡ በእርግጥም በዘመናት ሂደት ያለፉ፣ ታሪክ ላይ ያመጹ አገዛዞችና ነገስታት አነሳስና አወዳደቅ ለመረመረ ይህ ይገለጥለታል፡፡ ታዲያ የፈጣሪ የቅጣት በትር ፍጹም ፍትሃዊ እንደሆነው ሁሉ የታሪክ ቅጣትም ጊዜ ወይም ቦታ የማይቀይረው፣ ለማንም የማይወግን ፍጹም ፍትሃዊ ነው፡፡ ትናንትም ይሁን ዛሬ በታሪክ ላይ ያመጹ ሁሉ በጥፋታቸው ልክ ተቀጥተዋል፤ ነገም እንዲሁ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ 3. የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት 3.1 የታሪክ ክሽፈት ሲባል…… እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ የታሪክ ክሽፈት ሲባል፡- “…… ምንም ያልተመዘገበ ነገር መኖሩ፤ ታሪኩ ከበላ-ጠጣ-ተነሳ- በላ-ጠጣ-ተኛ….. የማያልፍ ሲሆን ወይም በላ-ጠጣ-ተኛ-ተነሳ-ተራበ-ተጠማ ብቻ ሲሆን (ነው) “ገጽ 99 ከዚህ ገለጻ እንደምንገነዘበው የታሪክ ክሽፈት ምንነት ሁለት ምሰሶዎች አሉት፡፡ አንደኛ የታሪክን ምንነት አለመገንዘብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የታሪክን አላማ አለመገንዘብ ነው፡፡ ምንም ያልተመዘገበ ነገር መኖሩ ከሚለው ሀረግ የምንረዳው የታሪክ ክሽፈት ፕሮፌሰሩ ትክክለኛ የታሪክ አረዳድ (ከላይ ለማሳየት እንደሞከርሁት ) ብለው ባስቀመጡት ልክ ሳይሆን ሲቀር ወይም የህዝብ የዘመናት የኑሮ ውጣ ውረድ ሳይመዘገብ ሲቀር ነው፡፡ ታሪኩ ከበላ-ጠጣ-ተነሳ- በላ-ጠጣ-ተኛ ወይም በላ-ጠጣ-ተኛ-ተነሳ-ተራበ-ተጠማ ብቻ ሲሆን የሚለው ሌላኛው የታሪክ ክሽፈት ምሰሶ የሚያመለክተው የታሪክ ዓላማን ከመሳት አንጻር ነው፤ ካለፈው ዘመን በጎና በጎ ያልሆኑ ተግባራት ትምህርት መቅሰም ሳይቻል ሲቀር ነው ፡፡ 3.2 የክሽፈት ታሪክ ሲባል…. የክሽፈት ታሪክ ማለት በመጽሀፉ ገጽ 28 ላይ እንደተመለከተው በዘመናት ሂደት የህዝብ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ከመሻሻልና ከማደግ ይልቅ ቁልቁል ሲወርድ፤ የሃለኛው ትውልድ ከቀደመው ትውልድ በአንጻራዊነት የተሻለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ህዝቡ የመንፈሳዊና ቁሳዊ ብልጽግናው እየከዳው ሲሄድ የሚያመላክት ነው፡፡ 3.3 የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት ቁርኝት……. በአዳፍኔ መጽሀፍ ተደጋግሞ እንደተነሳው በኢትዮጵያ ህዝብ የትውልድ ቅብብሎሽ ህዝቡ በመንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሀብቱ ከመሻሻል ይልቅ እየተዳከመ የመጣ ህዝብ ነው፡፡ ይህም የክሽፈት ታሪክ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የክሽፈት ታሪክ ምን ወለደው ለሚለው የፕሮፌሰሩ መልስ ይህ ነው፡- “….በዋናነት የመክሸፍ ምንጩ ሀለት ይመልሰለኛል፤ አንደኛው ትናንትን አለማስታወሰ ይመስለኛል፤ ሁለተኛው ነገን አለማሰብ፤ ትናንትን አለማስታወስ ማለት ታሪክን አለማወቅ (ነው) ….. ክብርና ኩራትን ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብና ሳንመዝን ለማይገባው (መስጠት ነው) ፤ በውጤቱም የሰራው እየተረሳና እየኮሰሰ፣ ያልሰራው እየተወሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤……… ስለዚህም መስራት የማያስከብርና የማያከብር ይሆናል፡፡” ገጽ 73 ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የታሪክ ክሽፈት ለክሽፈት ታሪክ ሰበብ መሆኑን ነው፡፡ እናም በታሪክ ክሽፈት ውስጥ የከሽፈት ታሪክን እናያለን ማለት ነው፡፡ 4. የታሪክ ክሽፈት ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር 4.1 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ማሳያዎች ….. ኢትዮጵያ የሶሰት ሺህ ዓመት ያላት አገር ናት፡፡ እንዲያውም በ2012 ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹The Hidden History of Ethiopia and Jews> በተሰኘው መጽሀፋቸው የኢትዮጵያ ታሪክ እስከ አራት ሺህ ዓመት ይደርሳል; ምን ይመስላል› ፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ታሪክ የትናንታን ኢትዮጵያ በጊዜና በቦታ ርቀት የሚስቃኝ ነው ወይስ….. ታሪካችን በይዘቱ የህዝቡን የዘመናት የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ በተማላ ሁኔታ የሚዘግብ ነው ወይስ…..የኢትዮጵያ ታሪክ አገሪቱና ህዝቦቻ በዘመን ሂደት ያለፉበትን ከፍታና ዝቅታ ትክክለኛ ምስል ያሳየናል ወይስ……. ከታሪክ ማህደራችን የትውልዶችን ሽግግር ማየት እንችላለን ወይስ……..፣ የታሪክ ትርክቱ ተዓማኒነት እስከምን ድረስ ነው….. የሚሉትን ጉዳዮች መመርመሩ የኢትዮጵያን የታሪክ የክሽፈት መንገድ የሚጠቁመን ይሆናል፡፡ ከአደፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ታሪክ በጊዜና ቦታ ርቀት፣ በይዘት ጥልቀት እንዲሁም በተዓማኒነት ሚዛን ሲለካ ብዙ ጎዶሎዎች ያሉት መሆኑ የክሽፈቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ከመጽሀፉ በመጠቃቀስ ለማሳየት ልሞክር፡ ሀ) ከጊዜና ቦታ ርቀት አንጻር የኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ምስል በአግባቡ አያሳይም፡- “የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው ከመሃሉ ወይም ከአሁኑ ነው፡፡” ገጽ 97 ለ) ከይዘት ጥልቀት ሚዛን አካያ ከፈተሸነው ታሪካችን ጎዶሎ ነው፡፡ የነገስታትና የጦርነት ጉዳዮችን እንጂ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ የኑሮ ውጣ ውረድ ከታሪክ ድርሳናት አናገኝም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን ሲገልጹ፡- “….ኢትዮጵያዊያን ብዙ የምንኮራበት ታሪክ አለን፡፡ ዞሮ ዞሮ የኩራታችንና የክብራችን ታሪክ አገራችንን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክለን ከማቆየታችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በትምህርትና በምርምር፣ በስነጽሁፍና በስነትበብ፣ በዕውቀትና በፍልስፍና ኑሮነ ለማሻሻል በሚያስፈልጉ ዘዴዎች ፣ በመመላለሸና በመገናኛ ዘፈዴዎች፣ በምህንድስና በእጅቨ ስራ……ወዘተ ምንም ዓይነት እድገትና መሻሻል አለማሳታችን ታሪካችን አያወሳም፡፡ “ገጽ 28 ሐ) የተመዘገበው ታሪካችን ጥሩ ጥሩውን ብቻ እንጂ ድክመቶታችንን የሚያሳየን አይደለም (ገጽ 28)፡፡ 5. ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ ማነው? 5.1 አዳፍኔና የታሪክ ከሽፈት…….. ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ ናቸው የሚላቸው ሶስት አካላት በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞች(መሪዎቸ)፣ ህዝቡ እንዲሁም የታሪክ ጸሀፊያን (ምሁራን)ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጀርባ ሆኖ የታሪክ ክሽፈቱን የሚያፋጥነው ደግሞ አዳፍኔ ነው፡፡ ለታሪክ ክሽፈት ተባባሪ የሆኑት ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካላት እንዴት ለታሪከ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ አደረጉ የሚለውን ከመቃኘታችን በፊት የአዳፍኔን ምንነትና ባህሪያት ማወቁ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ አዳፍኔ ማነው? 5.1.1 አዳፍኔ ማነው? በመላው ዓለም በተለይም በአፍሪካ መሰረቱ ሰፊ እንደሆነ የሚነገርለት አዳፍኔ ትውልዱ የትና መቼ እንደሆነ እርግጡን መናገር ባይቻልም ወደ ኢትዮጵያ ምድር የገባው በ1928 ዓ.ም ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡ አዳፍኔ በአካሉ ከአንድ ሰው ጉልበት የማያልፍ ትንሽ ነገር ነው(ገጽ 245)፡፡ አዳፍኔ መካካል ይወዳል፤ ከአንገቱ ላይ አብለጭላጭ ጌጥ ጠፍቶ አያውቅም፤ ይህ የአንገት ሀብል የተዋቀረው በቅርጻቸውና በመልካቸው ጉራማይሌ ከሆኑ ቀለበቶች ነው፡፡ እነዚህ የሀብሉ ቅንጣቶች የየራሳቸው መጠሪያ አላቸው፤ ተራ ጸሀፊ፣ ተራ ወታደር፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ህግ፣ ዳኛ፣ የምክር ቤት አባል፣ አስተዳዳሪ፣ የቀበሌ ሰራተኛና አስተዳደር፣ ወዘተ….. ይሰኛሉ፡፡ አዳፍኔ እጅግ የሚወዳቸው ሁለት ልጆች አሉት፡፡ የበኩር ልጁ ፍርሃት ይባላል፤ ተከታዩ ደግሞ መክሸፍ የሚል መጠሪያ አለው፡፡ ፍርሃትና መክሸፍ ለአዳፍኔ ሁለመናው ናቸው፤ ቆሞ የሚሄደው፣ የሚተነፍሰው በእነርሱ ነው፤ ያለነሱ አዳፍኔ ምንም ማለት ነውና አብዝቶ ይንከባከባቸዋል፡፡ በእርግጥ አንገቱ ላይ ያንጠለጠለው ሀብል ሊያጌጥበት አይደለም፤ የልጆቹ ዘብ እንጂ፡፡ እናም አዳፍኔና የሰንሰለቱ ቀለበቶች ታዲያ ውል አላቸው፡፡ ውላቸው ግን ለአዳፍኔ የወገነ ነው፤ የጌታና የሎሌ፡፡ በውላቸው መሰረት ቀለበቶቹ ልጆቹን (ፍርሃትና መክሸፍን) ይንከባከባሉ፤ ለአገልግሎታቸውም ከአዳፍኔ ምንዳ ይቆረጥላቸዋል፡፡ አዳፍኔ በህይወቱ አብዝቶ የሚፈራው ነገር ቢኖር እውነትን ነው፡፡ እውነት የልጆቹ ዋነኛ ጠላት ነው፤ እናም የዕውነት ምንጮች የሆኑት እምነትና እውቀት የዘወትር ስጋቱ ናቸው፡፡ እውነትን ለማጥቃትም የእምነት(ሀይማኖት) እና የትምህርት ተቃማትን ከቻለ ደልሎ ወደራሱ ለማስገባት ካልቻለ ደግሞ በሀይል ለማስገበር ዘወትር ይተጋል፡፡ ለዚህም ጭፍሮቹ ከእርሱ ፍላጎት በተቃራኒ እንዳይሄዱና ከእውነት እንዲጠብቁት ታማኝነታቸውን ለማግኘት ሁለት ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ አንደኛው በጥቅም መደለልና ህልውናቸው በእርሱ መኖር ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ አምነው እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ሌላኛው ዘዴው ደግሞ ወደ እውነትን መንገድ የሚወስደውን መንንድ መዝጋት ነው፤ ለዚህም ጭፍሮቹ እንዳይነቁና እንዳይሰለጥኑ ሌት ተቀን ነቅቶ ይጠብቃል፡፡ ጭፍረቹ አብዝቶ ከሚፈራው እውነት ሊጠብቁት ካልቻሉ አዳፍኔ ለክፉ ቀን መከታ ይሆኑኛል በሚል የሚቀልባቸው ሁለት አካላት አሉ፡፡ እነዚህም የመከላከያና የደህንነት ሀይሎች ይባላሉ፡፡ የአዳፍኔ አይን በመሆናቸውም ሁልጊዜ እንክብካቤው አይለያቸውም፡፡ እንግዲህ ከላይ በስሱም ቢሆን የተዋወቅነው አዳፍኔ ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ሚናው የላቀ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ተባባሪ የሆኑትና ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካላት የአዳፍኔ ውጤቶች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፈን እንደሚሞግቱት አዳፍኔ በታሪክ ክሽፈታችን ውስጥ ራሱን የሚገልጥበት ዋናው መንገድ ታሪካችን በጎ በጎውን ብቻ ነጋሪ፤ የትናንት ውጣ ውረዳችንን የሚያዳፍን መሆኑ ነው፡፡ “…….. (ታሪካችን) አለማደጋችንና አለመሻሻላችን ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ጉድለታችንን ታሪካችን አለመዘገቡ የሚያሳፍር ታሪካችን ነው፤ ……….. በኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ በብዙ ምዕተ ዓመታት ግዙፍ ቦታ የያዘ መስለኛል፡፡ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የማውቀው አንድም ጥናት የለም፡፡” “ገጽ 28 እና ገጽ 50 5.1.2 የኢትዮጵያ ታሪክና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞች (መሪዎቸ) ፕሮፌሰር መስፍን በ‹አዳፍኔ› መጽሀፋቸው ደጋግመው እንዳነሰት ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ በረጅም ዘመን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞችና አገዛዙ ያበቀላቸው ገዢዎች ናቸው፡፡ መገለጫውም ታሪክን ለመበረዝ፣ ለመፈብረክና ለማማፋት ያደረጋቸው የጥፋት ዘመቻዎች ናቸው፡፡ ታዲያ አገዛዙ ለታሪክ ክሽፈቱ ተጠያቂ የሚሆንባቸው አግባቦች ምንድናቸው? ለሚለው መሰረታዊ ጉዳይ መጽሀፉ ሶስት ጉዳዮችን ያነሳል፡፡ እነዚህም፡- • ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል • ህዝቡ ለታሪክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ • የታሪክ መረጃዎችን፣ ምልክቶችን፣ በመደበቅ፤ የታሪክ ጥናትና ምርምርን በማሳነስ 5.1.2.1 ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል…….. የኢትዮጵያን የታሪክ ክሽፈት በመሰረታዊነት የሚገልጸውም የአገዛዙና የታሪክ ዓላማ ልዩነት ነው፤ አገዛዙንና ታሪክን ከቃኘን ዓላማቸው ለየቅል ነው፡፡ የታሪክ ዓላማ የአገርና የህዝብ ኣላማ ነው፤ የታሪክ ዓላማ የእውነት ዓላማ ነው፡፡ የአገዛዙ ዓላማ ደግሞ ግለሰባዊ ነው፤ ፖለቲካዊ ነው፡፡ የታሪክ ምንነት እንዲሁም ዓላማ የሚወሰነው አገዘዛዙና መሪዎቹ የህዝብ ተቀባይነት ለማግኘትና ስልጣናቸውን ለማራዘም እንዲጠቅማቸው በሚያስችላቸው መልኩ ነው፤ በሌላ አገላለጽ ታሪክን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ያውላሉ፡፡ ትክክለኛው የታሪክ ትርክት ከአገዛዙ ኣላማ የሚጋጭ ከሆነ ለእነርሱ በሚስማማ መልኩ ታሪኩን ይበርዛሉ፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ አዲስ ታረክን ይፈበርካሉ፤ ካልሆነም ታሪክን ያጠፋሉ፡፡ “………ቀደም ያለው (አገዛዝ) የሰራውን በሃላ መታው ያፈርሰዋል ወይም ይደብቀዋል፤ ታሪክን የአገርና የህዝብ አድርጎ በመመልከት ፋንታ የግል በማድረግ ታሪክ ያለባህሪው እንዲያትርና በሰው እድሜ እንዲለካ ያደርጋል፤ ታሪክ የሚከሽፍበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡” ገጽ 133 5.1.2.2 ህዝቡ ለታሪክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ ሁለተኛው የአገዛዙ ሀጢአት ደግሞ ህዝቡ ለታሪክ ትክክለኛ ምንነት፣ እንዲሁም ዓላማ ያለው ግንዛቤ የተዛባ እንዲሆን ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያውን ማስፈጸሚያ መሳሪያ ለማድረግ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ለታሪክ ምንነት፣ ዓላማና ግምት የተሳሳተ ከሆነ አገዛዙ እንዳሻው ወይም ሲፈልግ ታሪክን ሊበርዝ፣ ሊፈበርክ፣አልያም ሊያጠፋ ይቻለዋል፡፡ በረጅም ዘመን የኢትዮጵ ታሪክ አገዛዙና ሀይማኖት፣ በተለይም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በህዝቡ ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ የነበራት ሚና የላቀ ነበር፡፡ ከታሪክ ክሽፈት አካያም የሁለቱም አስተዋጽኦ ተደጋጋፊ ነው፡፡ “………አገዛዙና ሀይማኖት የሰውን ልጅ ተቃርጠው፣ ለሁለት ገንጥለው ሥጋውን ለአገዛዙ ነፍሱን ደግሞ ለሀይማኖት አድርገው ተካፍለዋል፤ አንዱ ሥጋውን የበደለ ለነፍሱ ሲል፣ ሌላው ከሰው መርጦ ለሹመት እያለ የመሳፍንትና መካንንት አደግዳጊዎችን ያጠናክራል፡፡” ገጽ 64 አላማው ህዝቡ የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ እንዲኖረው ማድረግ ሲሆን፤ መሳሪያው ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ ነበር፡፡ በመጽሀፉ እንደተገለጸውም፡- “…………ከአጤ ምኒልክ ዘመን በፊት በኢትዮጵያ ት/ቤት በመባል ሚታወቀው በክርስቲያንና እስላም ካህናት የሚካሄደው ነበር………….የባህላዊው ትምህርት ዓላማውና ስርዓቱም ከቤተ ሀይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ……. (ዓላማውም)ሰዎችን ወደ እግዚአብሄር እንዲቀርቡ ለማድረግ ሲሆን አቀራረቡም ከጸሎት ወይም ከልመና የማያልፍ ነው፤ ይህም ማለት በበጎ ተግባር ላይ ሳይሆን፣ ወይም ለግል ኑሮ እያንዳንዱ ሰው ያለበትን ሃላፊነት በማስታወስ ሳይሆን መለመንን እንደችግር መፍቻ በማድረግ ነው፡፡” ገጽ 63፣ ገጽ 65 ባህላዊው የትምህርት ስርዓት ህዝቡ ኑሮው በአምላክ ፍቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ፣ በትናንት ድሉም ሆነ ተግዳሮቶቹ ሚናው ዜሮ እንደሆነ ይሰብካል ፡፡ ይህ በመሆኑም ህዝቡ ታሪክን የሚረዳው “……በእግዚአብሄር ፍቅርና ጥላቻ መስመር (ነው)” (ገጽ 181)፤ ስለሆነም የትናንቱን ከፍታም ሆነ ዝቅታ ማስታወስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው የታሪክ አረዳድ ትክክለኛውን የታሪክ ምንነትና ዓላማ የሚሽር ነው፡፡ 5.1.2.3 የታሪክ መረጃዎችንና ምልክቶች በመደበቅ፣ ጭራሹኑ እንዲጠፋ ለማድረግ በመሞከር ያለፉት ዘመናት በጎ ስራዎች እንዳይመዘገቡ፣ ጭራሱንም እንዳይታወቁ ለማድረግ መሞከር ሌላኛው አገዛዙ በታሪክ ላይ ያደረሰው ጥፋት ነው፡፡ ይህን ለማሳየት በመጽሀፉ የተጠቀሰው ዋናው አስረጅ ከ1933 ዓ.ም በሃላ የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው፡፡ በቅርቡ ታሪካችን ታላቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የአርበኞች ታሪክ ተደብቆ አንዲቀር የተደረገውም በአጼ ሀይለስላሴ መሰሪነት እንደሆነ ተጠቁማል፡፡ ከፋሺስት ቅኝ አገዛዝ አገራቸውንና ህዝባቸውን ነጻ ለማውጣት በዱር በገደሉ የተዋጉ፣ የተጋደሉ አርበኞች የአገዛዙ ኢላማ ሆነው፣ በክፉ ቀን ለባንዲራቸው ያደረጉት ተጋድሎ ተረስቶ የውርደት ካባ እንዲለብሱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይባስ ብሎም ለስደትና ለሞት የተዳረጉ ታላላቅ አርበኞች ነበሩ ( ገጽ 124-125፣ ገጽ 142፣ ገጽ 157 )፡፡ 5.1.3 የኢትዮጵያ ህዝብና የታሪክ ክሽፈት የኢትዮጵያ ህዝብ ለታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ሁለት ምክንያቶች ያላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ህዝቡ ለታሪክ የሰጠው ቦታ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ስለታሪክ ምንነትና ዓላማ ከሰጠው የተሳሳተ ትርጋሜ የመነጨ ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኮነንበት አግባብ ደግሞ ታሪኩን ጽፎ ለትውልድ እንዲተው እንዲያስችለው ዋነኛ መሳሪያ የሆነው የፊደል (ጽሁፍ) ጥበብ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረ ቢሆንም ህዝቡ ግን ይህን ታላቅ አጋጣሚ አልተጠቀመበትም እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን በእግዚአብሄር ፍቅርና ጥላቻ መስመር ነው (ገጽ 181 ) ይህ የታሪክ አረዳድ የሚያሳየው ያለፈው ዘመን ተግባራት ሁሉ የተከናወኑት በሰው ፍቃድ ሳሆን በፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ስለሆነም የዛሬው የሰው ልጅ ተግባራት የነገ ታሪኩ እንደሆነ አልተረዳውም፡፡ ይህ የታሪክ የተሳሳተ የታሪክ ምንነት ግንዛቤ ታሪክን መሰረታዊ አላማና አስፈላጊነትን ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ በውጤቱም፡-  ህዝቡ ለታሪክ ትምህርትና ዕውቀት አስፈላጊነት ዝቅተኛ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የዛሬን ሁነቶች መዝግቦ ለነገው ትውልድ የማየቆት ልማድ አያዳብርም  በዚህም ህዝቡ ለታሪክ መረጃዎችና መዛግብት ዝቅተኛ ግምት ይሰጣል፤ በመሆኑም የታሪክ መረጃዎች ተጠብቀው እንዳይዳብሩ ተጠብቀው እንዲቆዩ የህዝቡ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ 5.1.4 የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፊያንና የኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬ ላይ የምናገኘው የኢትዮጵያ ታሪክ ማህደር በአገር ውስጥ (ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው) እና በውጭ አገር የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት የተደራጀ ነው፡፡ የታሪክ ጸሀፍቱ ታሪክን ሲጽፉ ታዲያ ለኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ዕድገት በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ታሪክ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ማወደስ ያስፈልጋል፡፡ በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍም ይህ ተጠቅሳል፤ ይህ ሲባል ግን ጸሀፍቱ ሁሉ ታሪክን ለመጻፍ ሲሞክሩ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ስነ-ጽሁፍ እንዲዳብር ቀናኢነት ነበራቸው ብሎ መውሰድ ተሳሳተ ነው፡፡ በእርግጥም የታሪክ ጸሀፍት እንዴት ለታሪክ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ፕሮፌሰሩ የሰጡትን ትንታኔ ለመረዳት በኢትዮጵያን ታሪክ ዙሪያ የጻፉ ምሁራንን (ጸሀፍትን) ማንነት መመርመር ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ጸሀፍቱ ታሪክን ለመጻፍ ሲነሱ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ወይስ……..? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍ እንደተጠቆመው ጸሀፍቱ ኢትዮጵያዊያን ወይስ የውጭ ዜጎች‹፤ በሁለቱም ጎራ ያሉ ጸሀፍትን የድሮ ወይስ የአሁን ብሎ መከፋሉ በስራዎቻቸው ሚዛናዊነት፣ ተዓማኒነት፣ ጥራት ወዘተ……. ላይ የራሱ እንድምታ አለው፡፡ 5.1.4.1 የውጭ ጸሀፍትን በተመለከተ የድሮ የውጭ ጸሀፍት ሲባል…… የድሮ የታሪክ ጸሀፍትን ማንነት በመጽሀፉ በገልጽ ማግኘት አልቻልሁም፡፡ ሁለት ነገሮችን ማወቅ መልሱን ለማግኘት ቁልፍ ነው፡፡ አንደኛው የጸሀፍቱ ማንነትና ስራዎች ሲሆን ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ የተጀመረው መቼ ነው፣ በዘመኑ የነበሩ ጸሀፍት ማንነትና ታሪክን ከመጻፍ አካያ የነበራቸው መለያ ባህሪያትስ የሚለው ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት የድሮዎቹ የውጭ ጸሀፍት መለያ ያሉት ግዕዝን የተማሩ፣ ከኢትዮጵዊያን ጋር ቀርበው ለማወቅ የቻሉ፣ የኢትዮጵያዊያዊያንን ቃንቃና ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ የሚል ነው፡፡ይህ ቢያንስ ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ፍንጭ ሰጥቶኛል፡፡ ለሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ ግን መጽሀፉ ያለው ነገር የለም፡፡ እናም ፐሮፌሰሩ የድሮ ጸሀፍት ሲሉ እነማንን ነው› ለሚለው መልስ ለማግኘት መረጃ ማፈላለግ ነበረብኝ፡፡ ካገላበጥካቸው ስራዎች ውስጥ ግን ታዬ አሰፋ እና ሽፈራው በቀለ የተባሉ ምሁራን በጋራ ያሳተሙትን The Study of Amharic Literature: An Overview የሚለው ጥናት አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ “……..ከ1870ዎቹ ጀምሮ በአማርኛ ስነ ጽሁፍ ላይ በርካታ ለውጦች መታየት ጀመረ ፡፡ ይህንንንም ከሶስት አቅጣጫዎች ማየት የቻላል፡፡ የመጀመሪያው በርካታ የውጭ ጸሀፍት በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ላይ ጥናት ለማድረግ የተነሳሱበትና ተሳትፎ ማድረግ የቻሉበት መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ኢጣሊያዊው ኮንቲ ሮሲኒ፣ ጀርመናዊው አውግስቶ ዲልማን፣ ፈረንሳዊው ዞተንበርግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሁለተኛ ይህ የዘመን ማዕቀፍ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ጥራት ያላቸው የስነ ጽሁፍ ስራዎች መታየት የጀመሩበት ነበር፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በቀደመው የኢትዮጵ የስነ-ጽሁፍ ክምችት ውስጥ እምብዛም ያልነበሩት ታሪካዊና ፊሎሎጂካዊ ( ) ዘውግ ያላቸው መጻህፍት በስፋት ተጽፈዋል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ የትምህርት ተቃማት በተለይም በጀርመንና ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ጥናት ማዕከላት ተቃቁመዋል፡፡ ጸሀፍቱም የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ እንደመረጃ የሚጠቅማቸው ድርሳናት በግዕዝ ቃንቃ የተጻፉ ስለነበሩ ቃንቃውን ማወቅ ነበረባቸው፡፡ በዘመኑ የአውሮፓ ታላላቅ የትምህርት ተቃማት ግዕዝ ቃንቃ በስፋት መሰጠት ተጀምሮ ነበር፡፡” (ገጽ 28) በፕሮፌሰር መስፍን እይታ መሰረት በዋናነት የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ዘመቻ ተጀመረው በፋሺስት ወረራ ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ዓላማዋን ለማሳካት እንዲያግዛት የኢትዮጵያን ታሪክ መበረዝ እንደ ዋነኛ መሳሪያ ተጠቅማለች፡፡ ከላይ ከተመለከተው እንደምንረዳው ከዘመን አካያ ስናየው ፕሮፌሰር መስፍን የድሮዎቹ የውጭ ጸሀፍት የሚላቸው ከ1870ዎቹ እስከ 1920ዎቹ የተነሱትን ነው፤ ዓላማቸውም ዕውቀትን ለማስፋፋት ነበር፡፡ የኃለኞቹ የውጭ የታረክ ጸሀፍት ሲሉ…….. ፕሮፌሰር መስፍን የሃለኞቹ የታሪክ ጸሀፊያን የሚላቸው ከ920ዎቹ ጀምሮ የተነሱትን ነው፡፡ በተለይም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ታሪክን እንደዋነኛ መሳሪያ ተጠቅማለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል መንሳታቸው ለመላው ነጮች ሽንፈት ነው ብለው የሚያምኑ አውሮፓዊያን ጸሀፍት የኢትዮጵያን ታሪክ በመበረዝና፣ አዳዲስ የታሪክ ትርክቶችን በመፈብረክ ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተግተዋል፡፡ የኃለኞቹ የታሪክ ጸሀፊያን ዓላማቸው ታሪክን በሚዛናዊነት መጻፍ፣ ዕውቀትን ለማስፋፋት አይደለም፤ ይልቁንም ቁሳዊ ፍላጎታቸው ለማማላት፣ ታሪክን እንዲጽፉ በገንዘብ የሚረዳቸውን ተቃም ለማስደሰት፣ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ነው፡፡ የውጭ አገር የታሪክ ምሁራንና የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍ እንደተመለከተው ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በማስተማርም ሆነ በጥናት እና ምርምር ዋነኛ ተዋናዮች የነበሩት የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ የውጭ ዜጎች ታሪካችንን መጻፋቸው ክፋት ባይኖረውም (ገጽ 212) በስራዎቻቸው ግን ትክክለኛና የተማላ ታሪክ አንዳናገኝ የሚያደርጉ ቢያንስ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህንንም ፕሮፌሰር መስፍን የገለጹት እንዲህ ነው፡- “………ከአንድ አገር ሰዎች ከራሳቸው የሚፈልቅ መረጃ ወይንም ዕውቀት ከዚያ አገር ህዝብ በራቀ መጠን ጉልበቱ ይቀንሳል፤ የአገሩ ሰዎች መረጃውን በመተርጎሙና በማጠናቀሩ በኩል የተሻሉ በመሆኑ (ነው)፡፡ ……….. (የውጭ የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት) የጎሳ ስሜትን በመቀስቀስ…ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሆነዋል፡፡” (ገጽ 212፣ ገጽ 214) ከታሪክ ክሽፈቱ አንጻር የድሮዎቹና የአሁኖቹ የውጭ ጸሀፍት ስራዎች አደገኛነት ይለያያል፡፡ በዚህም የድሮዎቹ ስራዎች ከአሁኖቹ የተሻለ ተ”ዓማኒነት አላቸው፡፡ ለዚህ ምክንያት ተብሎ በመጽሀፉ የተጠቀሰው የሚከተለው ነው፡- “………..የዱሮዎቹ ግዕዝ ሳይቀር እየተማሩ በግእዝ የተጻፉትን ሁሉ በየቃንቃቸው ይተረጉሙ ነበር፤ እነዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ ያጠኑ የነበረው የየሀገራቸውን ምሁራን ዕውቀት ለማበልጸግ ነበር፤ የሃለኞቹ ምንደኞች ናቸው፡፡” ገጽ 213 5.1.4.2. ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍትን የድሮዎቹና የአሁኖቹ ሲሉ በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ለዚህም መሰረት ያደረጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ጸሀፍቱ ያለፉበት የትምህርት ስርኣት ሲሆን ሌላው ደግሞ የጸሀፍቱ ግለሰባዊ(ቤተሰባዊ) ማንነት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የጸሀፍቱን ስራዎች ተዓማኒነት የሚወስኑ ናቸው፡፡ የድሮዎቹ ጸሀፍት ከጸሀፍቱ ማንነት አንጻር በተነጻጻሪነት የድሮዎቹ ጸሀፍት ከጥቅመኝነት የራቁ፣ ዓላማቸውም ዕውቀትን መመርመር ነበር፡፡ እነዚህ የታሪክ ጸሀፍት በአብዛኛው በባህላዊው የትምህርት ስርዓት ያለፉ ናቸው፡፡ በዚህም ከተበላሸው የዘመናዊው ትምህርት ስርዓት የጸዱ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ ለመጻፍ ችለዋል፡፡ በተስተካከለ የታሪክ ትምህርትና ጥናት ያለፉ የሚላቸውን ምሁራን ለመጥቀስ ሞክረዋል፡፡እውነተኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማወቅ የፈለገ ሁሉ የፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ እና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ስራዎች ሊያነብ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ (ገጽ98) የአሁኖቹ ጸሀፍት የሃለኞቹ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ታሪክን በአግባቡ እንዳይጽፉ ያደረጉ ምክንያቶች ሁለት እንደሆኑ ፕሮፌሰሩ ይሞግታሉ፡፡ አንደኛው የታሪክ ጸሀፍቱ ያለፉበት መንገድ የተበላሸ መሆኑ ነው፡፡ሁለተኛው ደግሞ አብዛናው ጸሀፍት የባንዶች ልጆች መሆናቸው ነው፡፡ ያለፉበት የትምህርት ስርዓት የተበላሸ መሆኑ ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚገልጹት አብዛኛው የዛሬው ጸሀፍት ታሪካቸውን ሳይቀር የተማሩት በውጭ ምሁራን ነው፡፡ “…..የእኔ ትውልድ ከውጭ አገር ሰዎች ተማረው የኢትዮፕያ ህዝብ ከነባህሉ የአረብ ተወላጅ ተደርጎ ነው፤ የእኛ ነው የምንለው ነገር ሁሉ ከአረብ ያገኘነው መሆኑን እየነገሩን እኛም በተራችን ያንኑ ለተከታዩ ትውልድ ስናስተላልፍ ቆየን፤ የሴም ቃንቃ፣ ነገረ መንግስት፣ እረሻ፣ ጽህፈት፣ ወዘተ…..ሁለም ነገር ከባህር ማዶ ያገኘነው እየተደረገ ተማርን፤ እኛም በበኩላችን አስተማርን፡፡” ገጽ 116 በዚህ አይነት የትምህርት ስርኣት ያለፉ የታሪክ ጸሀፍት የአገራቸውን የሚንቁ፣ በአንጻሩ ነጭ አምላኪ ሆነዋል፡፡ የዛሬዎቹ ጸሀፍት ከአገራቸው ታሪክ መረጃዎችና ምንጮች ይልቅ በውጭ ምንጮች ላይ ማተኮራቸው፣ የአገር ውስጥ የታሪክ ምንጮችን እንደማስረጃ አድርጎ ለመውሰድ አለመፈለግ የዚህ ነጸብራቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ እንዲያውም ‹ተረት› የሚላቸውን እንደክብረ ነገስት፣ ፍትሃ ነገስት ያሉትን እንደታሪከ ምንጮች አድርጎ መውሰድ ባይቻል እንካ ቢያንስ ለመመርመር ሲሞክሩ አይታይም (ገጽ 231)፡፡ የጸሀፍቱ ግለሰባዊ ማንነት አብዛኞቹ የዛሬ ጸሀፍት የባንዶች ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ጸሀፍት የወላጆቻቸውን የባንዳነት ሃጢኣት ንስሃ ገብተው ለመንጻት ከመሞከር ይልቅ ሃጢያታቸውን ለመሸፋፈን ታሪክን በመበረዝ ለመሸሽ ሞክረዋል፡፡ “…………….በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን ታሪክ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው እንደሚመች እያደረጉ በመተርጎም የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ታሪክ ያበላሻሉ፤ እያበላሹም ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮፕያን ታሪክ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተለየ ባለመሆነኑ ከመቶ ዓመታት አይበልጥም የሚባለው የባንዶች ልጆች የፈጠሩት የሻዕቢያና የወያኔ ተረት ነው፤ ባንዳዎች ያልነበሩ የኤርትራና የትግራይ ሰዎች ይህንን የፈጠራ ታሪክ አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም የብዙዎቹ አባቶች በኢትዮፕዊነታቸው ኮርተው በአርበኝነት የሞቱ ወይም የተጎዱ ይሆናሉ፡፡” (ገጽ ——) ፕሮፌሰሩ ሁሉንም የታሪክ ጸሀፍት በጅምላ አልወቀሱም፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ህጸጾች የጸዱ ናቸው፣ በዚህም የኢትጵያን ታሪክ ለማወቅ የፈለገ ሁሉ ስራዎቻቸውን ሊያነብ ይገባል ያላቸውን እንደ ፕሮፌሰር አለም እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የመሳሰሉ ምሁራንን አወድሰዋል (ገጽ 98) ፡፡ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ክሽፈት ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት በሶስት መልኩ ለታሪክ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እነዚህም ለታሪክ ያላቸው የተዛባ ግንዛቤ፣ ታሪክን በሚዛናዊነት አለመጻፍ እና ታሪክን ሲጽፉ ለአገር ውስጥ የታሪክ ድርሳናትና የታሪክ ምንጮች አነስተኛ ግምት መስጠታቸው ነው፡፡ የተዛባ የታሪክ ግንዛቤአቸው እንደፕሮፌሰር መስፍነ እምነት አብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ታሪክ “ለአንድም ሰኮንድ የማቃርጥ የሰው ልጆች የአናናር ጅረት መሆኑን አልተረዱትም (ገጽ 98)፡፡ ከዚያ ይልቅ ታሪክን እንደ ተረት…መነሻ የሌለው፣ አቅጣጫ የሌለውና ዓላማ የሌለው አድረገው በጊዜ በታጠረ ብቅ ጥልቅ ውስት የሚነገር ተረት አድርገውታል……..(ታሪክን) በሁለት እግሩ ብቻውን ቆሞ የሚሄድ ነፍስ ያለው ነገር አድርገው ይወስዱታል”፡፡ (ገጽ 50፣ ገጽ 98) የታሪክ ጸሀፍት በሚዛናዊነት ታሪክን አለመጻፍ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት በብዙ መልኩ በገለልተኝነት ታሪክን ለመጻፍ አልቻሉም፡፡ “………(ጸሀፊያኑ) ለስልጣን በማጎብደድና ለጥቅም በመገዛት ሁነትን ሁሉ በአገዛዙ መነጽር ብቻ እያዩ ያንኑ ስህተት ለተከታታይ ትውልዶች እያስተላለፉ ስህተቶቹ እንዳይታረሙ ያደርጋሉ፡፡” ገጽ 30 የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፍትና የታሪክ የመረጃ ምንጮች ከታሪክ ክሽፈት አንጻር ታሪክ በተማላና በትክክለኛ ሁኔታ እንዲጻፍ የታሪክ የመረጃ ምንጮች ተዓማኒነት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ታሪክን ለመጻፍ ሲነሱ እንደዋና ግብኣታቸው አድርገው የሚጠቀሙት የውጭ ጸሀፍት ስራዎችን ወይም ውጭ ምንጮችን ነው፡፡ አገር በቀል የሆኑ የታሪክ ድርሳናትን የማሳነስ ሁኔታ በጸሀፍቱ ይታያል (ገጽ 212፣ 232)፡፡ ጸሀፊያኑ ለዚህ የሚያቀርባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የአገር ውስጥ የታሪክ ድርሳናት ማገኘት አስቸጋሪ ነው የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ ነባር የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፍትና ስረዎች የሚዛናዊነት ጉድለት ይታባቸዋል የሚለው ነው፤ ሚዛናቸውን የሚያጋድለው ዋናው ነገር ደግሞ ጸሀፍቱ ለሚወክሉት ብሄር አድልተው መጻፋቸው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚከራከሩት ኢትዮጵዊያን የታሪክ ጸሀፍት ወደ ውጭ ምንጮች እንዲዞሩ በምክንያትነት የሚያቀርባቸው ሁለቱ ምክንያቶች መሰረተ ቢስ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ መረጃዎች አነስተኛ መሆን ለሚለው ያሉትን መቼ ለመመርመር ሞከርን; ፍላጎቱም የለንም ሲሉ መልሰዋል፡፡ ወደ ውጭ ምንጭ ማማተሩ እንደምክንያት ለሚነሳው ሁለተኛው ጉዳይ የሰጡት ምላሽ ደግሞ የኢትዮጵያ ጸሀፍት ስራ ሚዛን ያጋደለው ጸሀፍቱ ከጥቅመኝነት፣ ጥገኘነትና ከፍርሃናትና ስጋት ነጻ አለመውጣታቸው እንጂ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሀፍት የዘር ሀረጋቸው ለሚመዘዘበት ጎሳ አድልተው ይጽፋሉ የሚለው ጉዳይ አሳማኝ እንዳልሆነ ፍንጭ ይሰጣሉ (ገጽ 232)፡፡ በቂ የአገር ውስጥ ታሪካዊ መረጃዎች ከሌሉ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የውጭ የታሪክ ጸሀፍት ስራዎችን እንደመረጃ ወስዶ ታሪክ መጻፉ ጉዳት የለውም ፡፡ ጸሀፍቱ ወደ ውጭ መረጃዎች ፊታቸውን ሲያዞሩ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ስላለባቸው ጉዳዮች ጽፈዋል፡፡ አንደኛ የጸሀፍቱን ማንነት ከመመርመር አንጻር ነው፡፡ በድሮዎቹና በአሁኖቹ የውጭ አገራት የታሪክ ምሁራን መካከል ልዩነት አለ፤ የድሮዎቹ የሚጽፉት ዕውቀትን ለማበልጸግ ሲሆን የአሁኖቹ ግን ምንደኞች ናቸው፡፡ ስለሆነም የድሮዎቹን ጸሀፍት ስራዎች እንደማጣቀሻ መውሰዱ የተሸለ ነው፡፡ ሁለተኛ የውጭ ጸሀፍት ታሪክን ሲጽፉ ዓላማ አድርገው የሚነሱት እውነተኛ ታሪክን ለመጻፍ ነው ወይስ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ አላቸው ብሎ መጠራጠር ያሻቸዋል፡፡ይህን ሳይመረምሩ እንደወረደ ስራዎቹን አምኖ ተቀብሎ እንደማጣቀሻ መውሰድ አደገኛ ነው (ገጽ 213)፡፡ ሶስተኛ የውጭ ስራዎች እንደምንጭ መውሰድ የመረጃው ጥራት(ተዓማኒነት) ያሳንሳል፡፡ ይህም የሚጻፈው ታሪክ ተዓማኒነት የጎደለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህን ሲያብራሩም፡- “……….ከአንድ አገር ሰዎች ከራሳቸው የሚፈልቅ መረጃ ወይንም ዕውቀት ከዚያ አገር ህዝብ በራቀ መጠን ጉልበቱ ይቀንሳል፤ የአገሩ ሰዎች መረጃውን በመተርጎሙና በማጠናቀሩ በኩል የተሻሉ በመሆኑ (ነው)፡፡” (ገጽ 212፣ 213) ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ኢትዮጵየያዊያን ጸሀፍት ወደ ውጭ ምንጮች አብዝተው ማማተራቸው ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ጸሀፍቱ የባንዶች ልጆች መሆናቸው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በትክክለኛ የትምህርት ስርዓት አለማለፋቸው ነው፡፡ 6 የታሪክ ክሽፈቱ ያመጣብን መዘዞች እንደ ፕሮፌሰር መስፍን እምነት የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት አገሪቱንና ህዝቦቻን ብዙ ዋጋ አስከፍላል፡፡ በአዳፍኔ መጽሀፍ በተለያየ መንገድ የተገለጹ ሀሳቦችን ከሰበሰብናቸው የታሪክ ክሽፈቱ መዘዞች ሶስት ናቸው፡፡  ከኢትዮጵያ አንድነት አንጻር  ኢትዮጵያ በቁሳዊ ስልጣኔ ሃላ ቀር እንድትሆን ከማድረግ አንጻር  ከኢትዮጵያ መንፈሳዊ ስልጣኔ (ሉዓላዊነት) አንጻር 6.1 የታሪክ ክሽፈትና የኢትዮጵያ አንድነት በመጽሀፉ እንደተገለጸው የህዝብ አንንነትነ የአገር መሰረት የሆነው ህዝቦች በክፉ ጊዜ አንድ መሆን፣ መተባበርና ለአገራቸው ክብርና ሉኣላዊነት ቀናኢነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መሰረትም ይኸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ከታሪክ ክሸፈቱ ጋር አብሮ እየከሸፈ ይገኛል፡፡ በዚህም “……..የአንድ ትውልድ ስህተት ወደሌላ ትወልድ እየተላለፈ ለብዙ ትውልዶች የስህተት ምንጭ (እየሆነ) ታሪካችንንና የኢትዮያን ህዝብ ህዝብነት (በመበከል) ዛሬም እንደቆላ ቁስል እነዘነዘን (ነው)፡፡” ገጽ 29 በመጽሀፉ እንደተብራራው የታሪክ ክክፈቱ አገር እንዲፈርስ በር ከፍታል፤ ለወደፊቱም በር መክፈቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ የቀረበው ደግሞ የታሪክ ክሽፈቱ አንዱ ማሳያ የሆነው የኢትዮጵን ታሪክ ከመሃሉ ወይም ከአሁኑ የመጀመር የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ኤርትራ የኢትዮጵያ መሰረት መሆናን ማስካድ ለጊዜውም ቢሆን ተችላል ( ገጽ 97) የኢትዮጵያ ታረክ ክሽፈት ሌላኛው ገጽታ የሆነው የትናንቱን የኢትዮጵያን ዕውነት መካድ የወደፊቱን የኢትዮጵያ አንድነት የሚያናጋ ነው፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የቀረበው ደግሞ በቀዳማዊ ሀይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ ስልጣን (ታስቦበት የተደረገ ባይሆንም) በመንግስት ስልጣን ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች ስብጥር የመሆኑ ዕውነት ተቀብሮ ያለፈው ስርዓት የአንድ ብሄር ( የአማራ ብሄር) የበላይነት እንደነበር ተደርጎ የሚነገረው የበሬ ወለደ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋና የፖለቲካ ገጽታ የሆነው ጎሰኝነት መሰረቱም ይህ ሀሰተኛ የታሪክ ትርክት ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ጎሰኝነትና እንዲያብብ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲቀጭጭና አገር የመበታተን አደጋ ላይ እንዲወድቅ መሰረት ሆናል፡፡ ይህንን ሁኔታ ፕሮፌሰር የገለጹት በዚህ መንገድ ነው፡- ……..ችግሩ ሁሉ ከአገዛዝ ጋር የተየያዘ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለ…….የአጼ ሀይለ ስላሴና ደርግ አገዛዝ የ‹‹አማራ›› ሆነው በመፈረጃቸው ውግዘቱ ሁሉ ያንን ቃንቃ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ተወረወረ፤ አስተሳሰቡ ቀላል በመሆኑ ዛሬም የወያኔን አገዛዝ የትግሬ አገዛዝ የሚያደርጉት አሉ፤……(ይህ)ከተዛባ አሰተሳሰብ የሚመነጭ ስህተት ነው፡፡ ገጽ 39 6.2 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈትና ቁሳዊ ስልጣኔ የኢትዮጵያ የታረክ ክሽፈት ሌላኛው ገጽታ ህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ዋጋ እንዳይሰጥ ማድረጉ ነው፤ ይህም ከትናንቱ ህይወቱ ትምህርት ወስዶ የነገ ህይወቱን ለማሻሻል እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ የብልጽግናና የለውጥ መሰረት የሆኑ እሴቶች፡ ለአብነትም ጠንካራ የስራ ባህል፣ ትጋት፣ ለገንዘብና ለጊዜ ዋጋ አለመስጠት፣ በጋራ የመስራትና የመተባበር ባህልን በኢትዮጵዊያን ዘንድ ብዙም ቦታ የላቸውም፡፡ “……….ዳገቱን እንዴት እንደወጣንና ቁልቁለቱን እንዴት እንደወረድን በትክክልና በዕውነት (እንድንገነዘብ)፣ ክብርና ኩራት ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብነና ሳንመዝን ለማይገባው (እንድንሰጥ)፣ በውጤቱም የሰራው እየተረሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ተውልድ ይተላለፋል፡፡…..ስለዚህም መስራት የማስከብርና የማያከብር ይሆናል፤……..ሳይሰሩ ለመክበርና ለመከበር መጣር ባህል ይሆናል፡፡”ገጽ 73-74 6.3 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈትና መንፈሳዊ ስልጣኔ (የአገር ሉዓላዊነት) እንደ ፕሮፌሰር መስፍን እምነት የኢትዮጵያ ስልጣኔ መንፈሳዊ ስልጣኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሳይከሽፍ የቆየውም ለዚህ ነው፡፡ ምንም እንካን ኢትዮጵያ በቁሳዊ ሀብትና ዘመናዊነታ ሃላ የቀረች ቢሆንም ድህነታ ግን ለውጭ ወራሪዎች እጅ እንድትሰጥ አላደረጋትም፡፡ ለዚህ ምከንያቱ የመንፈሳዊው ስለጣኔ መገለጫ የሆኑትና ለዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሆነው የኖሩት አርቆ አሳቢነት፣ ሀይማኖተኝነትና ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ መልካም ስነ ምግባር፣ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ለክብርና ኩራት ቅድሚያ መስጠት፣ ለአገር ነጻነትና ሉዓላዊነት መስዋዕትነት ተጋድሎ ማድረግ ወዘተ…. ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ መንፈሳዊ ስልጣኔ እስከመጨረሻው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አልተቻላቸውም፡፡ የታሪክ ክሽፈቱ አንዱ ውጤት የሆነው የህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ያለው ዝቅተኛ ግምት ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በእጅጉ በኢኮኖሚ ወደሃላ አስቀርታታል፡፡ ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ በአዳፍኔ መጽሀፍ የተገለጸው በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ሀይል ኢትዮጵዊያን አርበኞችን በማይጨው የጦር አውድማ ድል መንሳቱ ነበር፡፡ ለዘመናት ተከብሮ የኖረው የአገር ሉኣላዊነት ተደፈረ፡፡ኢጣሊያ ጦር ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ፣ በምድርና በአየር በወገን ጦር ላይ መኣቱን ሲያወርድ ፣ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ግን ከሃምሳ አመታት ቀደም ብሎ በአድዋ ጦርነት ታጥቀው የዘመቱትን ባህላዊ መሳሪያዎች ነበር፡፡ በዚህም፡- “………ኢትዮጵያ ያለችበትን በታም ዝቅተኛና ቆሞ ቀር ደረጃ በተግባር አስመሰከረች፤ይህ አዲስ ዕውነት የኢትዮጵ ህዝብ ለዘመናት የነበረውን አልበገር ባይነት ከነኩራቱና ክብሩ ገፈፈው፤ የመንፈስ ሃይሉ ደቀቀ፤ አንገቱን ደፋ፡፡” ገጽ 133 በአጠቃላይ ከአምስቱ ዓመታት የፋሺስት ወረራ በሃላ በኢትዮጵያን የመንፈሳዊ ስልጣኔው የከሸፈ ይመስላል፡፡ ለግል ጥቅም ሲባል ያልተገቡ አገርን በገንዘበ መለወጥ ወይም ባንዳነት፣ ህዝቡ የአገርን ችግር በአገር ቤት ከመጋፈጥና ለመፍታት ከመጣር ስደትን መምረጡ፣ ኢትዮጵያዊ ክብርና ኩራት እተመናመነ መሄዱ፣ አርበኝነት ቦታ ሲያጣ ባንዳነት መወደሱ ወዘተ.…… ማሳያ ናቸው፡፡ በውጤቱም ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሉኣላዊነት አደጋ ላይ ወድቃል፡፡ በአጠቃላይ የታሪክ ክሽፈቱ መዘዞች በተለይም ባለፉት 85 ዓመታት ጎልተው ታይተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ያቀረቡትን ትንታኔ ጠቅለል ባለ ሁኔታ በሚከተለው ምስል ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ 7. የኢትዮጵያ ታሪክን ከክሽፈት ቁልቁለት እንዴት መታደግ ይቻላል? 7.1 ህዝቡን በተመለከተ የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት አዘቅት ይላቀቅ ዘንድ ህዝቡ የራሱን ሚና መወጣት እንዳለበት ለዚህም በመጽሀፉ መጨረሻ ላይ የምናገኛቸው አስር መፍትሄዎችን መከተል አለበት፡፡ 7.2 አገዘዙን በተመለከተ በመጽሀፉ ላይ አገዛዙ ማድረግ ያለበት ነገር በቀጥታ አልተገለጸም፡፡ይሁንና አገዛዞች ከቀደመው አገዛዝ ስህተቶች መማር፣ መልካም ጎኖች ደግሞ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው በተዘዋዋሪ ይመክራሉ፡፡ “………ቀደም ያለው (አገዛዝ) የሰራውን በሃላ መታው ያፈርሰዋል ወይም ይደብቀዋል፤ ታሪክን የአገርና የህዝብ አድርጎ በመመልከት ፋንታ የግል በማድረግ ታሪክ ያለባህሪው እንዲያትርና በሰው እድሜ እንዲለካ ያደርጋል፤ ታሪክ የሚከሽፍበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡” ገጽ 133 7.3 የታሪክ ጸሀፍትን በተመለከተ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ?

  1. መግቢያ
    1.1 ስለ ደራሲውና ስለ መጽሀፉ አጠቃላይ
    በአማርኛ ቃንቃ ከሚጽፉ እጅግ ጥቂት ኢትዮጵዊያን ምሁራን መካከል አንጋፋው ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አንዱ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚጽፋቸው በሳል ጽሁፎችና በሚያነሳቸው አዳዲስ ጉዳዮች የምሁርነትን ልክ ያሳዩን ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በየሁለት አመቱ ልዩነት ማለት ይቻላል በተከታታይ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ መጽሀፍትን አስነብበውናል፡፡ዘንድሮም (ማለትም በ 2007 ዓ.ም) ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› በሚል አዲስ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡
    ‹አዳፍኔ፡ ፍርሃትና መክሸፍ› በአስር ምዕራፎችና በ280 ገጾች የተደራጀ ሲሆን በግራፊክ አሳታሚዎች ለህትመት በቅታል፡፡ ‹አዳፍኔ› ፕሮፌሰሩ በ2005 ዓ.ም ያሳተሙት ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሀፋቸው ተከታይ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ለዚህም ሁለት አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው ከጭብጥ አካያ ብዙ ተመሳስሎሽ አላቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹አዳፍኔ› ከያዛቸው አስር ምዕራፎች ውስጥ ሶስቱ (ይህም የመጽሀፉን ዘጠና ስድስት ገጾች ወይም 40 በመቶ ያህል ይሸፍናል ማለት ነው) በ ‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ› ላይ በተለያዩ ጸሀፍት ለተሰነዘሩ ትችቶች ምላሽ የሰጡበት( በመጽሀፉ እንደተገለጸው የ‹ ትችቶች ትችት›) ነው፡፡
    በዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ አተያይ የመጽሀፉ ዋነኛ መገለጫዎች(መልኮች) ሁለት ናቸው፤ እነዚህ ሁለት መገለጫዎችም የመጽሀፉ ውበቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው መጽሀፉ በይዘቱ ሰፋ ያለ መሆኑ ነው፤ ከዚሁ ጋር የተያያዘው ሁለተኛው መጽሀፉ በቅርጹና አቀራረቡ የራሱ የሆነ አዲስ ቀለም ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እጅግ በርካታ ጉዳዮችን ይነካል፤ ታሪክ፣ ባህል፣ ስልጣንና አገዛዝ (ፖለቲካ)፣ኢኮኖሚክስ፣ ስነ መንግስትና አስተዳደር (አገር፣ ህዝብና መንግስት)፣ ሀይማኖት፣ ትምህርትና ዕውቀት እንዲሁም ዕውነት፣ ስነ-ልቦና፣ ፍልስፍና እና ሌሎች የጥናት ዘርፎች ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጽንሰ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ ሌላው የመጽሀፉ መልክ ለጥናትና ምርምር፣ ለጥልቅ ውይይትና ክርክር የሚጋብዙ ሀሳቦችን ማንሳቱና በዚሁ በተቃኘ አቀራረብ መዘጋጀቱ ነው፡፡
    1.2 የመጣጥፉ ዓላማ
    ወጣቱ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሀፍ ዙሪያ ያለውን አተያይ ከሁለት አመታት በፊት ገደማ በአንድ መጣጥፉ አስነብቦናል ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል በመጣጥፉ ካነሳቸው በርካታ ቁም ነገሮች አንዱ የክሽፈት ታሪክ እንጂ የታሪክ ክሽፈት የሚባል ሊኖር አይችልም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፋቸው ‹የትችቶች ትችት› በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ለዚህ መልስ ሰጥተዋል፤ ነገር ግን መልሱ አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይህ ሲባል ግን ፕሮፌሰሩ መልስ አልሰጡም ለማለት ሳይሆን የተሰጠበት አግባብ የተደራጀና ግልጽ አይደለም፤ እንዲያውም የአዳፍኔ ዋነኛ ጭብጥ በክሽፈት ታሪክና በታሪክ ክሽፈት ዙሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሀሳቦቹ እዚህም እዚያም ተበታትነው የቀረቡ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ አንባቢ የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረው ያደርጋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
    በዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ እምነት የክሽፈት ታሪክ እና የታሪክ ክሽፈት የሚሉት ሁለት ሀሳቦች ብዙ ጉዳዮችን ያዘሉ በመሆናቸው በጥልቀት መታየት አለባቸው፡፡ በመሆኑም አዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ ስለ ክሽፈት ታሪክና ስለ ታሪክ ክሽፈት ያነሳቸውን ሀሳቦች በማሰባሰብ ለማቅረብ ተሞክራል፤ መጽሀፉ ከአደረጃጀት አንጻር በዚህ ሁኔታ ቢቀርብ መልዕክቱን በይበልጥ ለመረዳት ያስችላል ፤ በመጽሀፉ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በአንባቢያን የሚቀርቡ የውይይትም ሆነ የክርክር ሀሳቦች ቅርጽ እንዲይዙ ለማድረግም ያግዛል፡፡ የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ የታሪክ ክሽፈት፡ ከኢትዮጵያ አንጻር በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የደራሲውን እይታዎችን አጠቃሎ በማቅረብ ለውይይት እንዲመች ማድረግ ነው፤ በመጽሀፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ትዝብት ማስፈር የሚለው ሌላው የመጣጥፉ ግብ ነው፡፡
    1.3 የመጣጥፉ ይዘት
    የመጣጥፉ ይዘት የተቃኘውም ከላይ ለማንሳት ከሞከርኩት ዓላማ አንጻር ነው፡፡ በዚህም በዚህ አጭር ጽሁፍ ለሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ተሞክራል፡፡
     የታሪክ ምንነትና ዓላማ ምንድነው?
     የታሪክ ክሽፈትና የክሽፈት ታሪክ ማለት ምን ማለት? ቁርኝታቸውስ እንዴት ነው ?
     የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር እንዴት ይታያል ?
     ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ተጠያቂው ማነው ?
     የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈቶችና መዘዞች ምንድናቸው ?
     ከታሪክ ክሽፈት ለመውጣት ምን ማድረግ ያሻል ?
     የመጽሀፉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች
    በቅድሚያ ግን ስለታሪክ እና ተያያዥ ጉዳዮች አንዳንድ ሀሳቦችን በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
  2. ስለ ታሪክ ምንነት፣ ባህሪያትና ዓላማ
    2.1 ስለታሪክ ምንነትና ዓላማ
    የታሪክ ፍልስፍና ዘይቤ አባት በመባል የሚታወቀው አውግስሚኖስ የታሪክ ምንነትና ዓላማ ሲገልጸው እንዲህ ነው፡-
    ታሪክ መንግስት መቆሙንና መፍረሱን፣ ህዝቦች ማደጋቸውንና መውደቃቸውን ያትታል፡፡ይህም የሚሆንበት ምክንያት አምላክ ባቀደው መሰረት የሰው ዘር ወደ እውነተኛው ብርሃን ለመምራትና ለማዳን ሲል ነው፡፡
    የፕሮፌሰር መስፍን የታሪክ ምንነትና ዓላማ አረዳድም ከአውግስሚኖስ ጋር በይዘቱ አንድ ነው፣ ቅንቃው ቢለወጥም፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ማለት ፡-
    “…..ለአንድም ሰኮንድ የማያቃርጥ የኑሮና የአናናር ጅረት ነው፡፡ ……..ታሪክ አንድ ህዝብ የስራ መዝገብ ነው፡፡” ገጽ 98-99
    የታሪክ ዓላማ ደግሞ ህዝቡ ያለፈውን ዘመን ከፍታና ዝቅታ አስታውሶ፣ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ በጎ ጎኖች ትምህርት ወስዶ፣ ከችግሮቹ ተምሮ በኑሮው መሻሻል እንዲያሳይ ማድረግ ነው (ገጽ 28፣ ገጽ29 )፡፡
    በአጠቃላይ፡-
    • ታሪክ ማለት የትናንት ዕውነትን (በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ) መመርመር ነው፡፡
    • የታሪክ ዓላማ የሰው ልጅ የትናንት በጎ ተግባራቱን አዳብሮ፣ ከስህተቱ ደግሞ ተምሮ የዛሬና የነገ ህይወቱን እንዲያቀና ማድረግ ነው፡፡ በዚህም አውግስሚኖስ የታሪክን አስፈላጊነትና ዓላማ ከመለኮታዊ ሀይል ዓላማ ጋር ያዛምደዋል፡፡ በዚህም የታሪክ ዓላማ የፈጣሪ አላማ ነው፡፡
    በተለይ ሁለተኛው ሀሳብ ከታሪክ አረዳድ አንጻር ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን በጉዳዩ ላይ ትንሽ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
    2.2 ስለ ታሪክ ባህሪያት
    በግሌ የታሪክ ባህሪ ከአምላክ ባህሪ ጋር ይመሳሰሉብኛል፡፡ ታሪክ አምላካዊ ባህሪዎችን ሁሉ ይወርሳል፡፡ ታሪክን ከአምላከዊ ባህሪ ጋር ለማንጸር ያደረግሁት ጥረት ያልተመቻቸው እንደኔ እንደኔ የአምላክን ባህሪ የማያውቁ ናቸው ባይ ነኝ፡፡ ለመሆኑ የአምላክ ባህሪያት ምንድናቸው ? የታሪክ ባህሪያትስ ?
    በመሰረቱ የአምላካዊነት መሰረት ሀቅ ነው፤ የታሪክ መሰረቱም አንዲሁ ሀቅ (እውነት) ነው፡፡ ፈጣሪ የሰው ልጆችን ጨምሮ በአጠቃላይ በፍጡራን ላይ ፍጹም ስልጣን አለው፤ ታሪክም ይህ ስልጣን አለው ፡፡ የፈጣሪ ዓላማ የሰው ልጆቸ ሁሉ በቀና መንገድ እንዲያልፉ ማስተማር ነው፤ የታሪክ ዓላም እንደዚሁ ነው፡፡ ወደር የለሽ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት አምላካዊ ባህሪ ነው፤ ዓላማውም ሰዎች በራሳቸው ከጥፋት መንገድ እንዲታቀቡ፣ ካለፈው ስህተታቸው እንዲታረሙ ጊዜ መስጠት ነው፡፡ የታሪክ መንገድም ይህ ነው፡፡ በመሰረቱ ዕውነትን(ታሪክን) መበረዝ ወይም ማጥፋት የሚቻል ሊመስለን ይችላል፡፡ መሪዎችም ይህን ለማድረግ የቻሉ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን በጥልቀት ከመረመርነው አልቻሉም፡፡ የፈጣሪን ትዕግስት ዓላማ ያልተረዱም በስህተት ላይ ስህተት ላይ እየፈጸሙ በመጨረሻም ከነጭራሹ የፈጣሪን ስልጣን ሲመኙ፣ ሲብስም ህልውናውንም ሲክዱ መቀበሪያቸውን ጉድጋድ እያበጁ እንደሆነ ሳይታወቃቸው፣ የትዕግስቱ መብዛትም በቆፈሩት ጉድጋድ እንዲቀበሩ ያደረጋቸዋል፡፡ የታሪክም መንገድ ይህ ነው፡፡ ታሪክ ከስህተት ለመማር እድል ይሰጠናል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ ግን በቆፈሩት ጉድጋድ ይቀበራሉ፡፡ በታሪክ ማህደር እንደተዘከረው በታሪክ ላይ የዘመቱ ሁሉ መጨረሻቸው መጥፋት ነበር፡፡ በእርግጥም በዘመናት ሂደት ያለፉ፣ ታሪክ ላይ ያመጹ አገዛዞችና ነገስታት አነሳስና አወዳደቅ ለመረመረ ይህ ይገለጥለታል፡፡ ታዲያ የፈጣሪ የቅጣት በትር ፍጹም ፍትሃዊ እንደሆነው ሁሉ የታሪክ ቅጣትም ጊዜ ወይም ቦታ የማይቀይረው፣ ለማንም የማይወግን ፍጹም ፍትሃዊ ነው፡፡ ትናንትም ይሁን ዛሬ በታሪክ ላይ ያመጹ ሁሉ በጥፋታቸው ልክ ተቀጥተዋል፤ ነገም እንዲሁ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡
  3. የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት
    3.1 የታሪክ ክሽፈት ሲባል……
    እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ የታሪክ ክሽፈት ሲባል፡-
    “…… ምንም ያልተመዘገበ ነገር መኖሩ፤ ታሪኩ ከበላ-ጠጣ-ተነሳ- በላ-ጠጣ-ተኛ….. የማያልፍ ሲሆን ወይም በላ-ጠጣ-ተኛ-ተነሳ-ተራበ-ተጠማ ብቻ ሲሆን (ነው) “ገጽ 99
    ከዚህ ገለጻ እንደምንገነዘበው የታሪክ ክሽፈት ምንነት ሁለት ምሰሶዎች አሉት፡፡ አንደኛ የታሪክን ምንነት አለመገንዘብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የታሪክን አላማ አለመገንዘብ ነው፡፡ ምንም ያልተመዘገበ ነገር መኖሩ ከሚለው ሀረግ የምንረዳው የታሪክ ክሽፈት ፕሮፌሰሩ ትክክለኛ የታሪክ አረዳድ (ከላይ ለማሳየት እንደሞከርሁት ) ብለው ባስቀመጡት ልክ ሳይሆን ሲቀር ወይም የህዝብ የዘመናት የኑሮ ውጣ ውረድ ሳይመዘገብ ሲቀር ነው፡፡ ታሪኩ ከበላ-ጠጣ-ተነሳ- በላ-ጠጣ-ተኛ ወይም በላ-ጠጣ-ተኛ-ተነሳ-ተራበ-ተጠማ ብቻ ሲሆን የሚለው ሌላኛው የታሪክ ክሽፈት ምሰሶ የሚያመለክተው የታሪክ ዓላማን ከመሳት አንጻር ነው፤ ካለፈው ዘመን በጎና በጎ ያልሆኑ ተግባራት ትምህርት መቅሰም ሳይቻል ሲቀር ነው ፡፡
    3.2 የክሽፈት ታሪክ ሲባል….
    የክሽፈት ታሪክ ማለት በመጽሀፉ ገጽ 28 ላይ እንደተመለከተው በዘመናት ሂደት የህዝብ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ከመሻሻልና ከማደግ ይልቅ ቁልቁል ሲወርድ፤ የሃለኛው ትውልድ ከቀደመው ትውልድ በአንጻራዊነት የተሻለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ህዝቡ የመንፈሳዊና ቁሳዊ ብልጽግናው እየከዳው ሲሄድ የሚያመላክት ነው፡፡
    3.3 የክሽፈት ታሪክና የታሪክ ክሽፈት ቁርኝት…….
    በአዳፍኔ መጽሀፍ ተደጋግሞ እንደተነሳው በኢትዮጵያ ህዝብ የትውልድ ቅብብሎሽ ህዝቡ በመንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሀብቱ ከመሻሻል ይልቅ እየተዳከመ የመጣ ህዝብ ነው፡፡ ይህም የክሽፈት ታሪክ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የክሽፈት ታሪክ ምን ወለደው ለሚለው የፕሮፌሰሩ መልስ ይህ ነው፡-
    “….በዋናነት የመክሸፍ ምንጩ ሀለት ይመልሰለኛል፤ አንደኛው ትናንትን አለማስታወሰ ይመስለኛል፤ ሁለተኛው ነገን አለማሰብ፤ ትናንትን አለማስታወስ ማለት ታሪክን አለማወቅ (ነው) ….. ክብርና ኩራትን ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብና ሳንመዝን ለማይገባው (መስጠት ነው) ፤ በውጤቱም የሰራው እየተረሳና እየኮሰሰ፣ ያልሰራው እየተወሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፤……… ስለዚህም መስራት የማያስከብርና የማያከብር ይሆናል፡፡” ገጽ 73
    ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የታሪክ ክሽፈት ለክሽፈት ታሪክ ሰበብ መሆኑን ነው፡፡ እናም በታሪክ ክሽፈት ውስጥ የከሽፈት ታሪክን እናያለን ማለት ነው፡፡
  4. የታሪክ ክሽፈት ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር
    4.1 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ማሳያዎች …..
    ኢትዮጵያ የሶሰት ሺህ ዓመት ያላት አገር ናት፡፡ እንዲያውም በ2012 ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹The Hidden History of Ethiopia and Jews> በተሰኘው መጽሀፋቸው የኢትዮጵያ ታሪክ እስከ አራት ሺህ ዓመት ይደርሳል; ምን ይመስላል› ፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ ታሪክ የትናንታን ኢትዮጵያ በጊዜና በቦታ ርቀት የሚስቃኝ ነው ወይስ….. ታሪካችን በይዘቱ የህዝቡን የዘመናት የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ በተማላ ሁኔታ የሚዘግብ ነው ወይስ…..የኢትዮጵያ ታሪክ አገሪቱና ህዝቦቻ በዘመን ሂደት ያለፉበትን ከፍታና ዝቅታ ትክክለኛ ምስል ያሳየናል ወይስ……. ከታሪክ ማህደራችን የትውልዶችን ሽግግር ማየት እንችላለን ወይስ……..፣ የታሪክ ትርክቱ ተዓማኒነት እስከምን ድረስ ነው….. የሚሉትን ጉዳዮች መመርመሩ የኢትዮጵያን የታሪክ የክሽፈት መንገድ የሚጠቁመን ይሆናል፡፡
    ከአደፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ታሪክ በጊዜና ቦታ ርቀት፣ በይዘት ጥልቀት እንዲሁም በተዓማኒነት ሚዛን ሲለካ ብዙ ጎዶሎዎች ያሉት መሆኑ የክሽፈቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ከመጽሀፉ በመጠቃቀስ ለማሳየት ልሞክር፡
    ሀ) ከጊዜና ቦታ ርቀት አንጻር የኢትዮጵያ ታሪክ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ምስል በአግባቡ አያሳይም፡-
    “የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው ከመሃሉ ወይም ከአሁኑ ነው፡፡” ገጽ 97
    ለ) ከይዘት ጥልቀት ሚዛን አካያ ከፈተሸነው ታሪካችን ጎዶሎ ነው፡፡ የነገስታትና የጦርነት ጉዳዮችን እንጂ የህዝቡን ዘርፈ ብዙ የኑሮ ውጣ ውረድ ከታሪክ ድርሳናት አናገኝም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ይህንን ሲገልጹ፡-
    “….ኢትዮጵያዊያን ብዙ የምንኮራበት ታሪክ አለን፡፡ ዞሮ ዞሮ የኩራታችንና የክብራችን ታሪክ አገራችንን ከውጭ ወራሪዎች ተከላክለን ከማቆየታችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በትምህርትና በምርምር፣ በስነጽሁፍና በስነትበብ፣ በዕውቀትና በፍልስፍና ኑሮነ ለማሻሻል በሚያስፈልጉ ዘዴዎች ፣ በመመላለሸና በመገናኛ ዘፈዴዎች፣ በምህንድስና በእጅቨ ስራ……ወዘተ ምንም ዓይነት እድገትና መሻሻል አለማሳታችን ታሪካችን አያወሳም፡፡ “ገጽ 28
    ሐ) የተመዘገበው ታሪካችን ጥሩ ጥሩውን ብቻ እንጂ ድክመቶታችንን የሚያሳየን አይደለም (ገጽ 28)፡፡
  5. ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ ማነው?
    5.1 አዳፍኔና የታሪክ ከሽፈት……..
    ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ ናቸው የሚላቸው ሶስት አካላት በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞች(መሪዎቸ)፣ ህዝቡ እንዲሁም የታሪክ ጸሀፊያን (ምሁራን)ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጀርባ ሆኖ የታሪክ ክሽፈቱን የሚያፋጥነው ደግሞ አዳፍኔ ነው፡፡ ለታሪክ ክሽፈት ተባባሪ የሆኑት ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካላት እንዴት ለታሪከ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ አደረጉ የሚለውን ከመቃኘታችን በፊት የአዳፍኔን ምንነትና ባህሪያት ማወቁ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ አዳፍኔ ማነው?
    5.1.1 አዳፍኔ ማነው?
    በመላው ዓለም በተለይም በአፍሪካ መሰረቱ ሰፊ እንደሆነ የሚነገርለት አዳፍኔ ትውልዱ የትና መቼ እንደሆነ እርግጡን መናገር ባይቻልም ወደ ኢትዮጵያ ምድር የገባው በ1928 ዓ.ም ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡ አዳፍኔ በአካሉ ከአንድ ሰው ጉልበት የማያልፍ ትንሽ ነገር ነው(ገጽ 245)፡፡ አዳፍኔ መካካል ይወዳል፤ ከአንገቱ ላይ አብለጭላጭ ጌጥ ጠፍቶ አያውቅም፤ ይህ የአንገት ሀብል የተዋቀረው በቅርጻቸውና በመልካቸው ጉራማይሌ ከሆኑ ቀለበቶች ነው፡፡ እነዚህ የሀብሉ ቅንጣቶች የየራሳቸው መጠሪያ አላቸው፤ ተራ ጸሀፊ፣ ተራ ወታደር፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ህግ፣ ዳኛ፣ የምክር ቤት አባል፣ አስተዳዳሪ፣ የቀበሌ ሰራተኛና አስተዳደር፣ ወዘተ….. ይሰኛሉ፡፡
    አዳፍኔ እጅግ የሚወዳቸው ሁለት ልጆች አሉት፡፡ የበኩር ልጁ ፍርሃት ይባላል፤ ተከታዩ ደግሞ መክሸፍ የሚል መጠሪያ አለው፡፡ ፍርሃትና መክሸፍ ለአዳፍኔ ሁለመናው ናቸው፤ ቆሞ የሚሄደው፣ የሚተነፍሰው በእነርሱ ነው፤ ያለነሱ አዳፍኔ ምንም ማለት ነውና አብዝቶ ይንከባከባቸዋል፡፡ በእርግጥ አንገቱ ላይ ያንጠለጠለው ሀብል ሊያጌጥበት አይደለም፤ የልጆቹ ዘብ እንጂ፡፡ እናም አዳፍኔና የሰንሰለቱ ቀለበቶች ታዲያ ውል አላቸው፡፡ ውላቸው ግን ለአዳፍኔ የወገነ ነው፤ የጌታና የሎሌ፡፡ በውላቸው መሰረት ቀለበቶቹ ልጆቹን (ፍርሃትና መክሸፍን) ይንከባከባሉ፤ ለአገልግሎታቸውም ከአዳፍኔ ምንዳ ይቆረጥላቸዋል፡፡ አዳፍኔ በህይወቱ አብዝቶ የሚፈራው ነገር ቢኖር እውነትን ነው፡፡ እውነት የልጆቹ ዋነኛ ጠላት ነው፤ እናም የዕውነት ምንጮች የሆኑት እምነትና እውቀት የዘወትር ስጋቱ ናቸው፡፡ እውነትን ለማጥቃትም የእምነት(ሀይማኖት) እና የትምህርት ተቃማትን ከቻለ ደልሎ ወደራሱ ለማስገባት ካልቻለ ደግሞ በሀይል ለማስገበር ዘወትር ይተጋል፡፡ ለዚህም ጭፍሮቹ ከእርሱ ፍላጎት በተቃራኒ እንዳይሄዱና ከእውነት እንዲጠብቁት ታማኝነታቸውን ለማግኘት ሁለት ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ አንደኛው በጥቅም መደለልና ህልውናቸው በእርሱ መኖር ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ አምነው እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ሌላኛው ዘዴው ደግሞ ወደ እውነትን መንገድ የሚወስደውን መንንድ መዝጋት ነው፤ ለዚህም ጭፍሮቹ እንዳይነቁና እንዳይሰለጥኑ ሌት ተቀን ነቅቶ ይጠብቃል፡፡ ጭፍረቹ አብዝቶ ከሚፈራው እውነት ሊጠብቁት ካልቻሉ አዳፍኔ ለክፉ ቀን መከታ ይሆኑኛል በሚል የሚቀልባቸው ሁለት አካላት አሉ፡፡ እነዚህም የመከላከያና የደህንነት ሀይሎች ይባላሉ፡፡ የአዳፍኔ አይን በመሆናቸውም ሁልጊዜ እንክብካቤው አይለያቸውም፡፡
    እንግዲህ ከላይ በስሱም ቢሆን የተዋወቅነው አዳፍኔ ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ሚናው የላቀ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ተባባሪ የሆኑትና ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካላት የአዳፍኔ ውጤቶች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፈን እንደሚሞግቱት አዳፍኔ በታሪክ ክሽፈታችን ውስጥ ራሱን የሚገልጥበት ዋናው መንገድ ታሪካችን በጎ በጎውን ብቻ ነጋሪ፤ የትናንት ውጣ ውረዳችንን የሚያዳፍን መሆኑ ነው፡፡
    “…….. (ታሪካችን) አለማደጋችንና አለመሻሻላችን ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ጉድለታችንን ታሪካችን አለመዘገቡ የሚያሳፍር ታሪካችን ነው፤ ……….. በኢትዮጵያ ታሪክ መክሸፍ በብዙ ምዕተ ዓመታት ግዙፍ ቦታ የያዘ መስለኛል፡፡ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የማውቀው አንድም ጥናት የለም፡፡” “ገጽ 28 እና ገጽ 50
    5.1.2 የኢትዮጵያ ታሪክና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞች (መሪዎቸ)
    ፕሮፌሰር መስፍን በ‹አዳፍኔ› መጽሀፋቸው ደጋግመው እንዳነሰት ለኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ በረጅም ዘመን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ አገዛዞችና አገዛዙ ያበቀላቸው ገዢዎች ናቸው፡፡ መገለጫውም ታሪክን ለመበረዝ፣ ለመፈብረክና ለማማፋት ያደረጋቸው የጥፋት ዘመቻዎች ናቸው፡፡ ታዲያ አገዛዙ ለታሪክ ክሽፈቱ ተጠያቂ የሚሆንባቸው አግባቦች ምንድናቸው? ለሚለው መሰረታዊ ጉዳይ መጽሀፉ ሶስት ጉዳዮችን ያነሳል፡፡ እነዚህም፡-
    • ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል
    • ህዝቡ ለታሪክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ
    • የታሪክ መረጃዎችን፣ ምልክቶችን፣ በመደበቅ፤ የታሪክ ጥናትና ምርምርን በማሳነስ
    5.1.2.1 ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል……..
    የኢትዮጵያን የታሪክ ክሽፈት በመሰረታዊነት የሚገልጸውም የአገዛዙና የታሪክ ዓላማ ልዩነት ነው፤ አገዛዙንና ታሪክን ከቃኘን ዓላማቸው ለየቅል ነው፡፡ የታሪክ ዓላማ የአገርና የህዝብ ኣላማ ነው፤ የታሪክ ዓላማ የእውነት ዓላማ ነው፡፡ የአገዛዙ ዓላማ ደግሞ ግለሰባዊ ነው፤ ፖለቲካዊ ነው፡፡ የታሪክ ምንነት እንዲሁም ዓላማ የሚወሰነው አገዘዛዙና መሪዎቹ የህዝብ ተቀባይነት ለማግኘትና ስልጣናቸውን ለማራዘም እንዲጠቅማቸው በሚያስችላቸው መልኩ ነው፤ በሌላ አገላለጽ ታሪክን ለፖለቲካዊ ፍጆታ ያውላሉ፡፡ ትክክለኛው የታሪክ ትርክት ከአገዛዙ ኣላማ የሚጋጭ ከሆነ ለእነርሱ በሚስማማ መልኩ ታሪኩን ይበርዛሉ፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ አዲስ ታረክን ይፈበርካሉ፤ ካልሆነም ታሪክን ያጠፋሉ፡፡
    “………ቀደም ያለው (አገዛዝ) የሰራውን በሃላ መታው ያፈርሰዋል ወይም ይደብቀዋል፤ ታሪክን የአገርና የህዝብ አድርጎ በመመልከት ፋንታ የግል በማድረግ ታሪክ ያለባህሪው እንዲያትርና በሰው እድሜ እንዲለካ ያደርጋል፤ ታሪክ የሚከሽፍበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡” ገጽ 133
    5.1.2.2 ህዝቡ ለታሪክ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዳብር በማድረግ
    ሁለተኛው የአገዛዙ ሀጢአት ደግሞ ህዝቡ ለታሪክ ትክክለኛ ምንነት፣ እንዲሁም ዓላማ ያለው ግንዛቤ የተዛባ እንዲሆን ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያውን ማስፈጸሚያ መሳሪያ ለማድረግ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ለታሪክ ምንነት፣ ዓላማና ግምት የተሳሳተ ከሆነ አገዛዙ እንዳሻው ወይም ሲፈልግ ታሪክን ሊበርዝ፣ ሊፈበርክ፣አልያም ሊያጠፋ ይቻለዋል፡፡
    በረጅም ዘመን የኢትዮጵ ታሪክ አገዛዙና ሀይማኖት፣ በተለይም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በህዝቡ ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ የነበራት ሚና የላቀ ነበር፡፡ ከታሪክ ክሽፈት አካያም የሁለቱም አስተዋጽኦ ተደጋጋፊ ነው፡፡
    “………አገዛዙና ሀይማኖት የሰውን ልጅ ተቃርጠው፣ ለሁለት ገንጥለው ሥጋውን ለአገዛዙ ነፍሱን ደግሞ ለሀይማኖት አድርገው ተካፍለዋል፤ አንዱ ሥጋውን የበደለ ለነፍሱ ሲል፣ ሌላው ከሰው መርጦ ለሹመት እያለ የመሳፍንትና መካንንት አደግዳጊዎችን ያጠናክራል፡፡” ገጽ 64
    አላማው ህዝቡ የተሳሳተ የታሪክ አረዳድ እንዲኖረው ማድረግ ሲሆን፤ መሳሪያው ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ ነበር፡፡ በመጽሀፉ እንደተገለጸውም፡-
    “…………ከአጤ ምኒልክ ዘመን በፊት በኢትዮጵያ ት/ቤት በመባል ሚታወቀው በክርስቲያንና እስላም ካህናት የሚካሄደው ነበር………….የባህላዊው ትምህርት ዓላማውና ስርዓቱም ከቤተ ሀይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ……. (ዓላማውም)ሰዎችን ወደ እግዚአብሄር እንዲቀርቡ ለማድረግ ሲሆን አቀራረቡም ከጸሎት ወይም ከልመና የማያልፍ ነው፤ ይህም ማለት በበጎ ተግባር ላይ ሳይሆን፣ ወይም ለግል ኑሮ እያንዳንዱ ሰው ያለበትን ሃላፊነት በማስታወስ ሳይሆን መለመንን እንደችግር መፍቻ በማድረግ ነው፡፡” ገጽ 63፣ ገጽ 65
    ባህላዊው የትምህርት ስርዓት ህዝቡ ኑሮው በአምላክ ፍቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ፣ በትናንት ድሉም ሆነ ተግዳሮቶቹ ሚናው ዜሮ እንደሆነ ይሰብካል ፡፡ ይህ በመሆኑም ህዝቡ ታሪክን የሚረዳው “……በእግዚአብሄር ፍቅርና ጥላቻ መስመር (ነው)” (ገጽ 181)፤ ስለሆነም የትናንቱን ከፍታም ሆነ ዝቅታ ማስታወስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው የታሪክ አረዳድ ትክክለኛውን የታሪክ ምንነትና ዓላማ የሚሽር ነው፡፡
    5.1.2.3 የታሪክ መረጃዎችንና ምልክቶች በመደበቅ፣ ጭራሹኑ እንዲጠፋ ለማድረግ በመሞከር
    ያለፉት ዘመናት በጎ ስራዎች እንዳይመዘገቡ፣ ጭራሱንም እንዳይታወቁ ለማድረግ መሞከር ሌላኛው አገዛዙ በታሪክ ላይ ያደረሰው ጥፋት ነው፡፡ ይህን ለማሳየት በመጽሀፉ የተጠቀሰው ዋናው አስረጅ ከ1933 ዓ.ም በሃላ የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነው፡፡ በቅርቡ ታሪካችን ታላቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የአርበኞች ታሪክ ተደብቆ አንዲቀር የተደረገውም በአጼ ሀይለስላሴ መሰሪነት እንደሆነ ተጠቁማል፡፡ ከፋሺስት ቅኝ አገዛዝ አገራቸውንና ህዝባቸውን ነጻ ለማውጣት በዱር በገደሉ የተዋጉ፣ የተጋደሉ አርበኞች የአገዛዙ ኢላማ ሆነው፣ በክፉ ቀን ለባንዲራቸው ያደረጉት ተጋድሎ ተረስቶ የውርደት ካባ እንዲለብሱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይባስ ብሎም ለስደትና ለሞት የተዳረጉ ታላላቅ አርበኞች ነበሩ ( ገጽ 124-125፣ ገጽ 142፣ ገጽ 157 )፡፡
    5.1.3 የኢትዮጵያ ህዝብና የታሪክ ክሽፈት
    የኢትዮጵያ ህዝብ ለታሪክ ክሽፈት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ሁለት ምክንያቶች ያላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ህዝቡ ለታሪክ የሰጠው ቦታ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ስለታሪክ ምንነትና ዓላማ ከሰጠው የተሳሳተ ትርጋሜ የመነጨ ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኮነንበት አግባብ ደግሞ ታሪኩን ጽፎ ለትውልድ እንዲተው እንዲያስችለው ዋነኛ መሳሪያ የሆነው የፊደል (ጽሁፍ) ጥበብ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረ ቢሆንም ህዝቡ ግን ይህን ታላቅ አጋጣሚ አልተጠቀመበትም
    እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ ታሪክ ለኢትዮጵያዊያን በእግዚአብሄር ፍቅርና ጥላቻ መስመር ነው (ገጽ 181 )
    ይህ የታሪክ አረዳድ የሚያሳየው ያለፈው ዘመን ተግባራት ሁሉ የተከናወኑት በሰው ፍቃድ ሳሆን በፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ስለሆነም የዛሬው የሰው ልጅ ተግባራት የነገ ታሪኩ እንደሆነ አልተረዳውም፡፡ ይህ የታሪክ የተሳሳተ የታሪክ ምንነት ግንዛቤ ታሪክን መሰረታዊ አላማና አስፈላጊነትን ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ በውጤቱም፡-
     ህዝቡ ለታሪክ ትምህርትና ዕውቀት አስፈላጊነት ዝቅተኛ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የዛሬን ሁነቶች መዝግቦ ለነገው ትውልድ የማየቆት ልማድ አያዳብርም
     በዚህም ህዝቡ ለታሪክ መረጃዎችና መዛግብት ዝቅተኛ ግምት ይሰጣል፤ በመሆኑም የታሪክ መረጃዎች ተጠብቀው እንዳይዳብሩ ተጠብቀው እንዲቆዩ የህዝቡ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ይሆናል፡፡
    5.1.4 የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፊያንና የኢትዮጵያ ታሪክ
    ዛሬ ላይ የምናገኘው የኢትዮጵያ ታሪክ ማህደር በአገር ውስጥ (ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው) እና በውጭ አገር የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት የተደራጀ ነው፡፡ የታሪክ ጸሀፍቱ ታሪክን ሲጽፉ ታዲያ ለኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ዕድገት በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ታሪክ ዕድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ማወደስ ያስፈልጋል፡፡ በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍም ይህ ተጠቅሳል፤ ይህ ሲባል ግን ጸሀፍቱ ሁሉ ታሪክን ለመጻፍ ሲሞክሩ የኢትዮጵያን ታሪክ እና ስነ-ጽሁፍ እንዲዳብር ቀናኢነት ነበራቸው ብሎ መውሰድ ተሳሳተ ነው፡፡
    በእርግጥም የታሪክ ጸሀፍት እንዴት ለታሪክ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ፕሮፌሰሩ የሰጡትን ትንታኔ ለመረዳት በኢትዮጵያን ታሪክ ዙሪያ የጻፉ ምሁራንን (ጸሀፍትን) ማንነት መመርመር ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ጸሀፍቱ ታሪክን ለመጻፍ ሲነሱ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ወይስ……..? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡
    ከዚህ አንጻር በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍ እንደተጠቆመው ጸሀፍቱ ኢትዮጵያዊያን ወይስ የውጭ ዜጎች‹፤ በሁለቱም ጎራ ያሉ ጸሀፍትን የድሮ ወይስ የአሁን ብሎ መከፋሉ በስራዎቻቸው ሚዛናዊነት፣ ተዓማኒነት፣ ጥራት ወዘተ……. ላይ የራሱ እንድምታ አለው፡፡
    5.1.4.1 የውጭ ጸሀፍትን በተመለከተ
    የድሮ የውጭ ጸሀፍት ሲባል……
    የድሮ የታሪክ ጸሀፍትን ማንነት በመጽሀፉ በገልጽ ማግኘት አልቻልሁም፡፡ ሁለት ነገሮችን ማወቅ መልሱን ለማግኘት ቁልፍ ነው፡፡ አንደኛው የጸሀፍቱ ማንነትና ስራዎች ሲሆን ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ የተጀመረው መቼ ነው፣ በዘመኑ የነበሩ ጸሀፍት ማንነትና ታሪክን ከመጻፍ አካያ የነበራቸው መለያ ባህሪያትስ የሚለው ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሀፋቸው እንዳሰፈሩት የድሮዎቹ የውጭ ጸሀፍት መለያ ያሉት ግዕዝን የተማሩ፣ ከኢትዮጵዊያን ጋር ቀርበው ለማወቅ የቻሉ፣ የኢትዮጵያዊያዊያንን ቃንቃና ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ የሚል ነው፡፡ይህ ቢያንስ ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ፍንጭ ሰጥቶኛል፡፡ ለሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ ግን መጽሀፉ ያለው ነገር የለም፡፡ እናም ፐሮፌሰሩ የድሮ ጸሀፍት ሲሉ እነማንን ነው› ለሚለው መልስ ለማግኘት መረጃ ማፈላለግ ነበረብኝ፡፡ ካገላበጥካቸው ስራዎች ውስጥ ግን ታዬ አሰፋ እና ሽፈራው በቀለ የተባሉ ምሁራን በጋራ ያሳተሙትን The Study of Amharic Literature: An Overview የሚለው ጥናት አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
    “……..ከ1870ዎቹ ጀምሮ በአማርኛ ስነ ጽሁፍ ላይ በርካታ ለውጦች መታየት ጀመረ ፡፡ ይህንንንም ከሶስት አቅጣጫዎች ማየት የቻላል፡፡ የመጀመሪያው በርካታ የውጭ ጸሀፍት በኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ላይ ጥናት ለማድረግ የተነሳሱበትና ተሳትፎ ማድረግ የቻሉበት መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ኢጣሊያዊው ኮንቲ ሮሲኒ፣ ጀርመናዊው አውግስቶ ዲልማን፣ ፈረንሳዊው ዞተንበርግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሁለተኛ ይህ የዘመን ማዕቀፍ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ጥራት ያላቸው የስነ ጽሁፍ ስራዎች መታየት የጀመሩበት ነበር፡፡ በሶስተኛ ደረጃ በቀደመው የኢትዮጵ የስነ-ጽሁፍ ክምችት ውስጥ እምብዛም ያልነበሩት ታሪካዊና ፊሎሎጂካዊ ( ) ዘውግ ያላቸው መጻህፍት በስፋት ተጽፈዋል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ የትምህርት ተቃማት በተለይም በጀርመንና ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ጥናት ማዕከላት ተቃቁመዋል፡፡ ጸሀፍቱም የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ እንደመረጃ የሚጠቅማቸው ድርሳናት በግዕዝ ቃንቃ የተጻፉ ስለነበሩ ቃንቃውን ማወቅ ነበረባቸው፡፡ በዘመኑ የአውሮፓ ታላላቅ የትምህርት ተቃማት ግዕዝ ቃንቃ በስፋት መሰጠት ተጀምሮ ነበር፡፡” (ገጽ 28)
    በፕሮፌሰር መስፍን እይታ መሰረት በዋናነት የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ዘመቻ ተጀመረው በፋሺስት ወረራ ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ዓላማዋን ለማሳካት እንዲያግዛት የኢትዮጵያን ታሪክ መበረዝ እንደ ዋነኛ መሳሪያ ተጠቅማለች፡፡
    ከላይ ከተመለከተው እንደምንረዳው ከዘመን አካያ ስናየው ፕሮፌሰር መስፍን የድሮዎቹ የውጭ ጸሀፍት የሚላቸው ከ1870ዎቹ እስከ 1920ዎቹ የተነሱትን ነው፤ ዓላማቸውም ዕውቀትን ለማስፋፋት ነበር፡፡
    የኃለኞቹ የውጭ የታረክ ጸሀፍት ሲሉ……..
    ፕሮፌሰር መስፍን የሃለኞቹ የታሪክ ጸሀፊያን የሚላቸው ከ920ዎቹ ጀምሮ የተነሱትን ነው፡፡ በተለይም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ታሪክን እንደዋነኛ መሳሪያ ተጠቅማለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በአድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል መንሳታቸው ለመላው ነጮች ሽንፈት ነው ብለው የሚያምኑ አውሮፓዊያን ጸሀፍት የኢትዮጵያን ታሪክ በመበረዝና፣ አዳዲስ የታሪክ ትርክቶችን በመፈብረክ ለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ተግተዋል፡፡
    የኃለኞቹ የታሪክ ጸሀፊያን ዓላማቸው ታሪክን በሚዛናዊነት መጻፍ፣ ዕውቀትን ለማስፋፋት አይደለም፤ ይልቁንም ቁሳዊ ፍላጎታቸው ለማማላት፣ ታሪክን እንዲጽፉ በገንዘብ የሚረዳቸውን ተቃም ለማስደሰት፣ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ነው፡፡
    የውጭ አገር የታሪክ ምሁራንና የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት
    በአዳፍኔ ፍርሃትና መክሸፍ መጽሀፍ እንደተመለከተው ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በማስተማርም ሆነ በጥናት እና ምርምር ዋነኛ ተዋናዮች የነበሩት የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡ የውጭ ዜጎች ታሪካችንን መጻፋቸው ክፋት ባይኖረውም (ገጽ 212) በስራዎቻቸው ግን ትክክለኛና የተማላ ታሪክ አንዳናገኝ የሚያደርጉ ቢያንስ ሁለት ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህንንም ፕሮፌሰር መስፍን የገለጹት እንዲህ ነው፡-
    “………ከአንድ አገር ሰዎች ከራሳቸው የሚፈልቅ መረጃ ወይንም ዕውቀት ከዚያ አገር ህዝብ በራቀ መጠን ጉልበቱ ይቀንሳል፤ የአገሩ ሰዎች መረጃውን በመተርጎሙና በማጠናቀሩ በኩል የተሻሉ በመሆኑ (ነው)፡፡ ……….. (የውጭ የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት) የጎሳ ስሜትን በመቀስቀስ…ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሆነዋል፡፡” (ገጽ 212፣ ገጽ 214)
    ከታሪክ ክሽፈቱ አንጻር የድሮዎቹና የአሁኖቹ የውጭ ጸሀፍት ስራዎች አደገኛነት ይለያያል፡፡ በዚህም የድሮዎቹ ስራዎች ከአሁኖቹ የተሻለ ተ”ዓማኒነት አላቸው፡፡ ለዚህ ምክንያት ተብሎ በመጽሀፉ የተጠቀሰው የሚከተለው ነው፡-
    “………..የዱሮዎቹ ግዕዝ ሳይቀር እየተማሩ በግእዝ የተጻፉትን ሁሉ በየቃንቃቸው ይተረጉሙ ነበር፤ እነዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ ያጠኑ የነበረው የየሀገራቸውን ምሁራን ዕውቀት ለማበልጸግ ነበር፤ የሃለኞቹ ምንደኞች ናቸው፡፡” ገጽ 213
    5.1.4.2. ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት
    ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍትን የድሮዎቹና የአሁኖቹ ሲሉ በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ለዚህም መሰረት ያደረጋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ጸሀፍቱ ያለፉበት የትምህርት ስርኣት ሲሆን ሌላው ደግሞ የጸሀፍቱ ግለሰባዊ(ቤተሰባዊ) ማንነት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የጸሀፍቱን ስራዎች ተዓማኒነት የሚወስኑ ናቸው፡፡
    የድሮዎቹ ጸሀፍት
    ከጸሀፍቱ ማንነት አንጻር በተነጻጻሪነት የድሮዎቹ ጸሀፍት ከጥቅመኝነት የራቁ፣ ዓላማቸውም ዕውቀትን መመርመር ነበር፡፡ እነዚህ የታሪክ ጸሀፍት በአብዛኛው በባህላዊው የትምህርት ስርዓት ያለፉ ናቸው፡፡ በዚህም ከተበላሸው የዘመናዊው ትምህርት ስርዓት የጸዱ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ ለመጻፍ ችለዋል፡፡ በተስተካከለ የታሪክ ትምህርትና ጥናት ያለፉ የሚላቸውን ምሁራን ለመጥቀስ ሞክረዋል፡፡እውነተኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለማወቅ የፈለገ ሁሉ የፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ እና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ስራዎች ሊያነብ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ (ገጽ98)
    የአሁኖቹ ጸሀፍት
    የሃለኞቹ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ታሪክን በአግባቡ እንዳይጽፉ ያደረጉ ምክንያቶች ሁለት እንደሆኑ ፕሮፌሰሩ ይሞግታሉ፡፡ አንደኛው የታሪክ ጸሀፍቱ ያለፉበት መንገድ የተበላሸ መሆኑ ነው፡፡ሁለተኛው ደግሞ አብዛናው ጸሀፍት የባንዶች ልጆች መሆናቸው ነው፡፡
    ያለፉበት የትምህርት ስርዓት የተበላሸ መሆኑ
    ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚገልጹት አብዛኛው የዛሬው ጸሀፍት ታሪካቸውን ሳይቀር የተማሩት በውጭ ምሁራን ነው፡፡
    “…..የእኔ ትውልድ ከውጭ አገር ሰዎች ተማረው የኢትዮፕያ ህዝብ ከነባህሉ የአረብ ተወላጅ ተደርጎ ነው፤ የእኛ ነው የምንለው ነገር ሁሉ ከአረብ ያገኘነው መሆኑን እየነገሩን እኛም በተራችን ያንኑ ለተከታዩ ትውልድ ስናስተላልፍ ቆየን፤ የሴም ቃንቃ፣ ነገረ መንግስት፣ እረሻ፣ ጽህፈት፣ ወዘተ…..ሁለም ነገር ከባህር ማዶ ያገኘነው እየተደረገ ተማርን፤ እኛም በበኩላችን አስተማርን፡፡” ገጽ 116
    በዚህ አይነት የትምህርት ስርኣት ያለፉ የታሪክ ጸሀፍት የአገራቸውን የሚንቁ፣ በአንጻሩ ነጭ አምላኪ ሆነዋል፡፡ የዛሬዎቹ ጸሀፍት ከአገራቸው ታሪክ መረጃዎችና ምንጮች ይልቅ በውጭ ምንጮች ላይ ማተኮራቸው፣ የአገር ውስጥ የታሪክ ምንጮችን እንደማስረጃ አድርጎ ለመውሰድ አለመፈለግ የዚህ ነጸብራቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ እንዲያውም ‹ተረት› የሚላቸውን እንደክብረ ነገስት፣ ፍትሃ ነገስት ያሉትን እንደታሪከ ምንጮች አድርጎ መውሰድ ባይቻል እንካ ቢያንስ ለመመርመር ሲሞክሩ አይታይም (ገጽ 231)፡፡
    የጸሀፍቱ ግለሰባዊ ማንነት
    አብዛኞቹ የዛሬ ጸሀፍት የባንዶች ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ጸሀፍት የወላጆቻቸውን የባንዳነት ሃጢኣት ንስሃ ገብተው ለመንጻት ከመሞከር ይልቅ ሃጢያታቸውን ለመሸፋፈን ታሪክን በመበረዝ ለመሸሽ ሞክረዋል፡፡
    “…………….በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን ታሪክ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው እንደሚመች እያደረጉ በመተርጎም የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ታሪክ ያበላሻሉ፤ እያበላሹም ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮፕያን ታሪክ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተለየ ባለመሆነኑ ከመቶ ዓመታት አይበልጥም የሚባለው የባንዶች ልጆች የፈጠሩት የሻዕቢያና የወያኔ ተረት ነው፤ ባንዳዎች ያልነበሩ የኤርትራና የትግራይ ሰዎች ይህንን የፈጠራ ታሪክ አይቀበሉትም፤ ምክንያቱም የብዙዎቹ አባቶች በኢትዮፕዊነታቸው ኮርተው በአርበኝነት የሞቱ ወይም የተጎዱ ይሆናሉ፡፡” (ገጽ ——)
    ፕሮፌሰሩ ሁሉንም የታሪክ ጸሀፍት በጅምላ አልወቀሱም፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ህጸጾች የጸዱ ናቸው፣ በዚህም የኢትጵያን ታሪክ ለማወቅ የፈለገ ሁሉ ስራዎቻቸውን ሊያነብ ይገባል ያላቸውን እንደ ፕሮፌሰር አለም እሸቴ፣ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የመሳሰሉ ምሁራንን አወድሰዋል (ገጽ 98) ፡፡
    ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ምሁራንና የታሪክ ክሽፈት
    ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ምሁራንና ጸሀፍት በሶስት መልኩ ለታሪክ ክሽፈቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እነዚህም ለታሪክ ያላቸው የተዛባ ግንዛቤ፣ ታሪክን በሚዛናዊነት አለመጻፍ እና ታሪክን ሲጽፉ ለአገር ውስጥ የታሪክ ድርሳናትና የታሪክ ምንጮች አነስተኛ ግምት መስጠታቸው ነው፡፡
    የተዛባ የታሪክ ግንዛቤአቸው
    እንደፕሮፌሰር መስፍነ እምነት አብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት ታሪክ “ለአንድም ሰኮንድ የማቃርጥ የሰው ልጆች የአናናር ጅረት መሆኑን አልተረዱትም (ገጽ 98)፡፡ ከዚያ ይልቅ ታሪክን እንደ ተረት…መነሻ የሌለው፣ አቅጣጫ የሌለውና ዓላማ የሌለው አድረገው በጊዜ በታጠረ ብቅ ጥልቅ ውስት የሚነገር ተረት አድርገውታል……..(ታሪክን) በሁለት እግሩ ብቻውን ቆሞ የሚሄድ ነፍስ ያለው ነገር አድርገው ይወስዱታል”፡፡ (ገጽ 50፣ ገጽ 98)
    የታሪክ ጸሀፍት በሚዛናዊነት ታሪክን አለመጻፍ
    ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ጸሀፍት በብዙ መልኩ በገለልተኝነት ታሪክን ለመጻፍ አልቻሉም፡፡
    “………(ጸሀፊያኑ) ለስልጣን በማጎብደድና ለጥቅም በመገዛት ሁነትን ሁሉ በአገዛዙ መነጽር ብቻ እያዩ ያንኑ ስህተት ለተከታታይ ትውልዶች እያስተላለፉ ስህተቶቹ እንዳይታረሙ ያደርጋሉ፡፡” ገጽ 30
    የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፍትና የታሪክ የመረጃ ምንጮች ከታሪክ ክሽፈት አንጻር
    ታሪክ በተማላና በትክክለኛ ሁኔታ እንዲጻፍ የታሪክ የመረጃ ምንጮች ተዓማኒነት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የታሪክ ታሪክን ለመጻፍ ሲነሱ እንደዋና ግብኣታቸው አድርገው የሚጠቀሙት የውጭ ጸሀፍት ስራዎችን ወይም ውጭ ምንጮችን ነው፡፡ አገር በቀል የሆኑ የታሪክ ድርሳናትን የማሳነስ ሁኔታ በጸሀፍቱ ይታያል (ገጽ 212፣ 232)፡፡ ጸሀፊያኑ ለዚህ የሚያቀርባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የአገር ውስጥ የታሪክ ድርሳናት ማገኘት አስቸጋሪ ነው የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ ነባር የኢትዮጵያ የታሪክ ጸሀፍትና ስረዎች የሚዛናዊነት ጉድለት ይታባቸዋል የሚለው ነው፤ ሚዛናቸውን የሚያጋድለው ዋናው ነገር ደግሞ ጸሀፍቱ ለሚወክሉት ብሄር አድልተው መጻፋቸው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
    ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚከራከሩት ኢትዮጵዊያን የታሪክ ጸሀፍት ወደ ውጭ ምንጮች እንዲዞሩ በምክንያትነት የሚያቀርባቸው ሁለቱ ምክንያቶች መሰረተ ቢስ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ መረጃዎች አነስተኛ መሆን ለሚለው ያሉትን መቼ ለመመርመር ሞከርን; ፍላጎቱም የለንም ሲሉ መልሰዋል፡፡ ወደ ውጭ ምንጭ ማማተሩ እንደምክንያት ለሚነሳው ሁለተኛው ጉዳይ የሰጡት ምላሽ ደግሞ የኢትዮጵያ ጸሀፍት ስራ ሚዛን ያጋደለው ጸሀፍቱ ከጥቅመኝነት፣ ጥገኘነትና ከፍርሃናትና ስጋት ነጻ አለመውጣታቸው እንጂ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሀፍት የዘር ሀረጋቸው ለሚመዘዘበት ጎሳ አድልተው ይጽፋሉ የሚለው ጉዳይ አሳማኝ እንዳልሆነ ፍንጭ ይሰጣሉ (ገጽ 232)፡፡
    በቂ የአገር ውስጥ ታሪካዊ መረጃዎች ከሌሉ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የውጭ የታሪክ ጸሀፍት ስራዎችን እንደመረጃ ወስዶ ታሪክ መጻፉ ጉዳት የለውም ፡፡ ጸሀፍቱ ወደ ውጭ መረጃዎች ፊታቸውን ሲያዞሩ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ስላለባቸው ጉዳዮች ጽፈዋል፡፡
    አንደኛ የጸሀፍቱን ማንነት ከመመርመር አንጻር ነው፡፡ በድሮዎቹና በአሁኖቹ የውጭ አገራት የታሪክ ምሁራን መካከል ልዩነት አለ፤ የድሮዎቹ የሚጽፉት ዕውቀትን ለማበልጸግ ሲሆን የአሁኖቹ ግን ምንደኞች ናቸው፡፡ ስለሆነም የድሮዎቹን ጸሀፍት ስራዎች እንደማጣቀሻ መውሰዱ የተሸለ ነው፡፡ ሁለተኛ የውጭ ጸሀፍት ታሪክን ሲጽፉ ዓላማ አድርገው የሚነሱት እውነተኛ ታሪክን ለመጻፍ ነው ወይስ የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ አላቸው ብሎ መጠራጠር ያሻቸዋል፡፡ይህን ሳይመረምሩ እንደወረደ ስራዎቹን አምኖ ተቀብሎ እንደማጣቀሻ መውሰድ አደገኛ ነው (ገጽ 213)፡፡
    ሶስተኛ የውጭ ስራዎች እንደምንጭ መውሰድ የመረጃው ጥራት(ተዓማኒነት) ያሳንሳል፡፡ ይህም የሚጻፈው ታሪክ ተዓማኒነት የጎደለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ይህን ሲያብራሩም፡-
    “……….ከአንድ አገር ሰዎች ከራሳቸው የሚፈልቅ መረጃ ወይንም ዕውቀት ከዚያ አገር ህዝብ በራቀ መጠን ጉልበቱ ይቀንሳል፤ የአገሩ ሰዎች መረጃውን በመተርጎሙና በማጠናቀሩ በኩል የተሻሉ በመሆኑ (ነው)፡፡” (ገጽ 212፣ 213)
    ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ኢትዮጵየያዊያን ጸሀፍት ወደ ውጭ ምንጮች አብዝተው ማማተራቸው ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ጸሀፍቱ የባንዶች ልጆች መሆናቸው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በትክክለኛ የትምህርት ስርዓት አለማለፋቸው ነው፡፡

6 የታሪክ ክሽፈቱ ያመጣብን መዘዞች
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን እምነት የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈት አገሪቱንና ህዝቦቻን ብዙ ዋጋ አስከፍላል፡፡ በአዳፍኔ መጽሀፍ በተለያየ መንገድ የተገለጹ ሀሳቦችን ከሰበሰብናቸው የታሪክ ክሽፈቱ መዘዞች ሶስት ናቸው፡፡
 ከኢትዮጵያ አንድነት አንጻር
 ኢትዮጵያ በቁሳዊ ስልጣኔ ሃላ ቀር እንድትሆን ከማድረግ አንጻር
 ከኢትዮጵያ መንፈሳዊ ስልጣኔ (ሉዓላዊነት) አንጻር
6.1 የታሪክ ክሽፈትና የኢትዮጵያ አንድነት
በመጽሀፉ እንደተገለጸው የህዝብ አንንነትነ የአገር መሰረት የሆነው ህዝቦች በክፉ ጊዜ አንድ መሆን፣ መተባበርና ለአገራቸው ክብርና ሉኣላዊነት ቀናኢነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መሰረትም ይኸው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ከታሪክ ክሸፈቱ ጋር አብሮ እየከሸፈ ይገኛል፡፡ በዚህም
“……..የአንድ ትውልድ ስህተት ወደሌላ ትወልድ እየተላለፈ ለብዙ ትውልዶች የስህተት ምንጭ (እየሆነ) ታሪካችንንና የኢትዮያን ህዝብ ህዝብነት (በመበከል) ዛሬም እንደቆላ ቁስል እነዘነዘን (ነው)፡፡” ገጽ 29
በመጽሀፉ እንደተብራራው የታሪክ ክክፈቱ አገር እንዲፈርስ በር ከፍታል፤ ለወደፊቱም በር መክፈቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ የቀረበው ደግሞ የታሪክ ክሽፈቱ አንዱ ማሳያ የሆነው የኢትዮጵን ታሪክ ከመሃሉ ወይም ከአሁኑ የመጀመር የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ኤርትራ የኢትዮጵያ መሰረት መሆናን ማስካድ ለጊዜውም ቢሆን ተችላል ( ገጽ 97)
የኢትዮጵያ ታረክ ክሽፈት ሌላኛው ገጽታ የሆነው የትናንቱን የኢትዮጵያን ዕውነት መካድ የወደፊቱን የኢትዮጵያ አንድነት የሚያናጋ ነው፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የቀረበው ደግሞ በቀዳማዊ ሀይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ ስልጣን (ታስቦበት የተደረገ ባይሆንም) በመንግስት ስልጣን ላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች ስብጥር የመሆኑ ዕውነት ተቀብሮ ያለፈው ስርዓት የአንድ ብሄር ( የአማራ ብሄር) የበላይነት እንደነበር ተደርጎ የሚነገረው የበሬ ወለደ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዋና የፖለቲካ ገጽታ የሆነው ጎሰኝነት መሰረቱም ይህ ሀሰተኛ የታሪክ ትርክት ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ጎሰኝነትና እንዲያብብ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲቀጭጭና አገር የመበታተን አደጋ ላይ እንዲወድቅ መሰረት ሆናል፡፡
ይህንን ሁኔታ ፕሮፌሰር የገለጹት በዚህ መንገድ ነው፡-
……..ችግሩ ሁሉ ከአገዛዝ ጋር የተየያዘ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለ…….የአጼ ሀይለ ስላሴና ደርግ አገዛዝ የ‹‹አማራ›› ሆነው በመፈረጃቸው ውግዘቱ ሁሉ ያንን ቃንቃ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ተወረወረ፤ አስተሳሰቡ ቀላል በመሆኑ ዛሬም የወያኔን አገዛዝ የትግሬ አገዛዝ የሚያደርጉት አሉ፤……(ይህ)ከተዛባ አሰተሳሰብ የሚመነጭ ስህተት ነው፡፡ ገጽ 39
6.2 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈትና ቁሳዊ ስልጣኔ
የኢትዮጵያ የታረክ ክሽፈት ሌላኛው ገጽታ ህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ዋጋ እንዳይሰጥ ማድረጉ ነው፤ ይህም ከትናንቱ ህይወቱ ትምህርት ወስዶ የነገ ህይወቱን ለማሻሻል እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ የብልጽግናና የለውጥ መሰረት የሆኑ እሴቶች፡ ለአብነትም ጠንካራ የስራ ባህል፣ ትጋት፣ ለገንዘብና ለጊዜ ዋጋ አለመስጠት፣ በጋራ የመስራትና የመተባበር ባህልን በኢትዮጵዊያን ዘንድ ብዙም ቦታ የላቸውም፡፡
“……….ዳገቱን እንዴት እንደወጣንና ቁልቁለቱን እንዴት እንደወረድን በትክክልና በዕውነት (እንድንገነዘብ)፣ ክብርና ኩራት ማን ወይም እነማን እንዳስገኙልን ተጨንቀን ሳናስብነና ሳንመዝን ለማይገባው (እንድንሰጥ)፣ በውጤቱም የሰራው እየተረሳና እየተወደሰ ከትውልድ ወደ ተውልድ ይተላለፋል፡፡…..ስለዚህም መስራት የማስከብርና የማያከብር ይሆናል፤……..ሳይሰሩ ለመክበርና ለመከበር መጣር ባህል ይሆናል፡፡”ገጽ 73-74
6.3 የኢትዮጵያ የታሪክ ክሽፈትና መንፈሳዊ ስልጣኔ (የአገር ሉዓላዊነት)
እንደ ፕሮፌሰር መስፍን እምነት የኢትዮጵያ ስልጣኔ መንፈሳዊ ስልጣኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሳይከሽፍ የቆየውም ለዚህ ነው፡፡ ምንም እንካን ኢትዮጵያ በቁሳዊ ሀብትና ዘመናዊነታ ሃላ የቀረች ቢሆንም ድህነታ ግን ለውጭ ወራሪዎች እጅ እንድትሰጥ አላደረጋትም፡፡ ለዚህ ምከንያቱ የመንፈሳዊው ስለጣኔ መገለጫ የሆኑትና ለዘመናት የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሆነው የኖሩት አርቆ አሳቢነት፣ ሀይማኖተኝነትና ፈሪሃ እግዚአብሄር፣ መልካም ስነ ምግባር፣ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ለክብርና ኩራት ቅድሚያ መስጠት፣ ለአገር ነጻነትና ሉዓላዊነት መስዋዕትነት ተጋድሎ ማድረግ ወዘተ…. ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ መንፈሳዊ ስልጣኔ እስከመጨረሻው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አልተቻላቸውም፡፡
የታሪክ ክሽፈቱ አንዱ ውጤት የሆነው የህዝቡ ለቁሳዊ ሀብት ያለው ዝቅተኛ ግምት ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በእጅጉ በኢኮኖሚ ወደሃላ አስቀርታታል፡፡ ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ በአዳፍኔ መጽሀፍ የተገለጸው በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ሀይል ኢትዮጵዊያን አርበኞችን በማይጨው የጦር አውድማ ድል መንሳቱ ነበር፡፡ ለዘመናት ተከብሮ የኖረው የአገር ሉኣላዊነት ተደፈረ፡፡ኢጣሊያ ጦር ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ፣ በምድርና በአየር በወገን ጦር ላይ መኣቱን ሲያወርድ ፣ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ግን ከሃምሳ አመታት ቀደም ብሎ በአድዋ ጦርነት ታጥቀው የዘመቱትን ባህላዊ መሳሪያዎች ነበር፡፡ በዚህም፡-
“………ኢትዮጵያ ያለችበትን በታም ዝቅተኛና ቆሞ ቀር ደረጃ በተግባር አስመሰከረች፤ይህ አዲስ ዕውነት የኢትዮጵ ህዝብ ለዘመናት የነበረውን አልበገር ባይነት ከነኩራቱና ክብሩ ገፈፈው፤ የመንፈስ ሃይሉ ደቀቀ፤ አንገቱን ደፋ፡፡” ገጽ 133
በአጠቃላይ ከአምስቱ ዓመታት የፋሺስት ወረራ በሃላ በኢትዮጵያን የመንፈሳዊ ስልጣኔው የከሸፈ ይመስላል፡፡ ለግል ጥቅም ሲባል ያልተገቡ አገርን በገንዘበ መለወጥ ወይም ባንዳነት፣ ህዝቡ የአገርን ችግር በአገር ቤት ከመጋፈጥና ለመፍታት ከመጣር ስደትን መምረጡ፣ ኢትዮጵያዊ ክብርና ኩራት እተመናመነ መሄዱ፣ አርበኝነት ቦታ ሲያጣ ባንዳነት መወደሱ ወዘተ.…… ማሳያ ናቸው፡፡ በውጤቱም ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሉኣላዊነት አደጋ ላይ ወድቃል፡፡
በአጠቃላይ የታሪክ ክሽፈቱ መዘዞች በተለይም ባለፉት 85 ዓመታት ጎልተው ታይተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ያቀረቡትን ትንታኔ ጠቅለል ባለ ሁኔታ በሚከተለው ምስል ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡

  1. የኢትዮጵያ ታሪክን ከክሽፈት ቁልቁለት እንዴት መታደግ ይቻላል?
    7.1 ህዝቡን በተመለከተ
    የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት አዘቅት ይላቀቅ ዘንድ ህዝቡ የራሱን ሚና መወጣት እንዳለበት ለዚህም በመጽሀፉ መጨረሻ ላይ የምናገኛቸው አስር መፍትሄዎችን መከተል አለበት፡፡
    7.2 አገዘዙን በተመለከተ
    በመጽሀፉ ላይ አገዛዙ ማድረግ ያለበት ነገር በቀጥታ አልተገለጸም፡፡ይሁንና አገዛዞች ከቀደመው አገዛዝ ስህተቶች መማር፣ መልካም ጎኖች ደግሞ ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው በተዘዋዋሪ ይመክራሉ፡፡
    “………ቀደም ያለው (አገዛዝ) የሰራውን በሃላ መታው ያፈርሰዋል ወይም ይደብቀዋል፤ ታሪክን የአገርና የህዝብ አድርጎ በመመልከት ፋንታ የግል በማድረግ ታሪክ ያለባህሪው እንዲያትርና በሰው እድሜ እንዲለካ ያደርጋል፤ ታሪክ የሚከሽፍበት አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡” ገጽ 133
    7.3 የታሪክ ጸሀፍትን በተመለከተ
    በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊያን ጸሀፍትን በተመለከተ ሊስተካከሉ የሚገባውና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እንዲህ ይመክራሉ፡-
  2. ስለታሪክ ያላቸውን አረዳድ የተዛባ አረዳድ ማስተካከል፡፡ ይህ ከሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ ከይዘት እና ከጊዜ ጥልቀትና ስፋት አንጻር ያለው ውስንነት ይታረማል፡፡ በዚህም፡-
    ሀ. የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነትና የነገስታት ታሪክ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ከዚያ ውጭ ያሉ ርእሰ ጉዳዮች ማለትም የህዝቡ ማህበረ-ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮች፤ ስለኢትፕያ ስነጽሁፍ፣ ቃንቃዎችና ሌሎችም በርካታ ታሪካዊ ጉዳዮች የታሪካችን አካል ማድረግ ይቻለል፡፡
    ለ. የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ አመት ወይስ የሶስት ሺህ አመት የሚለው ክርክር እልባት ሊያገኝ ይችላል፡፡ በእርግትም ኢትዮጵያ ሶስት ሺህ አመት ዌም ከዚ በላይ እድሜ ያላት አገር እንደሆነች ለመረዳት ያስችላል፡፡
    ሐ. የኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት አንዱ መገለጫ የሆነው በጎ ታሪክን ብቻ ጽፎ የማቆየትና ያለፍንባቸውን ውጣውረዶችና ችግሮቻችንን የመዝለሉ ጉድለት ሊቀረፍ ይችላል፡፡
  3. ያለፉበት የትምህርት ስርኣት ችግር ያለበት መሆኑን መገንዘብና ከችግሩ ለመንጻት ንስሃ መግባት ሌላው መፍትሄ ነው፡፡ በመጽሀፉ እንደተመለከተው፡-
    ….የውጭ ሊቃውንቱ ትናት ልዩ ጥቅም ቢኖረውም ባይኖረውም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚያደርጉት ትናት በጭራሽ ልንቃወም አንችልም፤ የምቃወመው እነሱ አኛን እንደፈለጉ አድርገው ሊቀርጹን የሚያደርጉት ሙከራ ነው፤ እኛም እነደጥቁር ሰሌዳ የእነርሱን ነጭ ጠመኔ የበህርይ አድርገን መቀበላችን ነው፡፡ ገጽ 213
  4. ከጥቅመኝነት፣ ከጎሰኝነት፣ ከፍርሃትና ስጋት ራሳቸውን ነጻ ማውጣት አለባቸው፡፡

Discover more from ሩህ ሚዲያ – Ruh Media

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Posted in

አስተያየት ያስቀምጡ

ይህ ጣቢያ አይፈለጌ መልዕክትን ለመቀነስ Akismet ይጠቀማል። የአስተያየትዎ ውሂብ እንዴት እንደሚሰናዳ ይወቁ

Discover more from ሩህ ሚዲያ - Ruh Media

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading